
አዲስ አበባ፡– የጤና ቁጥጥር ሚዲያ ፎረም መመስረት በጤና ተቋማት የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለማጋለጥና ለመከላከል ዕገዛ እንደሚያደርግ በአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ገለጸ፡፡
የባለስልጣኑ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ታደሰ የጤና ቁጥጥር ሚዲያ ፎረም መመስረትን አስመልክተው እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስተባባሪነት የጤና ቁጥጥር ሚዲያ ፎረም ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ለመጀመሪያ ጊዜ በኔክሰስ ሆቴል ተመስርቷል፡፡ ቀደም ሲል ከሚዲያ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ ፕሮግራሞችና መግለጫዎች ሲኖሩ ለሕዝብ ተደራሽ ሲሆኑ ቆይተዋል፡፡ ይህን ተግባር ከፍ ለማድረግና ለማሳደግ በማሰብ በባለስልጣኑ ማኔጅመንት የጤና ቁጥጥር ሚዲያ ፎረም ለመመስረት መወሰኑን አንስተዋል፡፡
ወይዘሮ ሙሉእመቤት፤ ባለስልጣኑ ምግብና መድኃኒት እንዲሁም ጤና ነክ አገልግሎት በአግባቡ ተጠብቆ ኅብረተሰቡ ጋር እንዲደርስ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ተግባሩን በኃላፊነት ለመወጣት የሚዲያ አካላት እገዛ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የግልም ሆነ የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የሥራ እንቅስቃሴ በጋዜጣ፣ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን በስፋት እያቀረቡ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያድግ ከማድረግ በተጨማሪ ሕገወጥ ተግባራትን የመከላከል ሥራ ሲሠሩ እንደነበረ ያስታወሱት ዋና ሥራ አስኪያጇ፤ ለእዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አሁን የተመሠረተው የጤና ቁጥጥር ሚዲያ ፎረም የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ሕገወጥነትን መከላከል እና ማጋለጥ የሚችል ማህበረሰብ ከመፍጠር በተጨማሪ ባለስልጣኑ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ዕገዛ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤አሁንም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን አጋዥ እንደሚሆን ከፍተኛ ዕምነት እንዳላቸው አሳስበዋል፡፡
የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ብርቄ ፤የፎረም ምስረታው ዋና ዓላማ፣ አስፈላጊነት፣ የተግባቦት ንድፈ ሃሳቦች እንዲሁም የጤና ተቆጣጣሪ ሚዲያ ፎረም ምስረታው የቀጣይ ስድስት ወራት ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በመቀጠል ባለስልጣኑ ከመሠረተው የሚዲያ ፎረም በጋራ ለመሥራት ካቀዳቸው እቅዶች ዋነኛ በሆነው የትምባሆና አደንዛዥ እጽ አጠቃቀም ላይ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም “በትምባሆ እና በኒኮቲን ምርቶች የትምባሆ ኢንዱስትሪ ድብቅና አሳሳች ስልቶች ማጋለጥ በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የዓለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀንን አስመልክቶ ለአንድ ወር በሚቆየው የንቅናቄ ሥራ ላይ የሚዲያ ፎረሙ ተሳትፎና ድርሻ በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል፡፡
ስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም