
ችግሮችን በምክክር መፍታት ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ብቸኛው መንገድ መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፡- ችግሮችን በምክክር መፍታት ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ብቸኛው መንገድ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር መድረክን ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ ሚሊኒየም አዳራሽ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፉን ትናንት ሲያስጀምሩ እንዳሉት፤ ችግሮችን በምክክር አለመፍታት ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፤ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት ብቸኛው መንገድ ሀገራዊ ምክክር ነው ብለዋል።
ለችግሮቻችን መፈጠር መሠረት የሆኑ መንስኤዎችን በጋራ ተነጋግሮ መፈለግ ባለመቻሉ አለመግባባቶች ሳይፈቱ ዘመናትን መሻገራቸውን የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ፤ እነዚህን ችግሮቻችንን በምክክር ካልፈታን ሀገር የባሰ ፈተና ላይ እንደምትወድቅ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በርህራሄ እና መተሳሰብ የምትታወቅ ሀገር መሆኗን የጠቀሱት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለከፋ ችግር ተዳርገዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ዛሬ የተፈጠሩ ሳይሆኑ ዘመናትን አልፈው የመጡ ናቸው፡፡ የጋራ እሴቶቻችንን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች የመጡብን በንግግር ችግሮችን የመፍታት ልምድ ባለማዳበራችን ነው፡፡ የሃሳብ ልዩነቶቻችንን ቁጭ ብለን በመነጋገር መፍታት መቻል አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የታጠቁ አካላትና የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክር ሂደቱ አለመሳተፋቸው ኮሚሽኑን እንደሚያሳስበው አመላክተው፤ ኮሚሽኑ የምክክሩ ሂደት አካታች እንዲሆን እየሠራ ነው፡፡ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ እና በምክክሩ ያልተሳተፉ ኃይሎች ጭምር በጋራ ሃሳብ የጸና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የገጠሟን ችግሮች ለመፍታት ሕዝቡን በማሳተፍ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን ኮሚሽኑ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን አንስተዋል፡፡
ተሳታፊዎች ከድህነት እና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ እየታገለች ያለችውን ኢትዮጵያ በጸና ሰላም ላይ ለማቆም የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችሉ ገንቢ ሃሳቦችን እንዲያዋጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ እስካሁን ከ11 ክልሎች እና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች በድምሩ ከአንድ ሺህ 120 ቀበሌዎች የተሰበሰቡ 13 የአጀንዳ ሰነዶችን የማደራጀትና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ ተጠናቋል፡፡ ትናንት ከተጀመረው የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት አጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር መርሃ ግብር መካሄድ በኋላ በቀረው የትግራይ ክልልም አጀንዳ ማሰባሰብ ይካሄዳል ተብሏል፡፡
“ሀገራዊ ምክክር ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ መልዕክት ትናንት መካሄድ የጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በምክክር ሂደቱ የሲቪል ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መምህራን፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በአጠቃላይ ከ38 ተቋማት የተውጣጡ ከ850 በላይ ወኪሎች እየተሳተፉ ይገኛል፡፡
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን የሥራ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የስዕል ዐውደ ርዕይ ተከፍቶ በተሳታፊዎች ተጎብኝቷል፡፡
በተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም