በ10 ዓመት 2ሺ 500 አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክስ ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- በቀጣይ 10 ዓመት ለዜጎች ከሁለት ሺህ 500 በላይ አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ከግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የኢ- አገልግሎት (e- service) መስጠት እንደሚጀምር በትናንትናው እለት ይፋ አድርጓል።

በወቅቱ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሚራጅ ዘኪይ እንደገለጹት፤ እንደ ሀገር ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ በመንደፍ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይቷል።

አሁን ላይ ዲጂታል 2030 ለማሳካት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን በማንሳት፤ ስትራቴጂው ላይ ከተጠቀሱ ጉዳዮች ዋነኛው መንግሥት እና ዜጎች የሚያደርጉት የዲጂታል ግንኙነት እንዴት መሆን እንዳለበት በስፋት የሚገልጽ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

ወይዘሮ ሚራጂ እንደተናገሩት፤ ዜጎች አገልግሎቶችን ቀልጣፋ እና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ ማድረግ አንደኛው የዲጂታል ኢትዮጵያ ግብ ሆኖ ቆይቷል። ከእዚህ አንጻር አሁን ላይ እንደ ሀገር ከአንድ ሺህ በላይ አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ እየተሰጠ ሲሆን፤ በተያዘው የ10 ዓመት እቅድ ወደ 2ሺ 500 ለማሳደግ ታስቧል።

ኅብረተሰቡ በተቋማዊ ቢሮክራሲዎች ሳይንገላት አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ሀገር አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ተከፍቶ ወደ ሥራ ከተገባ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑንና ባለፉት ሦስት ወራት ድረ ገጹን የማሻሻል ሥራ መሠራቱን አንስተዋል።

የፈጠራ ሃሳቦችን ለማሳደግ መንግሥት ከያዘው አቅጣጫ አንጻር ባለሥልጣኑ የሚያከናውናቸው ተግባራት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፤ ተቋሙ ሀገር አቀፍ እንደመሆኑ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተደራሽነትን ያሰፋል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሉ ሞሲሳ በበኩላቸው፤ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በዋናነት ሦስት አገልግሎቶችን ለዜጎች የሚሰጥ እንደሆነ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ከሦስቱ አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ መንገድ አገልግሎት መስጠት የተጀመረው በንግድ ምልክት ምዝገባ እና ቅጂና ተዛማጅ መብቶች ላይ ነው ብለዋል።

አገልግሎቶቹን ከኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቱ ጋር ለማጣጣም ረጅም ጊዜ በመውሰዱ እስከ አሁን ሳይጀመር መቆየቱን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከእዚህ በፊት ዜጎች አገልግሎቱን የሚያገኙት ወደ ተቋሙ መጥተው ስለነበር ከተደራሽነት አንጻር ውስንነቶች በመኖራቸው የሚፈለገውን የንግድ ሥርዓት ጥበቃ ወደ ሥርዓት ለማስገባት አልተቻለም ሲሉ ተናግረዋል።

ተገልጋዮች በአካል በሚመጡበት ወቅት በወረፋ ምክንያት መንገላታት እንደሚያጋጥማቸው እና አለፍ ሲልም መረጃ የሚተላለፈው በእጅ እንደመሆኑ መረጃዎች የሚጠፉበት አጋጣሚ እንዳለም አንስተዋል።

ከእዚህ በፊት ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማግኘት በቀን በአማካይ 50 ያህል ሰዎች እንደሚመጡ ገልጸው፤ ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቱ ተደራሽነትን ስለሚያሰፋ በርካታ ተገልጋዮችን በቀን ለማስተናገድ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You