
አዲስ አበባ፡- ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ማግኘት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ሲሉ ሌተናል ጀነራል ዮሃንስ ገብረመስቀል ተናገሩ።
ሌተናል ጀነራል ዮሃንስ ለወጋሕታ ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጉዳይ በአዎንታዊ መልኩ ከተመለሰ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የቀጣናው ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ ። በተለይ የቀጣናው ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በሰላምና ጸጥታ ጉዳይ የሚኖራቸው ተጠቃሚነት ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚ ስትሆን አብሮ ለማደግ ይጠቅማል እንጂ የትኛውንም ሀገር አትጎዳም ያሉት ሌተናል ጀኔራል ዮሃንስ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ለኢኮኖሚና ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ እልባት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የጀመረችው እንቅስቃሴ ትክክል ነው፣ በሰላም እንጂ በኃይል አትሄድም፤ ምላሹ አወንታዊ ከሆነ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል ሲሉ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ካገኘች በቀጣናው ያሉትን ሁሉንም ሀገሮች ይጠቅማል ፣ ጥያቄውም ትክክል እና ፍትሃዊ ስለሆነ ሌሎች ሀገራት በቀናነት ሊቀበሉት ይገባልም ብለዋል።
የባሕር በር ጉዳይ ለትብብር ፣ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ሰላምና ደህንነት የሚጠቅም በመሆኑ ሌሎች ሀገሮች ሊደግፉ እንደሚገባ አመልክተው፤ ይህን ጉዳይ ሁሉም ኢትዮጵያዊም ሊደግፈውና ለስኬቱም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም መክረዋል።
የባሕር በር የኢትዮጵያ ቁልፍ ጉዳይ ነው፣ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ስትሆን ቀጣናው ሁሉ ተጠቃሚ ይሆናል፣ ከዚህ መነሻነትም የቀጣናው ሀገሮችም በአሉታዊ መልኩ ሊያዩት አይገባም፤ የጥያቄው ምላሽ ማግኘት ለደህንነት፣ ለትብብርና ዕድገት በጣም ጠቃሚ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ አወንታዊ መልስ ካገኘ ቀጣናውን ይጠቅማል እንጂ ምንም ጉዳት እንደሌለው ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ሊያድጉ የሚችሉት በመደጋገፍና በመተባበር እንጂ ባልተገባ ፉክክር አይደለም ያሉት ሌተናል ጀነራል ዮሃንስ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለብቻዋ ሳይሆን አብሮ ለማደግ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
“አብረን እንደግ እንደጋገፍ ማለት በአሉታዊ መልኩ መታየት የለበትም” ያሉት ጀኔራሉ፤ የቀጣናው ሀገራት ሰፊ የባሕር በር እያላቸው የማይጠቀሙት ከሆነ ምንም ትርጉም የለውም። ሁላችንም በስምምነት ከተጠቀምንበት ግን ለሁላችንንም ይጠቅመናል እንጂ አይጎዳንም፤ አለመጠቀም ትውልዶችን ከመጉዳት በስተቀር ምንም ትርጉም የለውም ብለዋል።
ለሚቀጥለው ትውልድ ሊታሰብበት ይገባል፤ ይህ እንዲሆን ከተፈለገ ደግሞ የኢኮኖሚው ችግር መፈታት አለበት፣ ቅንነት ካለ እና የባሕር በሩ ኢትዮጵያ ብትጠቀምበት ግን ሁሉንም ይጠቅማል እንጂ የሚጎዳ የለም ሲሉ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጉዳይ ለቀጣናው ሀገራት ስጋት አይደለም፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በጉልበት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ የቀረበ ነው፤ ኢትዮጵያ እንነጋገር፣ አብረን እንጠቀም፣ አብረን እንድግ ነው እያለች ያለችው ብለዋል። በዚህም ሕዝቡን ይጠቅማል እንጂ ጉዳት የለውም ሲሉ አመልክተዋል።
በመኣረግ ገ/ሄር
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም