
የምርምር ሥራዎች ዋነኛ ጠቀሜታ ኅብረተሰቡ በዕለት ተዕለት የኑሮ ዘይቤው የሚያጋጥሙትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ ማመንጨት ነው። ያለንበት የዲጂታላይዜሽን ዘመን ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግሮች የሚፈቱ ወጪ፣ ጊዜንና ጉልበትን የሚቆጥቡ ለአጠቃቀም ምቹ የሆኑ የምርምር ሥራዎች መኖራቸውን ይፈልጋል።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት የኅብረተሰቡን የኑሮ ጫና ሊያቀሉ የሚችሉ የምርምር ሥራዎች እንደሚያስፈልጓቸው ይታመናል። እነዚህ የምርምር ሥራዎች የሚሠሩት በምርምር ተቋማት፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በግለሰቦች ጨምሮ ቢሆንም፣ የምርምር ተቋማት በተለየ መልኩ ዋነኛ ሥራቸው አድርገው ይሠሯቸዋል፡፡
ምርምር ላይ ትኩረት አድርገው የኅብረተሰቡን ችግር ሊቀርፉ የሚችሉ ምርምሮችን ከሚሠሩ የምርምር ተቋማት መካከል አንዱ ባዮና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዩት ነው። ኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰቡን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ችግር ፈቺ የምርምር ቴክኖሎጂዎች እያፈለቀ ለሕዝብ እንዲተዋወቁና ተግባራዊ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል።
ኢንስቲትዩቱ በቅርቡ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለቤትነት መብት አግኝቶባቸው ካስተዋወቃቸው የምርምር ሥራዎች መካከል የመጠጥ ውሃ የሚያጣራው እንዲሁም ከቡና መፈልፈያ ወይም ማጠቢያ ጣቢያዎች የሚወገደውን አሲዳማ ውሃ መከም የሚያስችለው ቴክኖሎጂዎች ይጠቀሳሉ።
ሁለቱም የምርምር ሥራዎች በኅብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በተካሄዱ የምርምር ሥራዎች የተገኙ መሆናቸውን የባዮና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ገነት ጸጋዬ ይገልጻሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ከምርምር ሥራዎቹ መካከል አንደኛው የመጠጥ ውሃን የሚያጣራው ቴክኖሎጂ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ከእሸት ቡና መፈልፈያ ወይም ማጠቢያ ፋብሪካዎች የሚወገደውን ውሃ አሲዳማነት የሚያክም የምርምር ሥራ ነው። ኢንስቲትዩቱ በሁለቱም ምርምሮች በቅርቡ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ተቋም የባለቤትነት መብት አግኝቷል፡፡
የምርምር ሥራዎቹን ለመሥራት ሲታቀድ ኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ችግር ምንድነው የሚለውን ለመዳሰስ እንደተሞከረ ተመራማሪዋ ይገልጻሉ፤ እንደ ሀገር ከውሃ ማጣራት ጋር ተያይዞ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቅሰው፣ እነዚህን ችግሮች ሊፈታ የሚችል የውሃ ማጣሪያ አዘጋጅቶ መጠቀም እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ወደ ምርምር መገባቱን ተናግረዋል። በተደረጉ ጥናቶችም ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ንጽህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት እየተቸገረች መሆኗን አመላክተዋል።
