አዳዲስ የልማት ፋይናንስ አቅሞችን እየለዩ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- አዳዲስ የልማት ፋይናንስ አቅሞችን እየለዩ መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር ) አስታወቁ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት እና ለሴቶች እና ልጃገረዶች ጤና ጥበቃ የሚውሉ ሁለት የብድር ስምምነቶችን በትናንትናው ዕለት አፅድቋል፡፡

ምክር ቤቱ ካፀደቃቸው የብድር ስምምነቶች አንዱ ‹‹ለተቀናጀ የውጤታማ ግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማትና ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ፤ ዓረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት ከተሰኘው የፋይናንስ ተቋም ጋር የተደረገው የ49 ሚሊዮን 550 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የብድር ስምምነት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 33ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ስለብድር ስምምነቱ ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ በግብርና ላይ የሚሠራው ሥራ መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ነው፤ ይህ ፕሮጀክትም ዘርፉን ከመደገፍ አንጻር ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ግብርና ላይ ያተኮሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተሳስረው በአካባቢው ያሉና የተደራጁ አርሶ አደሮችን ወደ ሥራ ማስገባት እንዲችሉ ፕሮጀክቱ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ውሃን ጨምሮ በአካባቢው ያለውን ሀብት የሚጠቀም በመሆኑ አሳታፊና አካታች እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በጣም በርካታ የልማት ፋይናንስ አቅሞችን በደንብ እየለዩ መጠቀም የሚያስፈልግ እንደሆነ ጠቁመው፤ አሁንም ከኢነርጂ ጋር በተያያዘ ሌሎች የብድር ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን ሚኒስቴር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡

እንደሀገር ሊሠሩ የታሰቡ መንገዶችንም ለመጨረስ ከትሪሊዮን በላይ የሚገመት ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት እንደሚያስፈልግና ከብድር ተቋማትም ጋር እንዲህ ዓይነት ስምምነት ማድረግ እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡

በዓለም ባንክ፣ በኮሪያ ኤግዚም ባንክ እና በቻይና ኤግዚም ባንክ፣ የብድር አገልግሎቶች ሲሰጡ እንደነበር አስታውሰው፤ ከዓረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማትም ተመሳሳይ ብድር መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ገቢን የማሳደግና ከልማት አጋሮችም ሀብት የማሰባሰቡ ሥራ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡ የተገኘውን ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል ረገድም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምሳሌነት የምትጠቀስ መሆኗን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) የስምምነቶቹን አስፈላጊነት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ገንዘቡ ለሦስት ዋና ዋና ፕሮጀክቶች ማለትም፤ በግብርና ኢንዱስትሪ አካባቢ የሚገኙ የመስኖ አውታሮችን ለማስፋፋት፣ የማማከር አገልግሎት እና የገበሬ ማኅበራት እና ተቋማት ለሚያደርጉት የመስኖ ልማት ሥራ የአቅም ግንባታ እና የቁሳቁስ ድጋፎችን ለማድረግ የሚውል ነው፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ በዝናብ ውሃ ላይ የተመሠረተውን የእርሻ ዘዴ ወደ ዘመናዊ የመስኖ ግብርና አሠራር በማሸጋገር የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፤ በአካባቢው የሚገኙ ወጣቶችን ክህሎት በማጎልበት የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

በብድር የተገኘው ገንዘብ የሀገራችንን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን የግብርና ዘርፍ ወደ ዘመናዊ የመስኖ ግብርና አሠራር በማሸጋገር የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር ለማስተሳሰር ያለመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ብድሩ በአነስተኛ ወለድ በረጅም ጊዜ የሚከፈል እና ከአፍሪካ ልማት ባንክ በርዳታ ከተገኘው ገንዘብ ጋር ተጣጥሞ ጥቅም ላይ የሚውል ስለመሆኑም አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል የተደረገው የ45 ሚሊዮን 100ሺህ ኤስዲአር በዕለቱ ምክር ቤቱ ያፀደቀው ሌላው የብድር ስምምነት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

እንደ አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ ብድሩ የሴቶችን እና ልጃገረዶችን ጤና አጠባበቅ አገልግሎት ሽፋን እና ጥራት ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ ታምኖበታል፡፡ በተለይም ዝቅተኛ አፈጻጸም ባላቸው እና በአየር ንብረት በተጎዱ ጂኦግራፊያዊ አካባቢዎች የሚተገበር የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል እና አዳዲስ የጤና ሥርዓቶችን የሚያጠናከር እንደሆነ አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያጠቃቸው የሀገሪቱ ክፍሎች፤ በተለይም በመውለድ ዕድሜ ላይ ያሉ ሴቶች፣ እናቶች ከጨቅላዎቻቸው ጋር እና ከ5 እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ልጃገረዶች ላይ ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም እና በቴክኖሎጂ የተሻሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ መሠረተ ልማትን በመገንባት የአገልግሎት አሰጣጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለታካሚዎች ምቹ እና የሚስብ የጤና ተቋምን በማቋቋም ያልተደረሱ አካባቢዎች እና የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመድረስ ያለመ በመሆኑ ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋልም ብለዋል።

ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር በብድር የተገኘው ገንዘብ ከወለድ ነፃና በረጅም ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም እንደሆነም የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

የአስተያየት ዕድል የተሰጣቸው የምክር ቤት አባላት ሁሉም በብድር ስምምነቱ ላይ አዎንታዊ አስተያየቶችን ሰጥተው፤ የብድር ስምምነቱን ለማፅደቅ የወጣው አዋጅ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡

በዕለቱ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች እና የከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ምክር ቤቱ አዋጁን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡ የምክር ቤቱ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፤ 32ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለጉባኤንም ምክር ቤቱ በዕለቱ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

በኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You