10ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባዔ መካሄድ ጀምሯል

ጥናታዊ ምርምሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ተመራማሪዎች እና ፖሊሲ አውጪዎች በጥምረት ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- ሳይንሳዊ እና ችግር ፈቺ ጥናታዊ ምርምሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ፖሊሲ አውጪዎች ተቀራርበው መሥራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

‹‹የሕዝብ አገልግሎት ትራንስፎርሜሽንና ልማት›› በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው 10ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባዔ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሠሩ የጥናት እና ምርምር ውጤቶች በመደርደርያ ላይ የሚቀመጡ አይደሉም ።

በሀገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተዓማኒነት፣ ተጠያቂነት እና ኃላፊነትን የሚጠይቅ የሕዝብ አገልግሎት ፍላጎት እያደገ መምጣቱን አመልክተው፤ ጥያቄዎቹ ተገቢነት ያላቸው፣ ቀጣይነት ላለው ልማት እና ሀገር አቀፍ ትራንስፎርሜሽን አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና ማህበራዊ ሳይንቲስቶች ተቀራርበው መሥራታቸው የሚፈለግ ነው ያሉት ሚንስትሩ ፤ ጥናታዊ ምርምሮችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በዩኒቨርሲቲዎች እና በኢንዱስትሪው መካከል ድልድይ ሊፈጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

መልካም አስተዳደር መዳረሻው ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ጉዞ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ ጥናትና ምርምር እንደ ቁልፍ አቅጣጫ የሚያገለግል ነው ፤ ዩኒቨርሲቲው በያዛቸው አብሮ የመሥራት መነሳሳት ቁልፍ አጋር መሆናቸውን ገልፀዋል።

ኮሚሽነሩ የዲጂታል መሠረተ ልማት በፍጥነት እያደገ መምጣቱን፣ ማህበረሰብን በማገልገል ረገድ የመንግሥት ተቋማት ራሳቸውን መፈተሽ እንደሚገባቸው አመልክተው፤ ይህም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን /በቴክኖሎጂ እድገት ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑን አመልክተዋል።

ዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑ ሰው ተኮር መሆን አለበት፣ ለዚህ ደግሞ የተቋማት ዝግጁነት እና የፖሊሲ ማሕቀፍ ላይ መሥራት ያስፈልጋል ፤ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችም ለስኬታማነቱ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ንጉሡ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው 10ኛ የምርምር ጉባዔ ላይ ሳይንሳዊ ሒደትን የተከተሉ እና መመዘኛዎችን ያለፉ 33 ጥናቶች መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ጥናቶች ውስጥም 19 ጥናቶች በዩኒቨርሲቲው የተጠኑ ሲሆን 14 ጥናቶች በጉባዔው ተሳታፊ የሆኑ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የቀረቡ ናቸው ብለዋል። በ10ኛው የምርምር መድረክ ላይ የሴት ጥናት አቅራቢዎች ቁጥር ከፍ ብሎ መታየቱንም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸው፤ እየተጋፈጠች ለምትገኘው ፖለቲካዊም ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ፤ ሳይንሳዊ እና ችግር ፈቺ ምርምሮች እንደ ቅንጦት መታየት የለባቸውም ብለዋል።

በ10ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባዔ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ፣ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተሳታፊ ሲሆኑ በዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበረሰብ ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ በመድረኩ ተገልጿል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You