ተማራማሪዋ ገነት እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ መሥራት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ንጽህ የመጠጥ ውሃ ለሁሉም ማዳረስ ባይቻል እንኳ የውሃ ማጣሪያ (ማከሚያ) ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ በመሥራት የመጠጥ ውሃው እንዲጣራ ማድረግ ያስፈልጋል። ከውጭ የሚገቡ የውሃ ማጣሪያ ቴክኖሎጂዎችንም በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት ይገባል። ይህም ቴክኖሎጂ በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ እውን ሆኗል፡፡
የውሃ ማጣሪያውን በሀገር ውስጥ ለማምረት በማሰብ የተጀመረው የምርምር ሥራ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው፣ የውሃ ማጣሪያውን በ‹‹ናኖ›› ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከቡና ገለባ እና ከሸንኮራ አገዳ ተረፈ ምርት መሥራት መቻሉን አስታውቀዋል። ማጣሪያው በላብራቶሪ ተፈትሾ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ የውሃ ማጣሪያው ባክቴሪያን የሚገድል፣ በጣም መርዛማ የሆኑ ከባድ ሜታሎችን ማጣራት እንዲችል ተደርጎ የተዘጋጀ ነው። አሁን በሀገሪቱ ገበያ ላይ ከዋሉት የውሃ ማጣሪያዎች በብዙ መልኩ የተለየ ነው። የእስከ አሁኖቹ የውሃ ማጣሪያዎች ዋነኛ ችግር በአብዛኛው የሚጠቀሙት ግብዓት ከውጭ ሀገር የሚመጣ መሆኑ ላይ ነው፤ ዋጋቸውም የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘበ አይደለም። የመግዛት አቅም የሌላቸው ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ካልቻለ ደግሞ ለሁሉም ተደራሽ ሆነዋል ማለት አይቻልም።
አብዛኛው ሕዝብ በገጠሪቱ የሀገሪቷ ክፍል ስለሚኖር ለመጠጥ የሚጠቀመው ውሃ የወንዝ ውሃ ወይም የጉድጓድ ውሃ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ ውሃ እንደማይታክምና በጣም መርዛማ ኬሚካሎች ሊኖርበት እንደሚችል ጠቅሰው፣ የውሃ ማጣሪያዎችን ለመግዛት አቅም የሌለው የኅብረተሰብ ክፍል ውሃውን ለመጠጥነት ሊጠቀም የሚችልበት ሁኔታ ሰፊ መሆኑን ያመለክታሉ። ከውጭ የሚገቡ የውሃ ማጣሪያዎችን ገዝቶ ለመጠቀም ኅብረተሰቡ አቅም ላይኖረው እንደሚችል ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ እነዚህን የኅብረተሰቡን ችግሮች የሚፈታ የውሃ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ ይዞ መምጣቱን አስታውቀዋል። በዚህም አንደኛ በእያንዳንዱ አካባቢ ናሙና ወስዶ ውሃ ማጣሪያውን ማምረት እንደሚቻል፣ ሁለተኛ በየገጠሩ በየእያንዳንዱ ቤት ያለውን ፍጆታ መሠረት ባደረገ መልኩ የውሃ ማጣሪያውን በማዘጋጀት እንደሚሰራጭ አብራርተዋል፡፡
ተመራማሪዋ እንዳስታወቁት፤ በአሁኑ ወቅት በገበያ ላይ ብዙ ዓይነት የውሃ ማጣሪያዎች አሉ፤ ይሁንና አብዛኛዎቹ በዓይን የሚታዩ ነገሮችን የሚያጣሩ ናቸው። በኢንስቲትዩቱ በምርምር የተገኘው የውሃ ማጣሪያ ግን ባክቴሪያዎች፣ ፍሎራይድና ሌሎች ኬሚካሎችን ማጣራት/ማከም/ ያስችላል።
ማጣሪያው በዱቄት መልክ የተዘጋጀ መሆኑ ከሌሎች ማጣሪያዎች ለየት እንዲል ያደርገዋል። ገበያ ላይ ያሉት ማጣሪያዎች ከዚህ በተለየ መልኩ የተዘጋጁ ናቸው። ማጣሪያዎቹ በየጊዜው ከስድስት ወራት እስከ አስራ ሁለት ወራት የሚቀየሩ ናቸው። ‹‹እኛ በዱቄት መልኩ ስንሠራቸው ከፍተኛ አቅም እንዲኖራቸው አድርገን ነው። መርዛማ ኬሚካሎችን ከውሃው ለይተው የሚያስቀሩ ናቸው›› ብለዋል፡፡
አዲሱ የውሃ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ እስካሁን ዋጋ እንዳልወጣለት ተናግረው፣ ለአንድ ቤተሰብ ምን ያህል የውሃ ማጣሪያ ያስፈልጋል የሚለው ተጠንቶ ዋጋ እንደሚወጣለት አመልክተዋል። ‹‹በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሄደን እንደተመለከትነው ፍሎራይድ ያለበት ቦታ ላይ መርዛማ ኬሚካሎች አሉ፤ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ መርዛማ ከባድ ሜታል ነጥረ ነገር ይስተዋላል። እነዚህ ነገሮች ከቦታ ቦታ የተለያዩ ስለሆነ የየአካባቢውን ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ የውሃ ማጣሪያዎችን ተደራሽ ለማድረግ አቅደናናል፡፡›› ሲሉም ተመራማሪዋ ጠቁመዋል።
የውሃ ማጣሪያ የላብራቶሪ ሂደቶችን አልፎ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ቢሆንም ገና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ አልተደረገም የሚሉት ተመራማሪዋ ፤ ኅብረተሰቡ የሚጠቀመው ውሃ ምን ዓይነት የውሃ በካይ ነገሮች እንዳሉበት ለመፈተሽ ናሙና በመውሰድ ባክቴሪያ ያስወግዳል ወይስ አያስወግድ የሚለው እንደሚጣራም ገልጸዋል። ከዚያም አስፈላጊው ዓይነት የውሃ ማጣሪያ ተዘጋጅቶ ተደራሽ እንዲሆን ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የውሃ ማጣሪያውን ለመሥራት ሁለት ዓመት ያህል መፍጀቱን ጠቁመው፤ ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ማድረግ ላይ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል። በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያለውን ውሃ በመፈተሸ ጥቅም ላይ እንዲውል እንደሚደረግ አመልክተዋል።
ሁለተኛው የምርምር ሥራ ከእሸት ቡና መፈልፈያ/ማጠቢያ ጣቢያዎች የሚወገደውን አሲዳማ ውሃ ማጣራትን የተመለከተ ነው። ይህንን አሲዳማ ውሃ ለማከም ምርምር መካሄዱን ተመራማሪዋ አስታውቀው፣ ከመፈልፈያ ጣቢያው የሚወገደውን ውሃ አካባቢን በማይጎዳ መልኩ ከኬሚካል ነፃ ማድረግ የሚያስችል ማከሚያ እንደተዘጋጀለት አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ አሲዳማ ውሃ ለማከም ለአንድ ሜትር ኪዩብ ውሃ አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ግራም ማጣሪያ ጥቅም ላይ ይውላል። የመጠጥ ውሃውን ለማጣራት ደግሞ ለአንድ ሜትር ኪዮብ ውሃ ሶስት ነጥብ ስድስት ኪሎ ግራም ማጣሪያ ጥቅም ላይ ይውላል። አሲዳማ ውሃውን ለማከም ምን ያህል የማከሚያ እንደሚያስፈልግ በትክክል ተጣርቶ በላብራቶሪ ተፈትሾ በትልቅ በኢንዱስትሪ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ተማራማሪዋ አስረድተዋል።
እንደ ተመራማሪዋ ማብራሪያ፤ አሲዳማው ውሃ ከተጣራ በኋላ ወደ ሌላ ማከሚያ ዘዴ እንዲሄድ ይደረጋል። አሁን የቡና ማጠቢያ ጣቢያዎች የሚያስወገዱት አሲዳማ ውሃ ቀጥታ እየተለቀቀ ሲሆን፣ አሲዳማነቱን ለመቀነስ ግን ኬሚካል ጥቅም ላይ ይውላል።
ያ ኬሚካል ደግሞ ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ሲውል እንዲሁም ወደ ውጭ ሲለቀቅ ጨዋማ የሆነ አካባቢ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። ጨማዋ አካባቢ ሲፈጠር ደግሞ አካባቢውን ለእርሻ ለመጠቀምም ሆነ ለማከም ከባድ ያደርገዋል።
ይህ ከመሆኑ በፊት አካባቢንም ሆነ ሰው በማይጎዳ መልኩ በአካባቢው የሚገኘውን የቡና ገለባ በመጠቀም የውሃውን አሲዳማነት ለማከም እንደሚቻል ተመራማሪዋ አመልክተዋል። ይህንን የቡና ገለባ በመጠቀም አሲዳማ ውሃን ማከም ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማከሚያው አካባቢን የማይጎዳ ከመሆኑን ባሻገር ከዋጋ አንጻር በጣም ርካሽ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ አሲዳማ ውሃን የማከም የምርምር ሥራው በቤተመኩራ (ላብራቶሪ) ደረጃ አንድ ዓመት ያህል ጊዜ ወስዷል። ይህንን ቴክኖሎጂ የቡና ማጠቢያ ጣቢያዎች እንዲጠቀሙበት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ታምኖበትም በተለየ መልኩ በኢንዱስትሪ ደረጃ ለመሥራት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል። የቡና ማጠቢያ ጣቢያዎች ቴክኖሎጂውን እንዲያውቁትና እንዲጠቀሙበት ለማድረግም የማስተዋወቅ ሥራ ይከናወናል።
እነዚህን የምርምር ሥራዎች ለመሥራት ተግዳሮት የሆነብን ናሙናዎች መፈተሽ የሚያስችሉት መሳሪያዎች ሀገር ውስጥ አለመኖራቸው ነው የሚሉት ተመራማሪዋ፤ በተለይ የውሃ ማጣሪያውን ናሙናዎች ካናዳ ዩኒቨርሲቲ በመላክ ፍተሻው እንደተሠራም ይገልጻሉ። በተጨማሪም ሀገር ውስጥ ያሉትን መሳሪያዎች በመጠቀም መሥራት መቻሉን አመላክተዋል፡፡
የአሲዳማ ውሃ ማከሚያ ቴክኖሎጂውን ሀገር ውስጥ የተሠራ በመሆኑ ኢንስቲትዩቱን እምብዛም አስቸጋሪ ነገሮች እንዳላጋጠሙት ገልጸዋል። ኅብረተሰቡ ከቡና ማጠቢያ ጣቢያዎች የሚወጣው አሲዳማ ውሃ አካባቢን የሚጎዳ ስለመሆኑ በቂ ግንዛቤ እንደሌለው ተናግረዋል፤ በዚህ ላይ በቂ ግንዛቤ እስከሚያዝ ድረስ ማከሚያው ጥቅም ላይ እንዲውል በሚደረግበት ወቅት ተግዳሮት ሊገጥመው እንደሚችል ጠቁመዋል።
አሲዳማ ውሃው አካባቢውን እየበከለ ጥቅም ላይ ሳይውል መቆየት እንደሌለበት ገልጸው፤ ኅብረተሰቡም የውሃ ሀብቱን መጠቀም ሲገባው በበካይ ኬሚካሎች ምክንያት ከመጠቀም ተቆጥቦ እንዳይቸገር ግንዛቤን በማስረጽ ተግባር ላይ እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ሁለቱም የምርምር ሥራዎች እንደመሆናቸው በጀት ተመድቦላቸው የተሠሩ ናቸው። የመጠጥ ውሃ ማጣሪያው ሦስት መቶ ሺህ ብር የሚገመት ውጭ ተደርጎበታል፤ አሲዳማ ውሃ ማከሚያው በትንሽ በሚባል መልኩ ሃምሳ ሺ ብር ወጥቶበታል። የዚህ ምክንያቱ አሲዳማው ውሃን በማከም ጥቅም ላይ የሚውለው የቡና ገለባ በቀላሉ ስለሚገኝ ነው።
አሲዳማውን ውሃ ለማከም የምንጠቀመው ሂደት በጣም ቀላል ነው ሲሉም ገልጸዋል። ቴክኖሎጂው ተግባራዊ ሲደረግ የሚታከመው ብዙ ውሃ እንደመሆኑ እንዲሁም በኢንዱስትሪ ደረጃ ስለሚሠራ ከግንባታ ጀምሮ ብዙ ነገሮች ያስፈልጉታል፤ ጎን ለጎንም ሌሎች የማከሚያ መንገዶች ስለሚያስፈልጉ ሊመደብለት የሚገባው በጀት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።
ተመራማሪዋ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ለብዙ ሰዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩም አስታውቀዋል። ወጣቶችን በማደራጀት የውሃ ማጣሪያውን እንዲያመርቱ ማድረግ ይቻላል፤ በዚህም ለብዙ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ያስገኛል።
አንድ ውሃ ማጣሪያ ሲሠራ ብዙዎችን ያማከለ እንደመሆኑ ብዙ ወጣቶች እየተደራጁ መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ ይፈጥራል። ወጣቶቹ ቴክኖሎጂውን በደንብ እንዲያውቁት ለማድረግ አቅማቸውን በሥልጠና መገንባት ያስፈልጋል። በዚህ መልኩ ወደ ሥራ እንዲሠማሩ ይደረጋል።
አሲዳማ ውሃን ማከምም እንዲሁ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥ ተመራማሪዋ ያመላክታሉ። ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን የማከለ ቀላል መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህ የኀብረተሰብ ክፍሎች እውቀቱ እንዲኖራቸው ከተደረገ ብዙዎች እንዲሳተፉ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም