
. በሰኔ 15ቱ ግድያ ላይ በቂ መረጃ አለው
አዲስ አበባ፡- መንግሥት በቀጣይ ዓመት የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር በአቅርቦት ላይ በመመስረት በስፋት እንደሚሰራ ገለጸ። በሰኔ 15ቱ ግድያ ላይ መንግሥት በቂ መረጃ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ባለፉት 15 ዓመታት የዋጋ ንረቱ 15 በመቶ እያደገ ቢቆይም ባለፈው ዓመት ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት መቀነስ ተችሏል። ሆኖም ግን ከግንቦት/2011 ዓ.ም ወዲህ ግን አሻቅቧል ብለዋል።
የዛሬ 28 ዓመት የኢትዮጵያ ሕዝብ 48 ሚሊዮን ነበር። አሁን ከ100 ሚሊዮን በላይ ቢደርስም የሚታረሰው መሬት ግን ያው መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የፍላጎትና የአቅርቦት ያለመመጣጠንን ችግር ለማቃለል ምርታማነቱ የተወሰነ ለውጥ ቢያመጣም የሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፊት የነበረው የአገሪቷ የ78 ቢሊዮን ዶላር ምርት አሁን ወደ 84 ቢሊዮን ብቻ ማደጉን ጠቁመው፤ አጠቃላይ የሀብት ዕድገት በመኖሩ በፊት የነበረው የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ160 ዶላር አሁን 884 መድረሱን ተናግረዋል። በዚህም ኢኮኖሚው በፍላጎት ላይ የተመሰረተ እና የሰዎች ፍላጎት እና የቴክኖሎጂ ዕድገት በማሻቀቡ እና ምርታማነት ባለማደጉ በአማካኝ ባለፉት 15 ዓመታት የዋጋ ንረቱ 15 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል።
ምክንያቱ አንድም ኢኮኖሚው በፍላጎት ላይ በመመስረቱና ምርታማነት ባለማደጉ በመሆኑ ኢኮኖሚውን አቅርቦት ላይ ለመመስረት መንግሥት በቀጣይ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በተያዘው ዓመት ዝናብ አይኖርም የሚል ሥጋት ቢኖርም የተሻለ ዝናብ በመኖሩ በምርት ላይ ተስፋ እየታየ ሲሆን፤ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ በሚሰጋባቸው የዘይት እና የስንዴ አቅርቦት ላይ ቀድሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጨምረውም፤ የመንግሥት ዋነኛው ትኩረት ኢኮኖሚው በመሆኑ የሁሉንም ክልል ኃላፊዎች እና ሚኒስትሮችን ያካተተ እንደችግኙ ዓይነት ኮሚቴ በማዋቀር ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን የመፍጠር፤ መስኖ ላይ ያለውን ገንዘብ በአግባቡ የመጠቀምና ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን የመቆጣጠር ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የሰኔ 15ቱን የጄነራል ሣዕረ መኮንን እና የጄነራል ገዛኢ አበራን ገዳይን በሚመለከት፤ ጠባቂው አንገቱ ላይ በመቁሰሉ መናገር ስለማይችል ምንም ዓይነት መረጃ ለማግኘት ቢያዳግትም ከእርሱ ጋር በስልክ የተነጋገረው ሰው መያዙን ተናግረዋል። የአማራ ክልሉ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራና ግድያ ሲፈፀም አንተ ቴሌቪዥን ስለምታይ ትነግረኛለህ የተባለው ሰው እና ያንንም መረጃ የተናገረው ሰው መያዙን ገልፀዋል።
ገዳዩ ገዳይ ላለመምሰል ያደረገውን ሙከራም የተያዘው ጓድ የተናገረ ሲሆን፤ የክልሉን መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከትሎ ሌሎች ሰዎችን ለመግደልና መሰል ሥራ ለማከናወን ሊሰማሩ የነበሩ ሰዎችም መያዛቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ግድያውን በሚመለከት በብዙ መንገድ ተባባሪ የሆኑ በአገር ውስጥ፤ ከአገር ውጪ፤ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ያሉ መገናኛ ብዙኃን በመርዳት እና የጦር መሣሪያ በመግዛት የሚያግዙ፤ ቀድመውም እንዲህ ዓይነት ነገር ሊፈፀም እንደሚችል ሲናገሩ የነበሩ ስለመኖራቸው በርካታ መረጃ በመኖሩ ይህንን ለሕግ በሚያግዝ መልኩ ባለሙያዎች እንደሚያደራጁት ገልጸዋል። መንግሥት በቂ መረጃ ያለው መሆኑን እና ዋና ዋና ጠንሳሾች በሕግ እንደሚጠየቁ፤ እንዲሁም በገንዘብ ተታልለው የተሳተፉትም የማስተካከያ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ሰኔ 15 ኢትዮጵያን የገጠማትን
ችግር ለመቆጣጠር መንግሥት የተጠቀመው የአመራር ብቃት አስደናቂ መሆኑን እና መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል። ወደፊት በዝርዝር በጽሑፍም ሆነ በሌላ መልክ ሊቀርብ እንደሚችል ጠቁመው፤ እንዲህ ዓይነት ተግባር እንዳይደገም በጋራ መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል።
ከሲዳማ የክልል ጥያቄ ጋር ተያይዞ የነበረውን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተቃጠለውን የአረጋሽ ሎጅን እንደምሳሌ በማንሳት ድርጊቱን የፈፀሙት ከሲዳማ ሕዝብ ውጪ የሆኑ ዱርዬዎች እና ሌቦች መሆናቸውን አመልክተዋል። ጨምረውም አንዳንድ አግባብ ያላቸውን ጥያቄዎች ተከትሎ የሚቀላቀል የሌቦች ተግባር መኖሩ የሕግ መላላት ያለ ቢያስመስልም መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማክበር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመንግሥትና በመሪ ድርጅቱ መካከል ያለውን አንድነት በሚመለከት ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን በሰጡት ምላሽ፤ እንደመገናኛ ብዙኃኑ ሁሉ ሁለቱም ቡራቡሬ መሆናቸውን፤ አንዳንዱ ድሮ በነበረበት አስተሳሰብ ላይ ተቸክሎ የቀረ፤ ሌላው ደግሞ ወላዋይ፤ ጠዋት ጠንካራ ከሰዓት ልፍስፍስ ሲሆን፤ ለለውጥ የሚንቀሳቀሱም መኖራቸውን እና ለውጡን በአንድ ጀንበር ማምጣት የሚያስቸግር መሆኑን ተናግረዋል።
ክልል ላይ የከፍተኛ አመራር ለውጥ ተደርጓል። የሚኒስትሮች ለውጥም ተካሂዷል። የዳይሬክተር ለውጥም እንደዚያው፤ ሆኖም ሰው መለወጥ ብቻ ችግሩን እንደማይፈታ ለማወቅ ቢቻልም ወደፊት በዝርዝር እንደሚታይ እና መገናኛ ብዙኃኑም ውጤት የማያመጡትን ተቋማት ተከታትለው መጠየቅ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች የአዴፓን እና የህወሓትን መግለጫ፤ የፓርቲዎችን መዋሃድ፣ የሱዳንን ጉዳይ፤ የኢንተርኔት መዘጋትን እና ከሰኔ 15ቱ ጋር ተያይዞ አፈና እየተካሄደ መሆኑን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2011
ምህረትሞገስ