በ105 የመድኃኒት ችርቻሮ ድርጅቶች ላይ ርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባደረገው የቁጥጥር ተግባራት በ105 የመድኃኒት ችርቻሮ ድርጅቶች ላይ የእርምት ርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ የቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ እንጋ እርቀታ ባለሥልጣኑ ከመድኃኒት ችርቻሮ ባለሀብቶች ጋር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት ባደረገበት ወቅት እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ አንድ ሺህ 663 የመድኃኒት ችርቻሮ ድርጅቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ በተደረገው የቁጥጥር ተግባራት 74 የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፣ 30ዎቹ ታግደዋል (ታሽገዋል)። እንዲሁም አንድ የሙያ ፈቃዱን በመሰረዝ ዘርፍ እንዲቀይር ተደርጓል ብለዋል።

በቁጥጥር ወቅት የተገኙትን ግኝቶች ሲጠቅሱ ደግሞ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች ይዞ መገኘት፣ ያለማዘዣ ወረቀት መድኃኒት መሸጥ፣ አንዳንድ ተቋማቶች መድኃኒት አያያዝና አከማቸታቸው በስታንዳርድ መሠረት አለመሆን፣ የጤና ባለሙያ ያልሆኑ መድኃኒት ሲሸጡ መገኘታቸው/ ረዳት ባለሙያ አለመኖር፣ ምንጩ ያልታወቀ(Invoice) መድኃኒት ይዞ መገኘት፣ ለአካል ጉዳተኛ ምቹ ያልሆኑ ተቋማቶች መኖራቸው፣ ባለላይሰንስ (የሙያ ሥራ ፈቃድ ባለሙያ) በቁጥጥር ወቅት በሥራ ገበታ አለመገኘት፣ አንዳንድ ተቋማቶች የቁጥጥር ሥራን ለማደናቀፍ ሙከራ ማድረጋቸው እንዲሁም በተቋሙ የተለያዩ ማኑዋሎች የተሟሉ አለመሆናቸውን አንስተዋል።

አያይዘውም በ2017 በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተወገዱ ጊዜ ያለፈባቸውና የተበላሹ መድኃኒቶች 23 ሺህ 515 ኪሎ ግራም መሆናቸውን አመልክተው፤ ይህም በገንዘብ ሲተመን 51 ሚሊዮን 348 ሺህ 613 ብር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ ባለስልጣኑ በዘጠኝ ወራት ያከናወናቸው ዕቅድ አፈጻጸሞች ቀርበው ግምገማ የተካሄደባቸው ሲሆን፣ የመድኃኒት ችርቻሮ ባለሀብቶችም አሉ የሚሏቸውን ተግዳሮቶችና ለአሠራር ማነቆ የሆኑ አሠራሮች እንዲሁም መመሪያዎችን አንስተው ምላሽ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

የባለሥልጣኑ ኃላፊዎችም በአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ደረጃ የሚፈቱትን ባለሥልጣኑ ለመፍታት የሚሠራ መሆኑን አንስተው፣ ከባለሥልጣኑ ወሰን በላይ የሆኑትን ደግሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር በቀጣይ ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You