
አዲስ አበባ፡- አዲስ አበባን ለወንጀለኞች የማትመች ከተማ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ገለጸ።
የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚዴቅሳ ከበደ በቢሮው የ9ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ የኮሪዶር ልማት ሥራዎች ለሰላም እና ፀጥታ ሥራው ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ከዚህ በፊት ጨለማ የነበሩ ቦታዎች መብራት እንዲገባባቸው በማድረግ ለወንጀለኞች የማይመቹ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል። አዲስ አበባን ለወንጀለኞች የማትመች ከተማ ለማድረግ በተሠሩ ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
አቶ ሚዴቅሳ የኢኮኖሚ አሻጥር በማድረግ የኢኮኖሚ ግሽበት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን ገልፀው፤ ወንጀልን ለመዋጋት ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን እየተሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል። የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።
ትምህርት ቤቶች ትውልድ የሚገነባባቸው ናቸው። እነዚህን የትውልድ ማፍሪያ ስፍራዎች የሚያውኩ ግለሰቦችን እና ተቋማት ላይ ርምጃ መወሰዱንም ገልጸዋል።
የ9 ወራት ሪፖርቱን ለተሳታፊዎች ያቀረቡት አቶ ገብሬ ዳኛቸው በበኩላቸው፤ ባለፉት 9 ወራት የኢኮኖሚ አሻጥር ችግሮች በፈጠሩ እና የኑሮ ውድነት መባባስ ምክንያት በሆኑ ከ6 ሺህ 700 በላይ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱን ገልጸው፤ ያለ ሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ግብይት ሲፈፅሙ በተገኙ አንድ ሺህ 657 ነጋዴዎች ላይ በተመሳሳይ ርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።
የጨለማ ቦታዎች ተገን ተደርጎ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል በ242 ሺህ 179 ቦታዎች ላይ መብራት እንዲገባ ተደርጓል። በቀጣይም በ723 ሺህ ቦታዎች ላይ መብራት እንዲገባ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ በከተማዋ አደባባይ እና የመንገድ ላይ የድምፅ ብክለቶችን ለመቀነስ ተችሏል። በዚህም ሁለት ሺህ 271 የድምፅ ብክለት መንስኤዎች እንዲፈቱ ተደርጓል ብለዋል።
እንደ አቶ ገብሬ ገለጻ፤ የጫኝ እና አውራጅ የዋጋ ተመን ተስተካክሏል ፣ አንድ ሺህ 238 አዋኪ ድርጊት ፈፃሚዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል። ታርጋ ሳያወጡ ባጃጅ የሚያሽከረክሩ ግለሰቦች ሕጋዊ መስመር እንዲይዙ ተደርጓል፤ የቅጥር ጥበቃ አገልግሎት ላይ የሚነሱ ችግሮች ለመፍታት ተሠርቷል።
በ9 ወራት የሥራ ሂደት ላይ ካሉ ጉዳዮች ተራ አስከባሪዎች ላይ የሚነሱ ትርፍ መጫን፤ ታሪፍ መጨመር ፣ ተራ ጠብቆ እንዲሳፈር አለማድረግ ችግሮችን ለመከላከል በ84 ተርሚናሎች 959 አባላት በማደራጀት ችግሩን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በቢሮው አደረጃጀት ውስጥ ያሉ አምስት አመራሮች እና ሁለት ባለሙያዎች ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ እንደተወሰደባቸው የገለፁት አቶ ገብሬ፤ ከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማወያየት ግንዛቤ መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል።
ቢሮው የሚሠራቸውን ሥራዎች በቴክኖሎጂ ለማዘመን እጅግ በጣም ዘመናዊ የሆነና የተራቀቀ ቴክኖሎጂ አልምቶ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸው፤ በቢሮው በተደረገ የርካታ ዳሰሳ በቢሮው ውስጥ 87 በመቶ በማህበረሰቡ 92 በመቶ ርካታ መፍጠር መቻሉንም ተናግሯል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም