የባለተሰጥኦዎቹ ወጣቶች-ችግር ፈቺ ፈጠራዎች

ከውሃ መያዣ ፕላስቲክ ጥጥ ማምረት ተቻለ ሲባል ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚሰማ ሰው ግር ሊል ይችላል። ነገር ግን የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ተማሪ የሆነው አማረ አባይነህ ከውሃ ፕላስቲኮች ትራሶችን ፣ አሻንጉሊቶችን እና አንዳንድ ለብርድ የሚሆኑ ኮቶች ግብዓት የሚሆን ጥጥ ማምረት የሚያስችል ማሽን መፍጠር ችሏል፡፡

ተማሪው እንደሚናገረው ፤ ማሽኑ ከውጭ ሀገራት የሚገባውን ሰው ሠራሽ ጥጥ የሚያመርት ማሽን ነው። የሚመረተው ጥጥ አሻንጉሊቶችን ፤ ትራሶችን እና የኮምፈርት ልብሶችን ለመሥራት ያገለግላል፡፡

ማሽኑን ለመሥራት የተለያዩ ጉዳዮች እንዳነሳሱት የሚናገረው ተማሪ አማረ፤ ከእነዚህም አንዱ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች እንደመሆኑ በየመንገዱ የሚጣሉ የውሃ ፕላስቲኮች የከተማን ውበት ማበላሸታቸው ነው፤ ከዚህ አኳያም ማሽኑ የተሠራው ፕላስቲኮቹን መልሶ ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር መሆኑን ያስረዳል፡፡

ከሥራ ፈጠራ ረገድ በሁለት መንገድ የሥራ እድል ይፈጥራል። የመጀመሪያ የውሃ ፕላስቲክ ለቅመው ለሚሸጡ ሲሆን፤ ሌላው ጥጡን አምርተው ለሚሸጡ አካላት የሥራ እድል መፍጠር ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሀገሪቱ ይህን ጥጥ የምታስገባው ከውጭ ሀገራት በዶላር ገዝታ እንደመሆኑ የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት አንጻር መሆኑን ይናገራል።

አሁን ላይ ማሽኑ ማምረት የጀመረ ሲሆን ጥጡን በመጠቀም በትምህርት ቤት ደረጃ የተለያዩ አሻንጉሊቶች እና ትራሶች እየተሠሩ ነው። በቀጣይም ማሽኑ በስፋት እንዲያመርት መጠኑን በማሳደግ ለተለያዩ ድርጅቶች የማስተላለፍ እቅድ እንዳለው በመግለጽ፤ በሥራው ሂደት ድጋፍ ላደረጉለት መምህራን እና ጓደኞቹ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

“እኔ ይህን እድል ያገኘሁት የኮሌጅ ተማሪ ስለሆንኩ ነው። ነገር ግን በየመንደሩ እና በየሰፈሩ የተለያየ የፈጠራ ሃሳቦች ያሏቸው ልጆች አሉ። ስለዚህ እነዚህ ልጆች የራሳቸውን ፈጠራ አውጥተው የሚያሳዩበት እድል ቢመቻች መልካም ነው፡፡” ሲል ምክሩን ያስተላልፋል፡፡

የቴክኖሎጂው ዘርፍ እንደ ሀገር ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ቴክኖሎጂን በሁሉም ዘርፍ አካቶ ለመጠቀም በሚደረገው ጥረት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ትልቁን ድርሻ የሚወስድ መሆኑ ታምኖበት በዘርፉ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል፡፡

ከዚህ አንጻር የሥራና ክህሎት ሚንስቴር በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ መርሃ-ግብሮችን ቀርጾ እየሠራ እንደሆነ በተለያዩ መድረኮች ይገልጻል። የመርሃ-ግብሩ አካል የሆነው አራተኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር ከሚያዚያ 27 እስከ ግንቦት 02/2017 ዓ.ም ሲካሄድ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

በዝግጅቱ ላይም ከተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሥራ ፈጣሪዎች የፈጠራ ሥራቸውን አምጥተው ለእይታ አቅርበዋል። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ከእነዚህ ባለፈጠራዎች ጋር ቆይታ አድርጓል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ደግሞ ተማሪ ዓለምነው መላኩ የሚባል ሲሆን፤ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪ ነው። የሠራውም የፈጠራ ሥራ በፀሀይ ኃይል የሚሠራ ዲጂታል የውሃ ማጠጫ ጄኔሬተር ነው፡፡

የውሃ ጀኔሬተሩ የፀሀይ ኃይል በመጠቀም አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፤ በሁለት አይነት መንገድ መቆጣጠር ያስችላል። የመጀመሪያው ጄኔሬተሩ ሴንሰር የተገጠመለት ስለሆነ የአፈሩን ድርቀት በመለየት እራሱ ከፍቶ ያጠጣል። እርጥበታማ አፈር ላይ ሲደርስ እራሱ ይዘጋል ሲል ያስረዳል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መቆጣጠር የሚያስችል ሶፍትዌር የለማ ሲሆን፤ በተለይ በረሃማ አካባቢዎች ላይ ውሃ ማጠጣት ሲያስፈልግ ውሃ ካለበት አካባቢ በመሳብ ደረቃማ አካባቢ ላይ ማጠጣት እንዲችል ቀርቦ መክፈት መዝጋት ሳያስፈልግ ባሉበት ቦታ ለመቆጣጠር ያስችላል ሲል ይገልጻል፡፡

በአካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ወደ መስኖ ሥራ እንዳይገቡ ትልቁ ተግዳሮት የነዳጅ ዋጋ መወደድ እና በቀላሉ አለመገኘት መሆኑን የሚገልጸው ተማሪ ዓለምነህ፤ የውሃ ጄኔሬተሩ በፀሀይ እና በመብራት ኃይል የሚሠራ መሆኑ ይህን ችግር የሚቀርፍ እና ሥራን የሚያቀል መሆኑን ይጠቁማል፡፡

ሌላው በነዳጅ የሚሠራ የውሃ ጄኔሬተር አገልግሎት ላይ ሲውል በጭስ መልክ የሚወጣው ካርቦንሞኖኦክሳይድ ለሰብሎቹ ተጽእኖ አለው። ከዚህ አንጻር ሲታይ የፀሀይ ኃይል መጠቀም የተሻለ አማራጭ መሆኑን በመጠቆም፤ ለግብርና፤ ለሆቴሎች፤ ለድርጅቶች እና ለትላልቅ ህንጻዎች እንዲውል በቀጣይ በተለያየ መጠን የመሥራት ሃሳብ እንዳለው ይገልጻል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ውሃ ሲቀዳ በሮቶ ከተደቀነ በኋላ ስለሚረሳ የውሃ ብክነት ያጋጥማል። በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዴ ውሃ ሲመጣ መቅዳት ይረሳና የመቸገር ሁኔታ ይኖራል። ይህን ችግር ከመቆጣጠር አንጻር በድሬዳዋ ከተማ ዳዋ ኤሌክትሮኒክስ ማኑፋክቸሪንግ የሚሠራው ወጣት ካሳዬ ሌኩን መላ እንዳለው ይናገራል፡፡

ወጣቱ የፈጠረው አውቶማቲክ የውሃ መቆጣጠሪያ ሲሆን፤ በተለያዩ ቢላ ቤቶች፤ አፓርታማዎች፤ ንግድ ቤቶች እና ድርጅቶች ላይ ባሉት ትላልቅ የውሃ ማጠራቀሚያ ሮቶዎች ላይ ይገጠምና የውሃ መጠን የቱጋር እንዳለ ያሳያል፤ ውሃ ሲያልቅ እራሱ በመክፈት ይቀዳል፤ ሲሞላ ደግሞ በራሱ የሚዘጋ መሣሪያ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ጊቢ ውስጥ ሶስት አፓርታማዎች ቢኖሩ ለሶስቱም ሶስት የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ከመግዛት ይልቅ ሶስቱንም በአንድ ፓምፕ ብቻ መስመሮቹን በማስተሳሰር መጠቀም እንደሚያስችል በመግለጽ፤ በሶስቱም ሮቶዎች ላይ የውሃ መቆጣጠሪያውን በመግጠም አንዱ ሲሞላ ዘግቶ ሌላኛውን ስለሚቀዳ ያለተጨማሪ ፓምፕ መጠቀም ይቻላል ሲል ያስረዳል፡፡

ውሃ ሲመጣ ሮቶ ይደቀንና ይረሳል፤ ሌላው ደግሞ በመጣ ጊዜ ሳይቀዳ ይረሳና የውሃ ችግር ያጋጥማል። ለምሳሌ አንዳንድ ሆቴሎች ላይ የእጅ መታጠቢያ ውሃ ሲጠፋ ይስተዋላል ይህም ውሃውን የሚቆጣጠረው ሰው ስለሆነ ስለሚረሳ ነው የሚለው ካሳዬ፤ ለፈጠራ ሥራ ያነሳሳው እነዚህን ችግሮች ማስተዋሉ እንደሆነም ይናገራል፡፡

ፈጠራው በዋናነት ውሃ አለቀ የሚል ስጋት እንዳይኖር በራሱ ከፍቶ ይሞላል፤ በተለይ ደግሞ የውሃ ማጠራቀሚያ ጣራ ላይ ከተሰቀለ ወደ ጣራ መውጣት ሳይጠበቅ ባሉበት የውሃ መጠኑን ማየት ያስችላል። አሁን እቃውን በስፋት ወደ ገበያ ለማስገባት እንዲያስችል የቧንቧ ባለሙያዎችን የማስተዋወቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You