
ሸማ በየፈርጁ ይለበሳል እንደሚባለው ጀግንነትም እንደዘመኑ እና እንደ ሁኔታው ይለያያል:: የሀገር ሉአላዊነት በተደፈረ፤ የሀገር ዳርድንበር በተወረረ፤ ነጻነት በተዋረደ ወቅት መሳርያን ወልውሎ መነሳት፤ አጥንትን መከስከስ እና ደምን ማፍሰስ ተገቢ እና የግድ የሚል ነው:: ጀግኖች አባቶቻችንም ያደረጉት ይህንን ነው::
ጀግንነት ግን ተኩሶ መግደል ብቻ አይደለም:: ለሰዎች በጎ ማድረግ፤ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት፤ ድህነትን እና ተረጂነትን መጠየፍ እና ከውጭ ተጽዕኖን ለመገላገል ቆርጦ መነሳት ዘመኑ የሚጠይቀው ጀግንነት ነው:: የዛሬ ትውልድም እንደትላንቱ መሳርያ አንስቶ መዋጋት አይጠበቅበትም:: ዛሬ እንደ ዓድዋው ግዜ መለከት ነፍቶ፤ ነጋሪት ጎስሞ እና ክተት አውጆ የሚካሄድ ጦርነት የለም:: የዘመኑ ጦርነት እና ጀግንነት ድህነትን ማሸነፍ ነው::
ኢትዮጵያ ለዘመናት ያህል ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ብትሆንም በምግብ ሰብል እራሷን ባለመቻሏ ነጻነቷን በሚገባ ሳታጣጥም ኖራለች:: በዓድዋ የተገኘው ድል በቅኝ ገዢዎች የፈረጠመ ኢኮኖሚ ሲጠመዘዝ እና ሉአላዊነታችን በስንዴ እርዳታ ሲፈተን ኖሯል::፡ በጦርነት የተሸነፉት ቀኝ ገዢዎች በተዘዋዋሪ በኢኮኖሚ ቅኝ ሊገዟት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም:: የዓድዋውን ድላችንን ለልመና በምንዘረጋው እጃችን የበታችነትን አሜን ብለን እንድንቀበል በብዙ ተሰርቷል::
የኢትዮጵያ ኩራትና ድል በስንዴ ልመና ኮስሶ በዓለም መድረኮች ሁሉ ለምናቀርበው ጥያቄና ለምናሰማው ድምጽ መጀመሪያ ሆዳችሁን ሙሉ የሚል ምላሽን ስናገኝ ኖረናል:: ሰርክ ድህነታችንን እያስታወሱ እና በ1977 ዓ.ም ያጋጠመንን ድርቅ እና ርሃብን እያጣቀሱ ከኩራታችን ሊያወርዱን ሲጣደፉ ተመልክተናል:: ኢትዮጵያን የርሃብ እና የድርቅ ተምሰሌት አድርጎ የመሳሉ ሴራ በመዝገበ ቃላት ጭምር እንዲሰፍር በማድረግ የዓድዋውን ድላችንን እና ጀግንነታችንን የሚፈታተን ተግባር ተፈጽሞብናል::
ስለዚህም ዘመኑ የሚፈልገው ጀግንነት ጦር ሰብቆ እና መሳርያ ወዝውዞ የሚገኝ ድል ሳይሆን ወገብን ጠበቅ አድርጎ በመሥራት የሚገኝ አሸናፊነት ነው:: የዓድዋው ድልም ዘላቂ ሊሆን የሚችለው በጦር ሜዳ የተገኘው ድል በልማቱም መስክ መድገም ሲቻል ነው:: በዚህ ረገድ እንደ ሀገር እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች የሚመሰገኑ ናቸው::
ድህነት እና ተመጽዋችነት የታሪካችን አካል ሆኖ ለዘመናት አብሮን የቆየ ቢሆንም በሥራ መቀየር እንደሚቻል በገሃድ ማየት ችለናል:: ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ስንዴ ሸማች ከሆኑ ሀገራት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የምትታወቅ ሀገር ነበረች:: በየዓመቱም እስከ 107 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በማስገባት 1 ቢሎዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ስትገፈግፍ ቆይታለች:: ሆኖም ባለፉት አራት ዓመታት መንግሥት ለስንዴ ምርት በሰጠው ትኩረትም ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ከማቆሟም በሻገር ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች:: ይህ ጥረቷም በዓለም ላይ ስንዴ በማምረት ተጠቃሽ ከሆኑ 18 ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል:: ኢትዮጵያ ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ስንዴ ላኪነት እራሷን በመለወጥም ታሪክ ሰርታለች፤ ለቀጠናው ሀገራትም ኩራትና ተስፋ ሰርቶ የመለወጥ ተምሳሌትም ሆናለች:: በአፍሪካም ግንባር ቀደም ስንዴ አምራች ሀገርም ለመሆን በቅታለች::
ኢትዮጵያ እንደ ስንዴው ሁሉ ለሩዝ ምርት ትኩረት በመስጠት ከሀገራዊ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለመላክ በትኩረት በመሥራት ላይ ትገኛለች:: በተለይም ሀገሪቱ ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሆነ የአየር ጸባይና ምቹ መሬት ያላት መሆኑ ያቀደችውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደማያዳግታት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ::
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውም በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በሩዝ መልማት የሚችል መሬት ቢኖርም በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ሩዝ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ታደርጋለች::
ሆኖም በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሥርዓት መተግበር ከጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግሥት ፊቱን ወደ ሩዝ ምርት በማዞር በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል:: በአሁኑ ወቅትም 38 ሚልዮን ኩንታል የማምረት አቅም ላይ ተደርሷል::
በተለይ በአማራ ፎገራና በጅማ እንዲሁም በሶማሌ ክልል እየተከናወነ ያለው የሩዝ ምርት ኢትዮጵያን ከሩዝ ተቀባይ ሀገርነት ወደ ላኪነት የሚያሸጋግራት ነው:: በፍራፍሬ ዘርፍም ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው::
እነዚህ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ኢትዮጵያ በአጭር ግዜ ውስጥ ከተረጂነት ተላቃ እራሷን በምግብ እንደምትችል አመላካቾች ናቸው:: መንግሥት ‹‹ተረጂነት ይብቃ›› በሚል መርህ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ከተመጽዋችነት ለማላቀቅ አዲስ ዕቅድ ይዞ መጥቷል::
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እስከ 250 ሺ ሄክታር በማረስ ኢትዮጵያ በቂ እህል ለማምረትና ከእርዳታ ተቀባይነት ለመላቀቅ አቅዳለች:: ለዚህ ደግሞ አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከእርዳታ እሳቤ እራሱን ማውጣትና እራስን በምግብ ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ሊያግዝ ይገባል:: ሁሉም እርዳታ መቀበልን ከተጸየፈ ኢትዮጵያ ከተረጂነት ወደ ሰጪነት የምትሸጋገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም::
በአጠቃላይ በለውጡ ዘመን በግብርና ምርታማነት ላይ የተሰሩት ሥራዎች ነገን በተስፋ እንድንጠብቀው የሚያደርገን ነው:: በለውጡ መባቻ ዘመን በኢትዮጵያ በአጠቃላይ የነበረው የምርት መጠን 300 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 600 ሚሊዮን ኩንታል ሊያድግ ችሏል:: በ2017 መጨረሻም ከ800 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚጠበቅ ሲሆን በ2018 የምርት ዘመን ወደ 1 ቢሊዮን ኩንታል እንደሚደርስ ይጠበቃል:: ይህም ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን እንድትችል ከማድረጉም በሻገር ስንዴ፤ ሩዝ እና የፍራፍሬ ምርቶችን በስፋት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም የሚፈጥርላት ይሆናል::
እንደ ግብርና ሥራው ሁሉ የኢትዮጵያን ነገ ከሚያሳምሩት ውስጥ በኃይል አቅርቦት በኩል የተሰራው ሥራ ነው:: በተለይም ደግሞ የዓባይ ግድብ የሥራ አፈጻጸም ነገን ቀና ብለን እንድንመለከት የተስፋ ወጋገን ያጎናጸፈን ነው:: የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ማሕተም ነው:: ሆኖም ይህ ግዙፍ ግድብ በነበረው የአሠራር እና የአመራር ብልሽት ወደ መስተጓጎሉ ደርሶ ነበር:: በኢሕአዴግ የመጨረሻ ዘመናት ጀምሮ ግድቡ ሲመራበት የነበረው ሂደት ለሙስና እና ብልሹ አሠራር ተጋልጦ የነበረ በመሆኑ በሂደት ግንባታው የሚቆምበት እድል የሰፋ ነበር::
ሆኖም እንደ ዕድል ሆኖ በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ እውን በመሆኑ የግድቡ ግንባታ ከመስተጓጎል ሊተርፍ ችሏል:: በአሁኑ ወቅትም የሲቪል ሥራው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራውም እየተፋጠነ ነው:: በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹትም ‹‹ዛሬ የሕዳሴ ግድብ ወደ ኋላ ከ205 እስከ 210 ኪሎ ሜትር ተኝቷል። ዛሬ የሕዳሴ ግድብ ወደታች ጥልቀቱ መቶ 133 ሜትር ደርሷል። ዛሬ ሕዳሴ ግድብ የጣናን ሀይቅ እጥፍ አድጓል። ጣና እስከ 30 ቢሊዮን ነው። ይሄ 62 ነጥብ አምስት ነው፤ ደብል አድርጓል። የጣና ውሃ ስፋቱ ብቻ ሳይሆን በጣም ሻሎው ነው። 13፣ 14 ሜትር ነው ጥልቀቱ። ይሄ 133 ገደማ ሜትር ጥልቀት አለው። በጣም ጥልቅ ነው ማለት ነው። ወደታችም ወደኋላም ወደጎንም በጣም ሰፊ ስለሆነ የጣናን እጥፍ/ደብል ውሃ ሆኗል።››ሲሉ የዓባይ ግድብ የደረሰበት ደረጃ አብራርተዋል:: ይህ ደግሞ የዓባይ ግድብ ዛሬን አድምቆ ነገን ብርሃን ፈንጥቆ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማወጅ መዘጋጀቱን የሚያመላክት ነው:: ይህም የአሁኑ ትውልድ ጀግንነቱን ካሳየባቸው ድሎች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ነው::
ሌላኛው ከዛሬ አልፎ የነገ ተስፋ የሆነን ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን እየሄደችበት ያለው መንገድ ፍሬ እያፈራ መምጣቱ ነው:: በኢትዮጵያ አዲስ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በትኩረት ከሰራባቸውና ለውጥ ካመጣባቸው ጉዳዮች አንዱ የባሕር በር ጥያቄ ነው:: መንግሥት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል:: ለ27 ዓመታት ያህል ፈርሶ የቆየውን የባሕር ኃይል እንደገና በማደራጀት ኢትዮጵያ እንደገና የባሕር ኃይል እንዲኖራት አድርጓል::
ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከ33 ዓመታት በኋላ የባሕር በር የምታገኝባቸው አማራጮች ሰፍተዋል:: የኢትዮጵያን ጥቅም ከማይሹ ከአንድ እና ሁለት ሀገራት በስተቀር ዛሬ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የሚጠራጠር ወይም የሚቃወም መንግሥት የለም:: ይህም በዲፕሎማሲዊ ጥረት የተገኘ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው::
ሌላኛው የነገን ተስፋ ብሩህ ከሚደርጉት ሀገራዊ ክንውኖች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የአረንጓዴ መርሃ ግብር ነው:: የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እየተተገበሩ ካሉ ፕሮጀክቶች አንዱ ሲሆን በየዓመቱም በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚሳተፍበት ሀገራዊ ንቅናቄ ለመሆን በቅቷል::
ሰሞኑን ይፋ በተደረገው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ሪፖርት እንደተመላከተው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2011 ዓመተ ምህረት ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ አሁን በ2016 ዓ.ም ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ብሏል። እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የተቻለው በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ30 ሚሊዮን ሰዎች በላይ የሚሳተፉበት የችግኝ ተከላ በአንድ ጀንበር የአረንጓዴ ሌጋሲ በሚሊዮን የሚጠጋ ብዛት ችግኝ ተከላ በመካሄዱ ጭምር ነው:: ባለፈው ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ኢትዮጵያን ማልበስ ተችሏል:: በቅርቡ ይፋ እንደተደረገውም ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ 94 በመቶ የሚደርሱት ችግኞች መጽደቅ ችለዋል::
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ፋይዳው ባሻገር ግብርና ምርታማነትን በመጨመር በምግብ ሰብል ራስን የመቻል ፍላጎትን ያፋጥናል:: ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችንም ያሳድጋል፤ የኢትዮጵያ ብልጽግናንም እውን እንዲሆን ያስችላል::
ከእነዚህ ግዙፍ ሥራዎች ጎን ለጎንም በቱሪዝም፤ በኮሪደር ልማት፤ በዲፕሎማሲ፤ ጠንካራ ሀገራዊ ሰራዊት በመገንባት እና በመሳሰሉት ዘርፎች እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ነገን በተስፋ አሻግረን እንድንመለከት የሚያደርጉን ናቸው:: ከወዲሁም ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ዛሬ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን በቅታለች:: ተጽዕኖ ፈጣሪነቷም እያደገ መጥቷል:: ይህ ደግሞ የዛሬው ትውልድ ሀያ አራት ሰዓት ሰርቶ፤ ላቡን አንጠፍጥፎ እና ወገቡን አጉብጦ ያስመዘገበው ድል ስለሆነ የዛሬው ትውልድ ጀግንነት መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው::
እኛ የዛሬ ትውልዶችም ልንቀስመው የሚገባ ትምህርት አለ:: ለሀገር ሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ውለታ የሚመለሰው የሰላምና የልማት አርበኛ መሆን ስንችል ነው:: በተለይም ሰላም ለራቃት ሀገራችን የሰላም አምባሳደር በመሆን የአባቶቻችንን መስዋዕትነት ከንቱ እንዳይሆን የበኩላችንን ጥረት ልናደርግ ይገባል::
የግጭት፡ የጦርነት፤ ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትጵያን ለማውረስ የጋራ ዕሳቤ የጨበጥን አዲስ ትውልድ መሆን ይገባናል::
በአባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎ ያገኘነው ኩራትና ነጻነታችን ሙሉ እንዲሆን ሀገሪቱን በልማት ማበልጸግ ያስፈልጋል:: ይህ ትውልድ ታላቁን የዓባይ ግድብ ሰርቶ እያገባደደ ነው:: ይህን የሀገር ኩራት የሆነ ግድብ አጠናቆ ለሀገር ብሎም ለአፍሪካ ብርሃን ማጎናጸፍ የዚህ ትውልድ አንዱ አደራ ነው::
በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ የተገኘውን አኩሪ እንቅስቃሴ ዘላቂ ማድረግና ከኢትዮጵያም አልፎ አፍሪካን መመገብ ሌላው የዚህ ትውልድ አሻራ ሊሆን ይገባል:: አረንጓዴ አሻራ በማኖር ረገድ ኢትዮጵያውን ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛሉ:: ይህ አኩሪ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት የማይወዱ አካላት ሊያጣጥሉት ቢሞክሩም ተግባሩ የሚደበቅ አይደለምና ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው መድረኮች ሁሉ በውጤታማነቱ እየተወሳ ይገኛል:: ስለዚህም ትውልዱ ይህንን አንጻበራቂ እንቅስቃሴ ከዳር ማድረስና ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን አረንግዴ ማልበስ ቀጣይ የቤት ስራው ሊሆን ይገባል::
በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል በዓድዋም ሆነ በሌሎች የጦር አውድማዎች የሀገርን ዳር ድንበር አላስደፍርም በማለት ደማቸውን በማፍሰስ፤ አጥንታቸውን በመከስከስ ውድ ሕይወታቸውን መስዋዕት ሲያደርጉ ኖረዋል:: የአሁኑ ትውልድም የሀገሩን ዳርድንበርና ሉአላዊነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን በሰላም እና በልማቱም መስክ ሀገሪቱን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚያስችሉ ተግባራትን በመፈጸም መስዋዕት የከፈሉ ቀደም አባቶችን ፈለግ ሊከተሉ ይገባል::
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2017 ዓ.ም