
አዲስ አበባ፡- በአዲስ መልክ የተደራጁት 4 ሺህ 350 ብሎኮች ልማትን ለማፋጠን እና ሰላምን ለማስፈን እያስቻሉ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን፤ አስታወቀ። ከተማዋን መልሶ በማደራጀቱ ሂደት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች የማብቃት ሥራ ተሠርቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይመር ከበደ እንደገለጹት ፤ 4ሺህ 350 ብሎኮችን መልሶ የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል፤ ብሎኮችን መልሶ ማደራጀት ያስፈለገውም የመዲናዋን ልማት ለማፋጠንና ሰላምን ለመጠበቅ እንዲሁም መንግሥት ተደራሽ ያላዳረጋቸውን የልማት ሥራዎች በማህበረሰብ ተሳትፎ ለመሥራት አስቻይ ሆኖ በመገኘቱ ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል የነበረው አደረጃጀት የነበሩበትን ውስንነቶች በመገምገም እና በመተንተን መልሶ ማደራጀት አስፈላጊ ሆኗል ያሉት ኮሚሽነሩ ፤ የተደራጁ ብሎኮች ከፕላን ኮሚሽን ጋር በመሆን እየተጠናቀቁ እንደሆነና በዚህ መሠረት 4ሺህ 350 ብሎኮች መደራጀታቸውን ፤ እነዚህም ከ34 ሺህ በላይ አመራር የያዙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ብሎኮችን ከኮሪዶር ልማት ጋር በማጣጣም ማስተባበር እና ማብቃት ለኮሚሽኑ የተሰጠው ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህም ብሎኮች ተደራጅተው በአካባቢያቸው ልማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችል አደረጃጀት መዘርጋቱን ገልፀዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት ማህበረሰቡ ባሳየው የነቃ የልማት ተሳትፎ ብቻ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በማዋጣት አካባቢውን ማልማት መቻሉን ገልፀው፤ የበጎ ፈቃድ ሥራን በመሥራት መንግሥት ሊሠራው የነበረን ጉዳይ ሕዝቡ 43 ቢሊዮን ብር በሚገመት ወጪ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የህብረተሰቡ የልማት ፣ በበጎነት፣ የመተጋገዝና የመተባበር ባህል እንዲዳብር የማድረግ ሥራ የተሠራው ብሎኮችን ማእከል በማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እነዚህን ሥራዎች ሲሠሩ ባለፀጋዎች ትልቁን ድርሻ ወስደዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ወስደው ለበጎ ሥራ አውለዋል፤ ብሎኮችም የማይናቁ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ህብረተሰቡን እያገለገሉ ነው ብለዋል፡፡
በተደራጀ አቅም እየተገኘ ያለው ጥቅም በርካታ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ፤ ህብረተሰቡ ሰላም እና ልማቱ እንዲረጋገጥ እንዲሁም የተለያዩ ጥያቄዎቹ በተደራጀ መልኩ መልስ እንዲያገኙ የሚረዳ እና መልካም መስተጋብር የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አደረጃጀቱ በቀጣይም ሌሎች ተመሳሳይ የልማትና የሰላም ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም