ክልሉ በዘጠኝ ወራት 4ሺህ 254 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ አደረገ

-በማዕድን ዘርፍ ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል

አዲስ አበባ፡– በጋምቤላ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት 4ሺህ 254 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት አስታወቀ፡፡በማዕድን ዘርፉም ለ6 ሺህ 50 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩ ተገልጿል፡፡

የጋምቤላ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡጁሉ ጊሎ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት አንድ ሺህ 850 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ታቅዶ፤ 4ሺህ 254 ኪሎ ግራም ወርቅ ገቢ ማድረግ ተችሏል፡፡

ለብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን ከፍተኛ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ማድረጉ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተጨማሪም በክልሉ በአንጻራዊነት ሰላምና ጸጥታ መረጋጋት መኖሩና ከፌዴራል ጸጥታ አካላት ጋር የተቀናጀ ክትትል መደረጉ፤ እንዲሁም የወርቅ አምራቾች በተሻለ አቅም ማምረት መቻላቸው ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ከፍተኛ እንዲሆን አድርጓል ብለዋል፡፡

በክልሉ የወርቅ ልማት ትኩረት ተሰጥቶት ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ በእዚህም መሻሻሎች በመምጣታቸው ለውጦችና ውጤቶች መመዝገብ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

በክልሉ በአብዛኛው ወርቅ በባሕላዊ መንገድ በልዩ አነስተኛ ማህበራት እንደሚመረት የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ወርቅ ለማምረት ፍቃድ ወስደው በሕጋዊ መንገድ ወርቅ እያመረቱ ያሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ፍቃድ ሳይኖራቸው በተለምዶ ወደ ወርቅ ማምረት ሥራ ገብተው እየሠሩ ያሉ መኖራቸውም ይጠቁመዋል፡፡

እነዚህ ሕጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው ወደ ሥራ የገቡ አካላት ሕገወጥ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ገልጸው፤ ፍቃድ አውጥተው ሕጋዊነት ተከትለው ወርቅን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ የማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

በክልሉ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት አለባቸው ተብለው የተለዩት ወረዳዎች ጋምቤላ ፣ አቦቦ፣ መንገሺና ዲማ ናቸው ያሉት አቶ ኡጁሉ፤ በወረዳዎቹ በርካታ በባሕላዊ መንገድ ወርቅ የሚያመርቱ አምራቾች ያሉባቸው በመሆኑ ወርቅም በብዛት እየተመረተ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ ወርቅ ለማምረት ከተቋቋሙት የወርቅ ፋብሪካዎች መካከል ኢትኖ ማይኒንግ ዋነኛ ተጠቃሽ መሆኑን የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትኖ ማይኒንግ የወርቅ አምራች ኩባንያ በከፍተኛ ደረጃ ወርቅ ለማምረት ግንባታው ተጠናቅቆ በተያዘው በጀት ዓመት በህዳር ወር ተመርቆ ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

ሥራ ከጀመረ በኋላ 12 ኪሎ ግራም ወርቅ ማስገባቱን ለክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ማሳወቁን ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ በክልሉ በርካታ ወርቅን ጨምሮ አሸዋ፣ የኖራ ድንጋይ፣ ግራናይትን የመሳሰሉ ለኮንስትራክሽንና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ሌሎች በርካታ ማዕድናት ይገኙበታል፡፡ማዕድናቱን ለማልማት ፍቃድ ወስደው የተሠማሩ አካላት በርካታ ቁጥር ያላቸው አምራቾች አሉ፡፡በእነዚህ ማዕድናት የማልማቱ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በክልሉ በዘጠኝ ወራት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በማዕድን ዘርፍ በኮንስትራክሽን ግብዓትነት የሚውሉ ማዕድናትና በወርቅ ምርትና ግብይት ለ5ሺ 760 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ታቅዶ፤ ለ6 ሺህ 050 ዜጎች (ለ677 በቋሚነት እና ለ5 ሺህ 372 በጊዜያዊነት) የሥራ እድል ተፈጥሯል፡፡ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከል 21 በመቶ ሴቶች እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You