
የሰኔ ወር ፕላስቲክን የማስወገድ ወር ይሆናል
አዲስ አበባ፡- ለስድስት ወራት የሚቆየው የአካባቢ ብክለት መከላከል እና ጽዱ ኢትዮጵያ የመፍጠር ባህል ንቅናቄ ዛሬ እንደሚጀመር ተገለጸ። የመጀመሪያው የሰኔ ወር የማይታደሱ የፕላስቲክ ውጤቶችን የመከላከል እና የማስወገድ ወር እንደሚሆን ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ንቅናቄውን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ‹‹ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ›› በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ የሚጀመረው ንቅናቄ ባለፈው ዓመት የተጀመረውን የጽዱ ኢትዮጵያ ዘመቻ የሚያስቀጥል ነው። ባለፉት ወራት ‹‹ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ›› በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ የቆየው የጽዱ ኢትዮጵያ ዘመቻ ብዙ አካባቢዎችን ንጹህ አድርጓል። ባለፉት ስድስት ዓመታት በተደረገው የአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ እና ባለፈው አንድ ዓመት በተሠሩ የኮሪዶር ልማቶች ጽዳትና ውበትን ማሳየት ተችሏል።
በቀጣይ ስድስት ወራት ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል የማድረግ ንቅናቄ ይጀመራል። ለዚህም የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ እና የሕግ ማሕቀፎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ንቅናቄው የሚጀመረው በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ነው። የሕግ ማሻሻያ እና የሕግ ማሕቀፎች ቢዘጋጁም ከፍተኛ ክፍተት የሚታየው በግንዛቤ ላይ ስለሆነ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ግንዛቤ መፍጠሩ ላይ ከፍተኛ ሥራ ለመሥራት ተዘጋጅቷል።
በንቅናቄው ከ15 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የገጽ ለገጽ ገለጻ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ ከ50 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮች ግንዛቤ ይሰጣል። ግንዛቤ ከመስጠት ባሻገርም የቁጥጥር እና ክትትል ሥራዎች ይሠራሉ። ንቅናቄውን ተግባራዊ ለማድረግ እና ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል ለማድረግ በየዘርፉ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር ይሠራል ብለዋል።
‹‹የሰኔ ወር የፕላስቲክ ብክለትን የመከላከል ወር ነው›› ያሉት ኢንጂነር ለሊሴ፤ የፕላስቲክ ብክለት ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት በከተሞች መስፋፋት ምክንያት ፕላስቲክ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ስለሆነ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ኢንጂነር ለሊሴ ገለጻ፤ የፕላስቲክ ብክለትን ለመከላከል እና ለማስወገድ የሚያስችል የሕግ ማሕቀፍ ስለተዘጋጀ ከሰኔ ወር ጀምሮ ንቅናቄው ይጀመራል፤ ፕላስቲክ አለመጠቀምን ባህል ለማድረግ ይሠራል። አንድ ፕላስቲክ ለመበስበስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት የሚወስድበት ስለሆነ ህብረተሰቡ ይህን ሊያውቅ ይገባል ብለዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ስድስቱም ወራት የየራሳቸው ንቅናቄ ያላቸው ሲሆኑ የሐምሌ ወር የአፈርና ውሃን ብክለት የመከላከል፣ ነሐሴ የአየር ብክለትን የመከላከል፣ መስከረም የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ ጥቅምት የድምጽ ብክለት መከላከል እና የሕዳር ወር አጠቃላይ የአካባቢና ተፅዕኖ ግምገማ እና የሕግ ተከባሪነት የሚረጋገጥበት ይሆናል ብለዋል።
በመንግሥት የሚለሙ ፕሮጀክቶች፣ በልማት ድርጅቶች እና በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እና በውጭ ኢንቨስተሮች የሚለሙ ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ሥነ ምህዳር በሚጠብቅ መልኩ መሆኑ እንደሚታይ አመልክተዋል። ተግባራዊ ማድረጋቸውም በኦዲት ይረጋገጣል ነው ያሉት።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በእያንዳንዱ ወር መጨረሻ ላይ አፈፃፀሞች ይገመገማሉ፤ ጥሩ አፈፃፀም ያሳዩ ተቋማት፣ አካባቢዎችና ግለሰቦች ዕውቅና ይሰጣቸዋል። ጽዳትን ባህል ለማድረግ መገናኛ ብዙኃን በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
በኮሪያ ሪፐብሊክ አስተናጋጅነት ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የዚህ ዓመት የዓለም የአካባቢ ቀን ‹‹የፕላስቲክ ብክለትን ማስወገድ›› የሚል መሪ ቃል ያለው ሲሆን ለ52ኛ ጊዜ ይከበራል።
የኮሪያ ሪፐብሊክ የዓለም የአካባቢ ቀንን ለሁለተኛ ጊዜ የምታዘጋጀው ሲሆን ለፕላስቲክ አወጋገድ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ እና የሀገራት መልካም ተሞክሮ ልምድ የሚለዋወጡበት ይሆናል። በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ የሚከበረው ይህ የዓለም የአካባቢ ቀን ‹‹ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል ማድረግ›› የሚል መሪ ሃሳብ ያለው ሲሆን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በሚገኙበት ዛሬ በስካይላይት ሆቴል በፓናል ውይይት ይጀመራል።
በዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም