
አዲስ አበባ፡- በግጭቱ የተፈጠሩ መጥፎ ስሜቶችን በመተው አብሮነትን የሚያጠናክር የወል ትርክትን መገንባት እንደሚገባ የፕሪቶሪያ የሰላም ንግግር ዋና ተደራዳሪዎች ገለጹ።
የፕሪቶሪያ የሰላም ንግግር ዋና ተደራዳሪዎች የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በግጭቱ ወቅት ሕዝቡ ኢትዮጵያን እንዲጠላ ለማድረግ በተሰራጩ የተዛቡ ትርክቶች መጥፎ ስሜቶች ተፈጥረዋል፡፡እነዚህን መጥፎ ስሜቶች በማከም አብሮነትን የሚያጠናክር የወል ትርክት መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንደገለጹት፤ አንዳንድ አካላት ኩርፊያቸውን የመነጠል ትርክትን በማቀንቀን ለመግለጽ ይሞክራሉ፡፡ እነዚህ አካላት መሬት ላይ ያላቸው ተቀባይነት ግን አነስተኛ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት በኢትዮጵያዊነት ማሕቀፍ ውስጥ ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥና በጋራ መልማት ነው ብለዋል፡፡
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመፈረሙ የሚቆጫቸው አካላት አሁንም ግጭት እንዲፈጠር ፍላጎት እንዳላቸው አንስተው፤ የፌዴራል መንግሥቱ በክልሉ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በማስፈጸም ረገድ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በሂደት እነዚህን ተግባራት ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎች መስተዋላቸውን አመልክተዋል።
መደማመጥና መነጋገር ቢቻል ኖሮ የደረሱ ጉዳቶችን ማስቀረት የሚቻልበት እድል እንደነበር ገልጸው፤ በተደረሰው ስምምነት ግጭቱን ማስቆም መቻሉም ትልቅ ውጤት ነው ብለዋል።
ትናንት ትክክል የነበረ ነገር በጊዜ ሂደት ዘመኑን የሚዋጅ ለውጥ ያስፈልገዋል ያሉት አምባሳደሩ፤ ሁልጊዜም ወቅቱን የሚመጥን ለውጥና ተግባር እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ የትግራይ ሕዝብ ለዘመናት ኢትዮጵያ ጠል ኃይሎች ሲነዛ በኖረው የመነጠል ትርክት ሳይደናገር ስለ ኢትዮጵያ የጸና አቋሙን በተግባር ማሳየቱንም አንስተዋል።
መሥራት ያለብን የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ተባብሮ ጥቅሙን ማስከበር እንዲችል መሆን እንዳለበት ያነሱት አቶ ጌታቸው፤ አኩራፊነትንም ሆነ ወደ ሌላ ግጭት የሚወስድን መንገድ መዝጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ችግሩን በድርድር ለመፍታት በሚደረገው ሂደት አንዳንድ አመራሮች የሰላም ድርድሩ እንዳይሳካ ሲጥሩ እንደነበር አንስተው፤ አንዱን አካል ጥፋተኛ ሌላውን ደግሞ ሀቀኛ በማስመሰል መግባባት እንዳይኖር ሲሠሩ እንደነበር አውስተዋል።ሆኖም ራሳችን አስቀድመን መወያየታችን ፕሪቶሪያ ላይ ልዩነታችንን ለመፍታት እና ወደ ስምምነት ለመምጣት አግዞናል ብለዋል።
በቀድሞው ሕወሓት በኩል የተለያየ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ስለነበሩ የምንነጋገርበትን እያንዳንዱን ነገር ይዘው ለሚዲያ ያቀርቡና በሌላ ይተረጎም እንደነበር ጠቅሰው፤ በእኛም በኩል ነገሮችን ከመንደርና ሰፈር ጋር ሰፍቶ በራሱ መንገድ የማየት ችግር ነበር። በኋላ ልዩነቶችን በማጥበብ ተስማምተን መቀጠል ችለናል ብለዋል።
በቀጣይነትም መሠራት ያለበት መግባባትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መሆን እንዳለበት አቶ ጌታቸው ጨምረው ገልጸዋል።
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም