በትግራይ ክልል ከ35 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደረገ

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት በክረምት ወቅት በአረንጓዴ ዐሻራ ከ35 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል መዘጋጀቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለፀ፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብትና ደን ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ተስፋይ ተኽለሃይማኖት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ በዘንድሮ ዓመት በክረምት ወቅት በ 214 ወረዳዎች ከ71 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ታቅዶ፤ ከ35 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በማፍላት ለመትከል ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡

ከባለፈው ዓመት የተሻለ ሥራ ለመሥራት ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ የተለያዩ የሀገር በቀል እና የውጭ ዝርያ ያላቸው ፤ ፍራፍሬ፣ ለእንስሳት መኖ የሚያገለግሉ እፅዋቶች እና ለከተማ ውበት ታስበው የተዘጋጁ ችግኞች መዘጋጀታቸውን፤ እንዲሁም ችግኞቹ የሚተከሉበት ቦታ ተመርጦ መከለሉን ገልፀዋል፡፡

ባቀድነው መሠረት ለማከናወን የተለያዩ ምክንያቶች እንዳናሳካ አድርገውናል ያሉት ኃላፊው፤ በተቻለ አቅም ከተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች የተገኘ ድጋፍ እስከ አሁን ከ35 ሚሊዮን በላይ ችግኝ አዘጋጅተናል፤ ይህም ከታቀደው 49 በመቶ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ የተካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እርጥበትን በማከማቸት ለደን ልማት በሚያመች መልኩ መከናወኑን ጠቅሰው፤ በየአካባቢው የደን ልማት አስፈላጊነትና ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ከህብረተሰቡ ጋር መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ የደን ምንጠራ እና ጭፍጨፋ በተመለከተ እስከ አሁን የደረሰው የደን አደጋ በግልፅ ባይቀመጥም እጅግ ብዙ መሆኑን ጠቁመው፤ወደ ፊት በጥናት ለመለየት ታቅዷል፤ ለቀጣይ የተፈጥሮን ደን ለመንከባከብ እና ውድመት ለመቆጣጠር በትኩረት እንሠራለን ብለዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት፤ ሕዝባችን በከባድ ፈተና ውስጥ ሆኖም በልማት ሥራ ላይ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው፤ አሁንም በተለይ በክልሉ የተከሰተው ከፍተኛ የደን ውድመትን ለመከላከል እና ወደ ነበረበት ለመመለስ እንዲሁም የበለጠ ለመሥራት አጠናክሮ መሬት የወረደ ሥራ መሥራት አለበት ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You