“ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በዲጂታል መሠረተ ልማት አርአያ እየሆነች ነው” – ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት እና በክሕሎት ማበልጸጊያ ሥራዎች አርአያ እየሆነች መምጣቷን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ “አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ለአፍሪካ ብልፅግና እና ትብብር” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለአፍሪካ መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዲጂታል መሠረተ ልማት እና በክሕሎት ማበልጸጊያ ሥራዎች ግምባር ቀደም ሀገር እየሆነች መጥታለች። በኢትዮጵያ የተጀመሩ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ ዲጂታል መታወቂያ እንዲሁም የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና የኢትዮጵያን የዲጂታል ሕልሞች ወደ ተጨባጭ ለውጥ የሚቀይሩ ናቸው ብለዋል።

አፍሪካ በሀገር በቀል የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የተመራ አካታች ብልፅግና በማምጣት የአጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት እየሠራች መሆኑን አመልክተው፤ አፍሪካ በ2030 አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በሥነ ምግባርና በአካታችነት መርሕ በአህጉራዊ መልክ ልትገነባ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ለዜጎች ሕይወት መሻሻል ፣ ለተቋማት መለወጥና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ሞተር መሆኑን ገልጸዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ማቋቋሟ ታሪካዊ ርምጃ መሆኑን አውስተው፤ የቴክኖሎጂ አቅምና አጠቃቀምን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኗንና በተሠራው ሥራም አብዛኛው ሕዝብ በተመጣጣኝ ዋጋ የብሮድባንድ እና የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ሁሉም ሴክተሮች አገልግሎታቸውን ለማዘመንና የሰው ልጆችን ሕይወት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ለጤና ለትምህርት፣ ለግብርናና ለሌሎች ሴክተሮች ዕድገትና ተደራሽነት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው የገለጹት።

ባለፉት አምስት ዓመታት የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ፣ በማስተዳደር እና ጥበቃ በማድረግ የቴክኖሎጂውን ሥነ-ምህዳር ለማስፋፋት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸው ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑን አመልክተዋል።

ዲጂታል ማህበረሰብ በመገንባት ረገድም ኢትዮጵያ የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢንሼቲቭ ቀርጻ ወደ ተግባር መግባቷን አውስተው ፤ በዚህም እስካሁን አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የኮደርስ ስልጠና ወስደዋል፤ አሁንም ዜጎች የዲጂታል እውቀት ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ረገድም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል። ከ 15 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን እና ነዋሪዎቿ የዲጂታል መታወቂያ መያዛቸውን እንዲሁም ክፍያዎችን ከጥሬ ገንዘብ ወደ ዲጂታል መቀየር መቻሉን አንስተዋል።

አብዛኛው የመንግሥት ተቋማት አገልግሎታቸው ዲጂታል እንዲሆን መደረጉን ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸው፤ በቅርቡ በተመረቀው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 12 ተቋማት 41 አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ስር ለሕዝብ እየሰጡ ነው ብለዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የዲጅታል የክፍያ አማራጮችን ማስፋፋትን ጨምሮ ድጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በቀጣይም በ2030 የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ትራንስፎርሜሽን እውን በማድረግ በቴክኖሎጂ የበለጸገች ሀገር እንድትሆን በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት። የቴክኖሎጂ አካታችነትን ለማሳደግ በትብብር መሥራት እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

‹‹የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ETEX-2025›› ከግንቦት 8 እስከ 10 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል።

ጌትነት ምህረቴ

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You