በሆስፒታሉ ያለውን ከፍተኛ የቁሳቁስ እጥረት ለመቅረፍ አጋር አካላትን ያሳተፈ ቅንጅታዊ ሥራ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያለውን ከፍተኛ የቁሳቁስ እጥረት ለመቅረፍ አጋር አካላትን ያሳተፈ ቅንጅታዊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቺፍ ኤክስኪዪቲቭ ዳይሬክተር እና የሕጻናት ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ፍቅረጽዮን ደገሙ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በሆስፒታሉ በሁሉም ዲፓርትመንቶች ከፍተኛ የሆነ የመሣሪያ እጥረት አለ፤ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ አጋር አካላትን ያሳተፈ ቅንጅታዊ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

ችግሩ በመንግሥት በጀት ብቻ የሚቀረፍ ባለመሆኑ የተለያዩ አማራጮችን እየተከተልን እንገኛለን ያሉት ዶክተር ፍቅረጽዮን፤ አገልግሎት መስጠት እንዲቻልም ከሀገር ውጭ ከሚኖሩ ዲያስፖራዎች፣ ከአካባቢው ተወላጆች እንዲሁም የተለያዩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከመሣሪያ እጥረቱ በተጨማሪም ብልሽት ያጋጠማቸው ማሽኖች በአጭር ጊዜ ጠግኖ ወደ አገልግሎት ከመመለስ አኳያ ችግር እንዳለ አመልክተዋል፤ ለማምረትም ሆነ መሣሪያዎችን ጠግኖ ለመጠቀም የተለየ እውቅት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

ሆስፒታሉ በነፃ የሚሰጣቸው በርካታ የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች እንዳሉ አመልክተው፤ ለአብነትም የማዋለድ አገልግሎት፣ የጨቅላ ሕጻናት ሕክምና፣ የምግብ እጥረት ያለባቸውን ሕጻናት መርዳት፣ የቲቪ ሕክምና እንዲሁም የኤች አይቪ ሕክምና ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ዶክተር ፍቅረጽዮን፤ በተያዘው በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ ሆስፒታሉ ከዘጠኝ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የነፃ አገልግሎት ሰጥቷል፤ ከዚህ በተጨማሪም የሆስፒታሉ ባለሙያዎች በየጊዜው የገንዘብ መዋጮ በማድረግ የሕክምና ወጪያቸውን መሸፈን ለማይችሉ ዜጎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል። ወደ ማኅበረሰቡ በመውረድም ሙያዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ሆስፒታሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ ይበልጥ ችግር የሆኑበት ዘርፎች በመለየት አዳዲስ አገልግሎቶች እያስፋፋ ይገኛል ያሉት ዶክተር ፍቅረጽዮን፤ በቅርቡም የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ከወረቀት ነፃ የሆነና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት ኮምፒዩተር የማሰባሰብ፣ የተለያዩ መሠረተ ልማት የሟሟላት እና የኔትዎርክ ዝርጋታዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

እንደ ዶክተር ፍቅረጽዮን ገለጻ፤ ሆስፒታሉ በስሩ ለሚገኙ ሰባት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የተለያዩ ድጋፎች ያደርጋል፡፡ በቀጣይም አሁን የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በማዘመን አዳዲስ ሕክምናዎች ለመስጠት ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

የሕክምና ግብዓት በተለይ የመሣሪያ ግብዓት በዚህ ዘመን ለሕክምናው ዘርፍ ፈተና ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ መሆኑን አመልክተው፤ መሣሪያዎችን ለማስጠገን ሆነ በግዢ ለማቅረብ የሚፈጥረው የበጀት ጫና ከፍተኛ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ዶክተር ፍቅረጽዮን ደገሙ

በልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You