
አዲስ አበባ፡- የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ምርምሮችን እየሠራ መሆኑን የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ምርምሮቹ መሬት ላይ ወርደው የሕዝቡን ችግር መፍታት እንዲችሉ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አመልክቷል ።
የኢንስቲትቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ጸጋ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የሀገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው በተለዩ 52 የትኩረት መስኮች የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ።
የተቋሙ ኃላፊነት መረጃን መሠረት ያደረገ የምርምር ሥራዎችን መሥራት መሆኑን አመልክተው፤ የሚሠሩ የምርምር ሥራዎችም መሬት ላይ ወርደው የሕዝቡን ችግር መፍታት የሚችሉ እንዲሆኑም በትኩረት እንደሚሠራ አመልክተዋል ። የምርምር ሥራዎቹ በታላላቅ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ጭምር እየታተሙ እንደሆነም አስታውቀዋል።
ተቋሙ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ባቀረባቸው ምክረ-ሃሳቦች መሠረት በርካታ ተቋማት መቋቋማቸውን አስታውሰው፤ ለዚህም የኢትየጵያ ምርት ገበያ፣ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል ። ተቋሙም ከሰብሰሀራን አፍሪካ ሀገራት ዘጠነኛው አሰላሳይ ተቋም ተብሎ እውቅና እንደተሰጠውም ገልጸዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት 40 የሚደርሱ የሦስተኛ ዲግሪ ባለቤቶችን ጨምሮ 73 ተመራማሪዎችን ይዞ እየሠራ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገርና ብዙ ሕዝብ ያላት ሀገር ናት። ጥያቄዎቻችንና ፍላጎቶቻችንም በዛው ልክ ብዙ ሥራ የሚፈልጉ ናቸው። ከዚህ አንጻር ተቋሙ የሚጠበቅበት ሥራ ዘርፍ ብዙና ሰፊ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የምርምር ሥራ ከፍኛ ሀብት የሚጠይቅ ሥራ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ተቋሙ ምርምሮችን የሚያከናውነው አጋር ድርጅቶች እና መንግሥት ከሚበጅትለት ሀብት መሆኑን አመልክተዋል። ከአጋር ድርጅቶች የሚገኘው ሀብት እነሱ ባስቀመጡት አጀንዳ ላይ ተወዳድሮ የሚገኝ መሆኑ በቀጥታ እኛ ከምንፈልገው አጀንዳ ጋር ላይሄድ ይችላል፤ የምናከናውናቸው የጥናት ሥራዎች የእኛን ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እንዲሠሩ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
በሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት በርካታ ጥናትና ምርምሮች እንደሚያከናውኑ ያመለከቱት አቶ ፍቃዱ፤ መንግሥትም በየዓመቱ ከአጠቃላይ በጀቱ ዜሮ ነጥብ ሦስት በመቶውን ለምርምር ሥራዎች እንደሚመድብ አመልክተዋል ፤ ምርምሮቻችን ምን ያህል መሬት ላይ ያለውን ችግር ፈቺ ናቸው የሚለውን ማየት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ቻይናና ኮሪያን ጨምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገቡ ሀገራት የምርምር ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ሀገራቱ በእያንዳንዱ ዘርፍ የምርምር ተቋማት እንዳሏቸውም አመልክተዋል ።
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የሚሠሩ የምርምር ሥራዎች መሬት ላይ ወርደው የሕዝቡን ችግር መፍታት የሚችሉ ፤ የሀገሪቱን የእድገት ጉዞ የሚያፋጥኑ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑንም አቶ ፍቃዱ አስታውቀዋል።
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም