“በአፍሪካ ሰላምን ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን ሚና ማጠናከር ይገባቸዋል” – ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፦ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን የማይተካ ሚና የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባቸውም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ 3ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ የሃይማኖት መሪዎች ለሀገር የሰላም ግንባታ ሚናቸው ሚና የጎላ ነው ። በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን የማይተካ ሚና የበለጠ ማጉላት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

እርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቀላሉ ለመወጣትና ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆኑን አንስተው፤ ሚናቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃመድ ዓሊ የሱፍ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ህብረት የG-20 አባል እንደመሆኑ ለሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት በትኩረት በመሥራት አፍሪካ ሰላምና ልማቷ እውን የሆነ አህጉር ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት የተረጋገጠባት ለሌሎች ምሳሌ የምትሆን ሀገር መሆኗንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በወቅቱ፥ ኢትዮጵያ የሃይማኖትና የብሄር ነፃነትና እኩልነት የተረጋገጠባት እንዲሁም አንዱ ሌላውን አክብሮ የሚኖርባት ሀገር መሆኗን አንስተዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የተለያዩ ሃይማኖቶች ለሀገር ሰላምና ልማት በጋራ እንዲሠሩና በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩ እየሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የትኛውም ሃይማኖት ለሰላም ለዜጎች አብሮነትና ለልማት በትጋት መሥራትና ለዓለምአቀፍ ተግዳሮቶች በትብብር መፍትሄ መስጠት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

በጉባዔው በሰላም ግንባታ፣ በሠብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ፣ በአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ጨምሮ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ላይ በመምከር ለቡድን 20 አባል ሀገራት ምክረ ሃሳብ እንደሚቀርብም አንስተዋል።

በዓለም ሃይማኖት ተቋማት ኢኒሼቲቭ የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አምባሳደር ሙሴ ሃይሉ በዚሁ ጊዜ እአአ በ2063 የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የተያዘው አጀንዳ እንዲሳካ የእምነት ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዓለምአቀፍ ተግዳሮቶች ለመሻገር የሕዝቦች መከባበር፣ መተባበርና የጋራ ሥራ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

የእምነት ተቋማት መልካምነትን፣ አብሮነትና ሰላምን በመስበክ ተከታዮቻቸውን መልካም ሥነ ምግባር ማላበስ አለባቸው ብለዋል።

በኢኮኖሚ የተሳሰረችና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የሃይማኖቶችን እኩልነትና ነፃነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አንስተው ፤ በዚህ ላይ የሃይማኖት ተቋማት በትጋት ሊሠሩ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ጉባዔው በተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦች፣ በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና በቀጣይ መስከረም ወር በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የ2025 የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ዓለምአቀፍ ጉባዔውን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከአፍሪካ የሃይማኖት ተቋማት ህብረት እና ከቡድን 20 የሃይማኖቶች ህብረት ፎረም ከአፍሪካ ህብረት የሃይማኖቶች ውይይት ፎረም ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁትም ተነግሯል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀመድ ዓሊ የሱፍ፣ የሰላም ሚንስትር መሐመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ዓለም አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች፣ አምባሳደሮች፣ ምሁራን፣መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎችም በጉባዔው መሳተፋቸው ታውቋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You