ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀደምት የስልጣኔ ስራዎቿ ዓለም ቢያውቃትም፤ እነዛን የስልጣኔ ሥራዎቿን ማስቀጠል ተስኗት ከስልጣኔ እና ከዕድገት በስተጀርባ ዳዴ እያለች ትገኛለች:: የዛሬ 30 እና 50 ዓመት ከሀገራችን በስልጣኔም በምጣኔ ሀብትም የበታች የነበሩት እንደእነ ቻይና፣ ታይዋን፣ ሲንጋፖር፣ ሰሜንኮሪያ፣ ህንድ ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉት ሀገሮች የተለያዩ ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ከፍ በማድረግ የትናንት ታሪካቸውን በመቀየር ዛሬ ላይ አለም ላይ ካሉ ሀያላን እና ያደጉ ሃገራት ተርታ መመደብ ችለዋል::
ሀገርን ወደ እድገትና ስልጣኔ፣ ህዝብን ደግሞ ካለበት ዘርፈ ብዙ ችግር ለማላቀቅ ዋነኛው ቁልፍ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራ መሆኑን በማመን የወገናቸውን ችግር ለመፍታት ከዓመታት በፊት በቅንጦት ከሚኖሩበት ከአሜሪካን ሀገር ወደትውልድ ሀገራቸው ሁለት የፈጠራ ስራ ይዘውልን የመጡትን ፕሮፊሰር እያሱ ወልደሰንበትን ስለ ፈጠራ ስራቸው አነጋግረናቸዋል::
ፕሮፌሰሩ ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ነው:: ትምህርታቸውንም በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ከ1ኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ተከታትለዋል::የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለሁለት ዓመት በሀገር ውስጥ ከተከታተሉ በኋላ፤ የውጭ ሀገር የትምህርት እድል በማግኘታቸው ወደ አሜሪካን ሀገር ተጉዘው እ.አ.አ ከ1992 እስከ 1989 የባችለር፣ የማስተርስ እና የዶክትሬት ድግሪአቸውን አግኝተዋል::
በአሜሪካ ለአንድ ዓመት በውኖና እስቴት ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፊሰርነት አገልግለዋል:: ሉዩዋና እስቴት ዩኒቨርሲቲ በመዛወርም ለ16 ዓመታት ከረዳት ፕሮፊሰርነት እስከ ሙሉ ፕሮፌርነት ማዕረግ በማግኘት አገልግለዋል::
«በረሮ በአንድ ቤት ውስጥ የመመገቢያ እቃችንን አጥበን ካስቀመጥን በኋላ እዛ እቃ ላይ ከቆሻሻና ከአፈር ላይ ተነስታ በማረፍ የተሸከመችውን ቆሻሻ አራግፋ ነው የምትሄደው:: ከበረሮ ዝንብ ትሻላለች ቢያንስ አየር ላይ በራ አንድ ነገር ላይ አርፋ ነው የምትሄደው:: በረሮዋ ግን ሙሉ ለሙሉ ከቆሻሻ ላይ በመቆየት የተሸከመችውን በሽታ አምጭ ተህዋስያን የምንመገብበት ዕቃ ላይ ሙሉ ለሙሉ ነው ጥላ የምትሄደው:: እናም ጠዋት ላይ ይሄን አጥበነዋል ያልነውን ዕቃ ነው ለመመገቢያነት የምንጠቀመው:: በዚህን ጊዜ እኛ ጎልማሶች ምናልባትም ይሄን በሽታ አምጪ ተህዋስያን ልንቋቋም እንችል ይሆናል::
«ልጆች ይህን መቋቋም አይችሉም:: ስለዚህ ሁሌም ለምን የሀገራችን ልጆች እንደ ሰለጠኑ አገራት ልጆች ጤንነታቸው ተጠብቆ አያድጉም፤ ለምንስ እናቶች ልጆቻቸው ሲታመሙ ሁሌ ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣሉ፤ ልጆችስ ከመታመማቸው በፊት ለምን አስቀድመን በሽታውን አንከላከልም በሚል ቁጭት ይህን የፈጠራ ስራ ከብዙ ውጣውረድ እና ጥረት በዚያው በአሜሪካን ሀገር ሳይንሳዊ ላቦራቶሪ እና መሳሪያዎችን በመጠቀም፤ የወገንን ደህንነት ባገናዘበ መልኩ ቅድሚያ የበረሮ ማጥፊያውን ከዚያም የአይጥ መግደያውን ከባለቤቴ ጋር ለመስራት ቻልን::
«አንዳንድ ጊዜ ምርምር ብዙ ተለፍቶበት እውን ላይሆን ይችላል፡፡ እኛ ግን እግዚአብሔር እረድቶን ራዕያችን እውን ሆኖልን ከስድስት ዓመት በፊት ነበር እነዚህን የፈጠራ ስራዎች ይዘን ወደትውልድ ሀገራችን የተመለስነው:: ባለቤቴም ዶክተር አደይ አበባ አበራ ሙሉ ለሙሉ የፈጠራው አጋርና ባለቤት ናት» በማለት የፈጠራ ስራውን ለመስራት ምን እንዳነሳሳቸው ነግረውኛል::
«የበረሮ ማጥፊያው በረሮዎችን ይገድላል፤ እንቁላላቸውንም የሚያመክ ነው:: መድሀኒቱ ምንም አይነት ሽታ ስለሌለው አየር አይበክልም:: ስለዚህ በሰው ዘንድ ምንም አይነት የጎንዮሽ ችግሮችን እንዳይፈጥር ተደርጎ በሳይንሳዊ መንገድ የተሰራ ስለሆነ ዝምብሎ መድሃኒቱን እቃ ላይ ቁጭ ማድረግ ነው:: ስለዚህ እቃ ማውጣት፣ ቤት መዝጋት፣ ህፃናት እና አዛውንቶችን ከቤት ውጭ እንዲቆዩ ማድረግ አያስፈልግም፤ በረሮዎቹም መድሃኒቱን ነክተው መመገቢያ እቃዎችን ቢነኩ በሰው ላይ ምንም ችግር አያመጣም:: እንዲሁም በሶስት ቀን ውስጥ አንድ ካርቶን በረሮዎችን ማጥፋት ይቻላል::
«ሁለተኛው የፈጠራ ስራችን የአይጥ መግደያው ሲሰራ ብዙ ሳይንሳዊ ምርምር በማድረግ እስካሁን አለም ላይ ካሉ የፈጠራ ስራዎች ለየት ባለ መልኩ የሰራ ነው:: አይጥዋ መድሀኒቱ ጥሟት እንድትበላ በማድረግ በሶስት ቀን ውስጥ አፍዝዞ የሚገድል ነው:: እንዲሁም ከሞተችም በኃላ ምንም ሽታ እንዳይኖራት የሚያደርግ ነው:: በተጨማሪም ካሁን ቀደም የነበሩ የአይጥ መግደያ መድሀኒቶች አይጥን ብቻ ሳይሆን ሰውንም የሚገድሉ ነበሩ:: እናም ይሄን ችግር በመቅረፍ አይጥን እንጂ የሰው ልጆችን እንዳይገድል በማድረግ ለመስራት ችለናል::
«እነዚህን የፈጠራ ስራዎች ለመስራት ለእያንዳዳቸው አምስት አምስት አመት ፈጅቶብናል:: እነዚህን ምርቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ወይም 99.9 በመቶ ከሀገር ውስጥ ጥሬ እቃ እና ንጥረ ነገሮች ነው የሚመረቱት:: ቀሪው 0.1 በመቶ የሚሆነው ንጥረ ነገር ከውጭ የሚገባ ነው :: ይህ ማለት ከ 100 ኪግ የበቆሎ ዱቄት ውስጥ 5 ግራም ንጥረ ነገር መጨመር ማለት ነው::
«በአጠቃላይ ሁለቱም የፈጠራ ስራዎቻችን በረሮ እና አይጥን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፋ በማድረግ በሰው ልጆች ላይ ምንም አይነት የጎንዮሽ ችግር እንዳይፈጥር አድርገን የተሰራ ነው:: በዚህም ታይፎይድ፣ ተስቦ፣ ሄፕታይተስ የመሳሰሉትን በሽታዎች ቀድመን በመከላከል ጤነኛ ልጆች እና ቤተሰብ እንዲኖረን ያስችለናል:: በእነዚህ በሽታ አምጭ ነፍሳት ምክንያት የሚሞቱ ህፃናት ቁጥርም መቀነስ ተችሏል::
እንዲሁም ታሞ ከመማቀቅ እና ካላስፈላጊ የህክምና ወጭ ህብረተሰቡን መታደግ ችለናል» በማለት ስለፈጠራ ስራቸው ጠቅለል ያለ መረጃ ሰጥተውናል::
ፕሮፊሰር እያሱ ሲያብራሩ « ተደራሽነቱ በሀገራችን ሰባት ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በትልልቅ ከተሞች የሚገኝ ሲሆን፤ ለገበሬው መድሀኒቱን ያለትርፍ ለመሸጥና ለማዳረስ በሂደት ለይ ነን:: ምክንያቱም አርሶ አደሩ በአይጥ ምክንያት በየዓመቱ 25 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን ያጣል:: ይህ ማለት አንድ ገበሬ አራት ኩንታል እህል ቢያመርት ከእርሻ እስከ ጎተራ፣ ከጎተራ እስከ ሸማች እስኪደርስ ድረስ አንድ ኩንታል እህል በአይጥ ይወድምበታል ማለት ነው::
በዚህም በሀገራችን አይጥን ማጥፋት ብንችል 32 በመቶ ጠቅላላ የሀገሪቱን ምርት መጨመር ያስችለናል:: ነገር ግን ይህን በሰው ላይ ምንም የጎንዮሽ ችግር የማይፈጥር መድሀኒቱን በመድሀኒት ቤቶች እንዳንሸጥ ስለተከለከለ ህብረተሰቡ በቀላሉ ለማግኘት ተቸግሯል፤ እኛም ምርታችንን ከፍ አድርገን ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ተግዳሮት ሁኖብናል»
ፕሮፊሰር እያሱ ከመንግስት እና ከህብረተሰቡ ያገኙትን ድጋፍም እንዲህ ሲሉ ነግረውናል « መንግስት የፈጠራ ስራውን ለመስራት የሚያገለግሉ ሳይንሳዊ የሆኑ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ እንድናስገባ አድርጎናል፤ እንደስኳር እና ዘይት የመሳሰሉ ግብአቶችን በጅምላ እንድናገኝ እረድቶናል:: እንዲሁም ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በዛን ጊዜ ሚኒስትር ከነበሩት ዶክተር አብይ እጅ ለሰራነው የፈጠራ ስራ ባለቤቴ የማበረታቻ የዋንጫ ሽልማት ተቀብላለች:: በሌላ በኩል ህብረተሰቡም ይህን የፈጠራ ስራ በአገራቸው ምርት እምነት ጥለው፤ የፈጠራ ስራውን መርጠውት በመጠቀማቸው እና ምርቱን የተጠቀመው ህብረተሰቡ ለበረሮ እና ለአይጥ ፍቱን መድሀኒት መሆኑን በተግባር ካየ በኋላ ምርታችንን እንዲጠቀሙት ለሌሎች በመንገር ትልቁን የማስተዋወቅ ስራ ሰርቶልናል::”
ፕሮፊሰር እያሱ ወደ ሀገርቤት ከመጡ በኋላ በስራቸው ምን ምን ችግሮች አጋጥሞችው እንደነበርም እንዲህ አጫውተውናል« ይህን የፈጠራ ስራ ይዘን ስንመጣ እውቀት እና ሀሳብ ይዘን ህዝባችንን ለማገልገል ነው :: ታዲያ ይህን የፈጠራ ስራ ከግብርና ሚኒስቴር ፍቃድ እንዲሰጠን በጠየቅንበት ወቅት በተገቢው ጊዜ እና ወቅት ፍቃዱን አለማግኘታችን ለስራችን እንቅፋት ሆኖብን ነበር:: ለምሳሌ መጀመሪያ የጠየቅነው የበረሮውን ፍቃድ ነበር ይህን ፍቃድ ለማግኘት ስድስት ወር ነበር የፈጀብን፤ ይህን ምርት ጥራት እና አስተማማኝነቱን ለመፈተሽ ይህንን ያክል ጊዜ መውሰድ አለበት ብዬ አላምንም:: በተለይም ሁለተኛውን የፈጠራ ስራችን ማለትም የአይጥ መግደያውን ፈቃድ ለማግኘት ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ነው የፈጀብን:: ይህን መድሀኒት ወደምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ለመላክ በኡጋንዳ ፍቃድ ለማግኘት ሰባት ወር ነበር የፈጀብን::
በዚህም አንዳንድ ሰዎች ያልተገባ ጥቅምን በመሻት ሀላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ ባለመወጣታቸው ምክንያት ፍቃዱ በመዘግየቱ ምርታችንን ወደጎረቤት ሀገሮች መላክ አልቻልንም:: በወቅቱ ሀገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በሚያስፈልጋት ወቅት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አጥታለች:: እንደዚህ አይነት ለሀገር ሸክም የሆኑ የመንግስት ሀላፊዎችና ሰራተኞችን መንግስት በለውጡ አንድ ሊላቸው ይገባል::
«በሌላ በኩል ፈጠራ አንድ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ የፈጠራ ስራው ተግባር ላይ እንዲውል ማድረግ ሌላኛው ትልቅ ፈተና ነው::
ህብረተሰቡ ምንም ጥርጣሬ ሰይገባው ምርቱን እንዲጠቀም ማስቻል ነበር:: በኋላም ህብረተሰቡ ይህ የፈጠራ ስራ ከሌሎች መድሀኒቶች በብዙ ነገሮች የተሻለ መሆኑንና በሀገር ልጅ የወገንን ጤና በጠበቀ መልኩ የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት የተሰራ ሳይንሳዊ የፈጠራ ስራ መሆኑን በመገንዘብ ምርታችንን ለመጠቀም ጊዜ አልፈጀበትም»
ለወደፊትም ችግር ፈች የሆኑ ስራዎችን ለህብረተሰቡ እንደሚያቀርቡም እንዲህ ጠቁመውናል «በተጨባጭ ያየናቸው የህብረተሰባችን መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉ መገንዘብ ችለናል:: ለነዚህም መፍትሄ ለመስጠት ከባለቤቴ ጋር ሌሎች የፈጠራ ስራዎችን በመሰራት ላይ ነን:: ከነዚህም የፈጠራ ሰራዎች ውስጥ ለምሳሌ ያክል 85 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ህዝብ በገጠሩ የሀገራችን ክፍል የሚኖር ነው፤ እናም ይህ ህዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት አያገኝም:: ስለዚህ ይህን ችግር ለመፍታት ሙሉ ለሙሉ በሀገራችን በሚገኙ ቀለል ባሉ ጥሬዕቃዎች የሚሰራ ቆሻሻ የሆነ ወይም ሙሉ ለሙሉ ለመጠጥነት የማይውል ውሃን እንዲጠጣ የሚያደርግ እና አላስፈላጊ ኬሚካሎችን የሚያጣራ የውሀ ማጣሪያ በቅርቡ ለህብረተሰቡ ይፋ እናደርጋለን፤ ይህንንም ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለገጠሩ ማህበረሰብ እንዲደርስ እንሰራለን ብለን እናስባለን»
ፕሮፊሰሩም ለሌሎች በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ሲሉ ምክር አዘል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል « ለራሳችን ብቻ መኖር እስካልፈለግን ድረስ ሀገራችን ኢትዮጵያ የማንኛውንም ሰው እርዳታና ከማንኛውም ሰው ጋር አብሮ የመስራት ፍላጎት አላት::
ሀገራችንን ለማሳደግ እና ወገናችንን ለማገዝ ውጭ ሀገር ሆነን እድሉ በጣም ጠባብ ነው:: ለምሳሌ እኔ ለ16 ዓመት በአሜሪካን ሀገር ስኖር ለስምንት ተማሪዎች ብቻ ነው የትምርት እድል የሰጠሁት፡፡ ይህን ማድረጌ ከሚያስደስቱኝ ነገሮች አንዱ ነው:: ነገርግን ወደ ሀገር ቤት ከገባሁ በኋላ በስድስት ዓመት ውስጥ 30 ተማሪዎችን በማስተርስ እና በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ማስተማር ችያለሁ:: እንዲሁም እነዚህ ተማሪዎች የተለያየ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ የፈጠራ ስራዎችን እንዲሰሩ የማማከር ስራም ሰርቻለሁ:: በተጨማሪም ለ50 ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ችያለሁ:: በመሆኑም ከውጭ የሚመጡ ሰዎች ትንሽ ችግር ሲኖር ተስፋ ቆርጦ ተመልሶ መሄድ ሳይሆን፤ ችግሩን ከሚመለከተው አካል ጋር የሰከነ ንግግር በማድረግ የመፍትሄ አካል በመሆን ሀገራችንን ወደተሻለ እድገት ማድረስ ይጠበቅብናል::
«እኛ ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ሂደቶችን አልፈናል፡፡ ድሮ የአይጥ መርዝ ሲባል የሰውም መግደያ ነበር፤ እናም ይህን አመለካከትና ችግር ማስቆም ችለናል:: ይህ ለኛ ትልቅ ስኬት ነው:: እኛ ሁለት ሁነን መጥተን ይህን መስራት ከቻልን እና የህብረተሰቡን ችግር ማቃለል ከቻልን፤ ሁለት መቶ ሰው ያለውን እውቀት፣ የስራ ልምድና የፈጠራ ስራ ይዞ ወደ እናት ሀገሩ ቢመለስ በትንሽ ጊዜ ውስጥ በሀገራችን ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አዳጋች አይመስለኝም» ብለዋል፡፡
ፕሮፊሰር እያሱ በመጨረሻም ህብረተሰቡ በገበያ ላይ የተጭበረበሩ ምርቶች እየገቡ ስለሆነ ትክክለኛውን የዘራ ምርት ዘራ የበረሮ ማጥፊያና የአይጥ መግደያ የሚል በካርቶኑ ላይ መፃፉን እና በካርቶን መሸፈኑን በማረጋገጥ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል::
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011
ሰለሞን በየነ