
-በአንድ አካባቢ አጥፍተው በሌላ አካባቢ ንጹህ ሆኖ መገኘት ያበቃል
አዲስ አበባ፦ አሽከርካሪዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ መቆጣጠር የሚያስችል ዲጂታል ሥርዓት ይፋ ሆነ። አሽከርካሪዎች አንድ አካባቢ አጥፍተው በሌላ አካባቢ አጥፊ እንዳልሆኑ የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚያበቃ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችሉ ሶስት የዲጂታል ሶሉሽኖች ይፋ በሆኑበት ወቅት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚንስቴር ሚንስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ የለማው የዲጂታል ሶሉሽን አሽከርካሪዎች አንድ አካባቢ አጥፍተው በሌላ አካባቢ አጥፊ እንዳልሆኑ የሚኖሩበት ጊዜ እንዲበቃ የሚያደርግ ነው።
ሚንስትሩ ትራንስፖርት የማይገባበት የሕይወት መስክ የለም፤ ሥራዎችን በተገቢው ፍጥነት ለመተግበር፣ ሥራ እና ሠራተኛን ለማገናኘት ሻጭ እና ገዥን ለማስተሳሰር ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ዘርፍ ማሳደግ እና ማዘመን ብልፅግናን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
ሚንስትሩ መንግሥትም ለትራንስፖርት ዘርፍ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ፖሊሲዎችን ማፅደቁን፤ የአምስት እና የ10 ዓመት እቅዶች በመንደፍ ወደ ሥራ መግባቱንም አስታውሰዋል።
የዲጂታል ሶሉሽኑ ሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሥርዓትን በማዘመን ዜጎች በየመናኸሪያው የሚደርስባቸውን እንግልት የሚቀንስ፤ ቅልጥፍና እና ደህንነትን የሚያረጋግጥ አገልግሎት ለመስጠት ይረዳል ብለዋል።
የተቀናጀ ነዳጅ አቅርቦት ሥርዓት በማሻሻል የነዳጅ ሻጮችን እና ገዥዎችን እንቅስቃሴ ያዘምናል። እንዲሁም የሀገር አቀፍ የትራፊክ ቅጣት ማዕከላዊ አስተዳደር ሥርዓት የመንገድ ደህንነት ችግር የሚፈጥሩ አሽከርካሪዎች የት አካባቢ እንደሚኖሩ፣ እድሜያቸው ፣ ፆታቸው፣ የአሽከርካሪዎች ሥልጠና የወሰዱት ማዕከል እና ሌሎች መረጃዎችን በመያዝ በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ አጥፊዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል። ይኸውም ከመንገድ አደጋ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሚረዳ ይሆናልም ብለዋል።
የዲጂታል ሶሉሽኖቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ በሕዝብ እንግልት ሲያተርፉ የነበሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ተግዳሮት ሊሆኑ እንደሚችሉ የጠቆሙት ሚንስትሩ፤ በክልሎች ያሉ አመራሮች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ለአፈጻጸሙ ቁርጠኝነት ሊያሳዩ እንደሚገባ ተናግረዋል። ያለአግባብ ሕዝቡን ሲዘርፉ የኖሩ ሰዎችም ጥቅማቸውን የሚነካ በመሆኑ በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በቀጣይም ሌሎች ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እንደሚሠሩም አስታውቋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ ሥርዓቶቹ እንደ ሀገር የዲጂታል ጉዞን ለማሳለጥ እና የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል ይረዳል ብለዋል። ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅም መገንባቱን ገልጸው፤ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
ንግድ እንዲዘምን በማድረግ የዋጋ ንረትን ማስተካከል ይቻላል። ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሥራን በማዘመን ኢኮኖሚን ማረጋጋት ይቻላል። ትራንስፖርት በእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ውስጥ በየእለቱ ይገባል። የዜጋው ሰአት እና ጊዜ ለምርት እና ምርታማነት አይተኬ ሚና አለው፤ በዚህም ዘርፉን ማዘመን ወሳኝ ነው ብለዋል።
የአመራር ቁርጠኝነት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ አሁን እየተኬደበት ባለው ፍጥነትም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ እቅድ የሚሳካ እንደሚሆንም ገልፀዋል።
የዲጂታል ሶሉሽዩን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚንስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ በመሆን ያበለጸጉት መሆኑ በእለቱ ተገልጿል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 7 ቀን 2017 ዓ.ም