
አዲስ አበባ፡- “ሀገር የቅብብሎሽ ውጤት ስለሆነ ትውልድን እና ነገን አስቦ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ነገን ለመሥራት ትናንትን መዘንጋት አይገባም፡፡ “ሀገር የቅብብሎሽ ውጤት ነው፤ ትውልድን እና ነገን አስቦ መሥራት ያስፈልጋል፤ ለዚህ ነው ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ አስተሣሥረን ሚዛን ጠብቀን ሀገር እንገነባለን ብለን የተነሣነው” ብለዋል።
ይህንንም በንግግር ሳይሆን በተግባር አሳይተናል ሲሉም በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ በአባጅፋር እና የአፄ ፋሲል አብያተ መንግሥታትን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች የተከናወኑ የቅርስ ጥገናዎችን ለአብነት አንሥተዋል።
ትናንትን ብቻ በመጠገን ነገ አይሠራምና ትናንት እና ነገን የሚያገናኝ ድልድይ መገንባት እንደሚያስፈልግም አመልክተው፤ ለዚህም ደግሞ ባለፋት ሰባት ዓመታት የተገነቡ ከገበታ ለሸገር እስከ ገበታ ለትውልድ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን አስታውሰዋል።
“የትላንት ሀብቶቻችንን እየጠገንን እናቆያለን፤ ለዛሬ የሚያስፈልጉትን እንገነባለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ሲሆን የነገ ሕልማችን በግልጽ እንደሚታይ ገልጸዋል።
ለውጡ እንደመጣ በርካታ በግለሰብ ደረጃም በቡድንም ሆነው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ አካላት ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ የተወሰደውን ርምጃ ያስታውሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በውሳኔውም በርካታ ሰዎችን አትርፈናል ብለዋል። በዚያ ውሳኔ መሠረት ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ዕድል ያገኙ ግለሰቦች ሀገራቸውን በትጋት እያገለገሉ መሆናቸው ትልቁ የኢትዮጵያ ትርፍ እንደሆነም ገልጸዋል።
በውሳኔው በርካታ ለረጅም ዘመናት የተለያዩ ቤተሰቦች መገናኘታቸው እና በርካቶች ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በንግድ ጭምር ሀገራቸውን እያገለገሉ መሆናቸው ጨክነን የወሰንነው ውሳኔ ትሩፋት ነው ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ በተመለከተ እንደገለጹት፤ ከኢትዮጵያ ሁኔታ የተነሳ ከሌሎች የተማረና በእኛ ልክ የተሰፋ ሪፎርም ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም መነሻ ራስን ከማየት የጀመረ መሆኑንም አመልክተዋል።
በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ከሀገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር መጠነ ሰፊ ውይይቶች ማድረጉን አስታውሰው፤ በኢኮኖሚ ፈተና ውስጥ ሆነው ወደ ሪፎርም በመሸጋገር ለውጥ ካመጡ ሀገራት ተሞክሮዎች መወሰዳቸውንም ተናግረዋል።
በውይይቶቹ እና ተሞክሮ በመቅሰም የተገኙ ሀሳቦችን መሠረት በማድረግ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ወደ ተግባር መግባቱን አመልክተው፤ በሪፎርሙ አማካኝነትም በኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ለውጦች መመዝገባቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሀገር በቀል ነው ሲባል ከሌሎች አንማርም ዝግ ነን ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት እንደሚገባ ጠቁመው፤ የኢኮኖሚ ሪፎርሙም ሙሉ ለሙሉ ከውጭ የተቀዳ ነው የሚለው አስተያየት ተገቢ እንዳልሆነም ነው ያነሱት።
ከኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ ዓለም ባንክ እና ሌሎች አበዳሪዎች ጋር የተደረጉ ድርድሮች የሀገሪቷን ጥቅም እና ፍላጎት ያስጠበቁ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ፣ የሚጨበጥ እና የሚዳሰስ ለውጥ መኖሩን ተናግረዋል።
መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የዋጋ ንረት ሁኔታ የተከማቸ መዋቅራዊ ችግሮች፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ክስተቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ፈተናዎች ተዳምረው የዜጎችን ኑሮ እየፈተነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
መንግሥት የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ስብራቶች ለመጠገን የሚያስችሉ ሁሉን አቀፍ የማሻሻያ ሥራዎችን ማከናወኑን ተናግረው፤ በሪፎርሙ አማካኝነት በኢኮኖሚው ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ መመዝገቡን ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢኮኖሚው ዘርፍ ከተገኘው ስኬት መካከል የወጪ ንግድን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከ1984 እስከ 1998 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በወጪ ንግድ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ብቻ ማግኘቷን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት ብቻ ከወጪ ንግድ (ከኤክስፖርት) ከ8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታገኛለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
የዋጋ ንረቱን ከነበረበት 34 በመቶ ዘንድሮ 13 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማለቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በገቢ፣ ድህነት ቅነሳ፣ ውዝፍ ዕዳ ከአጠቃላይ ጥቅል ዓመታዊ ምርት አንጻር መቀነሱ ኢትዮጵያ ከዋጋ ንረት እያገገመች ለመሆኗ ማሳያ ነው ብለዋል።
በተለያዩ መስኮች የተገኙ ለውጦች ቀጣዩ ትውልድ የሚረከበውን ዕዳ በመቀነስ የተሻለ ሀገር እንዲረከብ የሚያስችል መሠረት የጣለ መሆኑንም አመልክተው፤ ኢትዮጵያ ከበሽታዎቿ እያገገመች በመዳን መንገድ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያን ትንሣኤ እውን ለማድረግ ያለመታከት መሥራት እና መድከም እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።
የተገኘውን ለውጥ ማጽናት እና ማስቀጠል የሁሉም ወገን የጋራ ኃላፊነት እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም