የከተማዋን ነዋሪዎች በቀጥታ ተሳታፊ የሚያደርጉ የሰላምና ጸጥታ አደረጃጀቶችን የማጠናከር ሥራ ይሠራል

አዲስ አበባ፦ የከተማዋ ነዋሪዎችን በቀጥታ ተሳታፊ የሚያደርጉ የሰላምና ጸጥታ አደረጃጀቶችን የማጠናከር ሥራ እንደሚሠራ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ሥልጠና የወሰዱ አሥራ አንድ ሺህ የሰላም ሠራዊት አባላትን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ትናንት አስመርቋል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በወቅቱ እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ እየለማችና እየተለወጠች በመሆኑ የሕዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያረጋገጡ ጠንካራ የጸጥታና የደህንነት አደረጃጀት ያስፈልጋታል። ከዚህ አካያ የከተማዋን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የሕዝቡን ባለቤትነት በሚያጎላ መልኩ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ከ253 ሺህ በላይ የሰላም ሠራዊቶችን፣ ከ12 ሺህ በላይ የሕዝብ ቅጥር ጥበቃዎችን፣ ከ40 ሺህ በላይ የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎችን እና በርካታ የጸጥታ ኃይል አጋዥ ኃይሎች የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ሌት ተቀን ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።

ይህ ሕዝባዊ የጸጥታ አደረጃጀት በ2017 ዓ.ም የተከናወኑ የአደባባይ በዓላትና ልዩ ልዩ ሁነቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቁ የበኩሉን ሚና ተወጥቷል ያሉት ወይዘሮ ሊዲያ፤ በዚህም የከተማዋ የጸጥታ አለኝታ መሆኑን በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን ተናግረዋል።

ቢሮው በሁለት ዙር ከ32 ሺህ በላይ አዳዲስ የሰላም ሠራዊት አባላትን መልምሎና አሠልጥኖ ከነባሮቹ ጋር እንዲቀላቀሉ አድርጓል። በዚህም የአካባቢያቸውን እና የከተማቸውን ሰላም እየጠበቁ ይገኛሉ። አሁን ደግሞ 11 ሺህ የሰላም ሠራዊት አባላትን በበጀት ዓመቱ 3ኛ ዙር 4ተኛ ኮርስ ማስመረቁን ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ተመራቂዎቹ በሀገር ፍቅርና አርበኝነት፣ በሰላም አስፈላጊነት እና የእያንዳንዱ ዜጋ ሚና እንዲሁም በወንጀል ምንነትና በመከላከያ ዜዴዎች ላይ የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ሥልጠናዎችን ተከታትለው በብቃት ያጠናቀቁ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በቀጣይ የከተማዋን ሰላም፣ ጸጥታና ሕግ የማስከበር ሥራዎችን በተቋም አቅም ከመፍጠር ባለፈ የከተማዋ ነዋሪዎች በቀጥታ ተሳታፊ የሚሆኑበት የሰላምና ጸጥታ አደረጃጀቶችን የማጠናከር ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፤ የከተማዋ የልማት ሥራ በሰላም መደፍረስ እንዳይስተጓጎል የተመራቂ የሰላም ሠራዊት አባላት ሚና ከፍተኛ ነው። የየትኛውንም የጥፋት ኃይል ዓላማ ለማክሸፍ የተጠናከረ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ሂደት የከተማዋ ነዋሪዎች አይነተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ አዲስ አበባ ብልፅግና ሁለንታዊ እንዲሆን ዋናው ሰላም በመሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች የተደራጁ የሰላም ሠራዊት አባላት የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ተመራቂ የሰላም ሠራዊት አባላት ከመደበኛ የፀጥታ መዋቅር ጋር የተጠናከረ ቅንጅት በመፍጠር የሰላም ማስጠበቅ ሥራውን መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You