
ዘመኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አብዮት ዘመን ነው። አብዮቱ ይዞት ከመጣው ትሩፋት ተጠቃሚ ለመሆን አሁን ላይ ግለሰቦች ፣ ተቋማት፣ ሀገራት እና መንግሥታት በስፋት እና በፍጥነት እየተንቀሳቀሱ ነው። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ስኬት የዓለምን ገጽታ በብዙ መልኩ እየቀየረው ይገኛል።
ሀገራችን ኢትዮጵያም ባላት አቅምና መልካም አጋጣሚ ሁሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አብዮት ተጠቃሚ ለመሆን የተቻላትን ሁሉ እያደረገች ነው ፤ በዚህም እያስመዘገበችው ያለው ውጤት ብዙዎችን እያስገረመ ፤ ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ መድረኮች እያደመቀም ይገኛል።
ከትናንት በስቲያ 1 ሺህ 500 ድሮኖችን በኢትዮጵያ ሰማይ ስር በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ አየር ላይ የማብረር ትዕይንት አሳይተዋል። ትርኢቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ትልቅ አቅም የገነባ እንደሆነም ብዙዎች በመገረም እና በመደነቅ እየመሰከሩ ነው ። የነገይቱ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ተስፋ ማሳያ አድርገው እየወሰዱ ያሉም ብዙዎች ናቸው ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም