“መልከ ብዙ ግዳጆችን በተመሳሳይ ጊዜ መወጣት የሚችል ጠንካራ ሠራዊት እየተገነባ ነው”›– ኢንጅነር አይሻ መሐመድ የመከላከያ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያዊ ማንነትን ተላብሶ መልከ ብዙ ግዳጆችን በተመሳሳይ ጊዜ መወጣት የሚችል ጠንካራ ሠራዊት እየተገነባ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።

ሚኒስትሯ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ ጊዜው ቀጣናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች የተሟላ ዝግጁነትን የሚጠይቅ ነው። ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያዊ ማንነትን ተላብሶ መልከ ብዙ ግዳጆችን በተመሳሳይ ጊዜ መወጣት የሚችል ጠንካራ መከላከያ ሠራዊት እየተገነባ ነው ብለዋል።

የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ሪፎርም የተካሄደባቸውና ስኬት የተመዘገበባቸው ናቸው ያሉት ኢንጅነር አይሻ፤ ዘመኑ የሚጠይቀውን ትጥቅ ያሟላ እና ወደ ኢትዮጵያ የሚቃጣን የትኛውም ኃይል መመከት የሚችል ዘመናዊ ሠራዊት ተገንብቷል ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ዋነኛ ተልዕኮ የሀገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ማስከበር ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ማፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎችንም ይመክታል። በዚህም መሠረት በክልሎች ጥያቄ አቅራቢነት በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልል የተፈጠሩ የሰላም መደፍረሶችን እና የፀረ ሕዝብ እንቅስቃሴዎች ችግሮችን የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህም በርካታ አካባቢዎች የነበሩ ችግሮች እየከሰሙ፣ ሕዝቡም ተረጋግቶ ወደ ልማት ሥራዎች እየተመለሰ መሆኑን አመልክተዋል።

ሠራዊቱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ከሕዝብ የመነጠል፣ ማንነታቸውን የማሳወቅ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ሰላማዊ ሕይወትን የመረጡ አካላትም ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ እያደረገ ነው። ይህም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የነበሩ አካባቢዎች ወደ ቀደመ ሰላማቸው እንዲመለሱ አድርጓል ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ የሸኔም ይሁን የጽንፈኛው ፋኖ ቡድን ቁመና እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ እያደረጉ ያሉት በየቦታው እየተሽሎኮሎኩ የሽፍታ ሥራዎችን የመሥራት ሁኔታ የሚስተዋልበት ነው። ከዚህ ውጭ ለመከላከያ ሠራዊት ስጋት የሚሆንበትም ቁመና እንደሌላቸው አመላክተዋል።

ለሕዝብ እስከጠቀመ ድረስ የትኛውም ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪ ሲደረግ መቆየቱን አመልክተው፤ ሰላማዊ ሕይወትን መርጠው የመጡትንም የማቋቋም ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ጠንካራ አቅም እና ሕዝብ ያላት፣ እስከዛሬም ሉዓላዊነቷ አስጠብቃ የኖረች ሀገር ናት። የሀገሪቱ በዚህ ጥንካሬዋ መቀጠልና ከዚህ በፊትም ከነበረውም ሁኔታ እየተሻሻለች መቀጠል የሚያሳስባቸው ታሪካዊ ጠላቶች አሉ። ስለሆነም በተፈጥሮ ሀብቷ መጠቀም መጀመሯ፣ በሀገር በቀል እሳቤዎች የምትመራ ሀገር ወደመሆን መሸጋገሯ የሚያሳስባቸው ሀገራት አሉ።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ሀገራትን ተተናኩላ እንደማታውቅ ጠቁመው፤ የሚቃጡባትን ትንኮሳዎች መመለስን ግን ታውቅበታለች። ይህን ማድረግ ያልቻሉ አካላትም ያለውን የሚዲያ ዓውድ ተጠቅመው የመተንኮስ ፍላጎት እየታየ ነው ብለዋል።

የተገነባው ሠራዊት ግን በማንኛውም የተሳሳተ ስሌት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለመንካት የሚፈልጉ ኃይሎችን መመከት የሚችልበት ጠንካራ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You