ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን በዲፕሎማሲና በሰላማዊ መንገድ ለማሳካት እየሠራች ነው

አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያለው እንደመሆኑ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እየሠራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፍር በድሩ ገለጹ።

ይህም በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ መተሳሰብን ማጎልበት፣ የጋራ መግባባትን መፍጠር፣ ሰላም፣ ደህንነት እና ብልፅግና ለማሳደግ ያለመ ነው።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፍር በድሩ 3ኛው የቀይ ባሕርና የኤደን ባሕረ ሰላጤ የምክክር መድረክ ትናንት በአዲስ አበባ ሲካሄድ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ዓባይ ወንዝን እና ቀይ ባሕርን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮቿ አድርጋ ትመለከታለች። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ ያለው እንደመሆኑ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እየሠራች ትገኛለች ብለዋል።

ዓባይ እና ቀይ ባሕር የዲፕሎማሲና የጋራ መግባቢያ ቦታ እንጂ የግጭት መነሻ መሆን የለባቸውም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄም በዲፕሎማሲ እና ሉዓላዊነትን ያከበረ መሆኑን ተናግረዋል። ድንበር ተሻጋሪ ስጋቶች፣ ያልተፈቱ ግጭቶች እና ከፍተኛ የሥልጣን ሽኩቻዎች የቀይ ባሕርና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ እና ስምምነት ያለው ሀገራዊ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የምክክር መድረኩም ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር፣ እንደ የባሕር ላይ ወንበዴዎች ያሉ አሳሳቢ ጉዳዮችን ለመፍታት እንደሚረዳም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የጋራ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በትብብር እየሠራች መሆኗን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት እኤአ በ2030 በሥልጠና እና በምርምር አህጉራዊ መሪ ለመሆን እየሠራ ነው። ይህም ተግባራዊ ምርምር ማድረግ፣ የውጭ ፖሊሲ ተዋናዮችን ማብቃት እና በዲፕሎማሲ፣ በሰላም እና በዓለም አቀፍ ትብብር የልህቀት ማዕከል መሆንን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

የመከላከያ የትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕርና በኤደን ባሕረ ሰላጤ አንገብጋቢ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚያስችል ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ የባሕር ላይ ዝርፊያዎችን ጨምሮ ሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚኖራት አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑንም ጠቁመዋል። የእዚህ ትብብር ቁልፍ ትኩረት እንደ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ ፅንፈኝነት እና ሕገወጥ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች ያሉ የጋራ ስጋቶችን መዋጋት  እንደሚያስችል ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከባሕረ ሰላጤና ከቀይ ባሕር ሀገራት ያላት ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊ ብቻ ሳይሆን በጋራ እጣ ፈንታ የተሳሰረ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት እና ከባሕረ ሰላጤው ሀገራት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ በቀጣናው ሰላምን፣ ልማትን እና ብልፅግናን ለማስፈን በትጋት እየሠራች መሆኑን ገልጸው፤ ቀጣናው ካለመረጋጋት ይልቅ የብልፅግና ድልድይ እንዲሆን፤ ከመጋጨት ይልቅ ውይይትን እና አንድነትን አካባቢ እንዲሆን ሁሌም የተሻለውን መምረጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You