
አዲስ አበባ፡– አምራች ኢንዱስትሪው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም የህልውና ጉዳይ አድርገው ሊውስዱ እንደሚገባ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
በኢንስቲትዩት የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ፤ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ እና ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀድጉ ኃይለኪሮስ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት ፤ በዘርፉ ካሉ ተግዳሮቶች አንዱ፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም የህልውና ጉዳይ አድርገው አለመውሰዳቸው ነው፡፡
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘንድ አዳዲስ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም አለመፈለግ፤ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መጠቀም ከፍተኛ ወጪ ያስወጣል የሚል እሳቤ መኖር ፤ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙት ማሽኖች ጊዜ ያለፈባቸው ፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ለመጠቀም አስቸጋሪ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እንዱስትሪዎቹ አልተረዱትም እንጂ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አለመጠቀማቸው ምርታማነትን እና ጥራት በመቀነስ የበለጠ ለወጪ ይዳርጋቸዋል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በጊዜ ሂደት ከገበያ የመውጣት ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አመልክተዋል ፡፡
እንደ አጠቃላይ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም አለመፈለግ፤ የግንዛቤ ችግር እና ቴክኖሎጂን በቀላሉ የሚላመድ የሰው ኃይል፤ ማለትም የክህሎት ክፍተት እንደ ተግዳሮት የሚነሳ ነው፤ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ተቋሙ የግንዛቤ እና ሌሎች ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኢንዱስትሪውን አቅም ለማሳደግ እንደ ሀገር ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ አርቲፌሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መቋቋም፤ የተለያዩ ፖሊሲዎች መቀረጻቸው እና በጠቅላይ ሚንስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኩል እየተተገበሩ ያሉ መርሃ ግብሮች እንደ እድል የሚወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ሚንስቴር በኩልም የክህሎት ክፍተቱን ለመሙላት የትምህርት ፍኖተ ካርታ የመከለስ እና አዳዲስ ፖሊሲዎች እየተቀረጹ መሆናቸው ተስፋ ሰጪ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ሀድጉ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት ፤ ኢንስቲትዩቱ በመጀመሪያ የኢንዱስትሪዎች ችግር ምንድነው የሚለውን በመለየት፤ ስትራቴጂዎችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ነው ፤ በዚህም በቀዳሚነት የተቀረጸው የአቅም ግንባታ ስትራቴጂ ነው ፤ በዚህም ያለውን ችግር ለመፍታት ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የኢንዱስትሪ ትስስር መኖሩን በመግለጽ፤ ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ዘጠኝ የምርምር ወረቀቶች እየተሠሩ ነው፡፡ በዘርፉ ያለውን ችግር ተቋሙ ብቻውን የሚፈታው ስላልሆነ በቀጣይ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር እንደሚሠሩ አስታውቀዋል ፡፡
አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ቴክኖሎጂ በመጠቀም በጣም በፍጥነት ወደፊት ሊሄዱ ችለዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እንደ ኮዳክ የፊልም ኢንዱስትሪ የመሳሰሉ በርካታ ካምፓኒዎች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ባለማዘመናቸው በርካታ ሠራተኞቻቸውን በትነው ከገበያ ውጪ መሆናቸውን አመልክተዋል ፡፡
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም