ከአፍሪካ ቀንድ ቀውስ ጀርባ ያሉ ስውር እጆች!

በዓለማችን መረጋጋት ከጠፋባቸው ቀጣናዎች መካከል አንዱ የአፍሪካ ቀንድ ነው፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያልቁባቸውን ጦርነቶች የሚያስተናግድ ቀጣና ነው። በዜጎች መብት ጥሰት ስማቸው በክፉ የሚነሱ ሀገራት መሪዎች መገኛ ከሆኑ አካባቢዎች መካከልም አንዱ የአፍሪካ ቀንድ ነው። ይህ ቀጣና ውጥረት የማያጣው በሀገራት ውስጣዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሀገራቱ መካከል የእርስ በርስ ግንኙነት መሻከር ከሚፈጠርባቸው አካባቢዎችም አንዱ ነው ሲል ቢቢሲ የዜና አውታር ይገልጸዋል፡፡

አልዓይን የዜና ወኪል በበኩሉ ቀጣናውን እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ፤ ሱዳን፤ ጅቡቲ እና ሶማሊያ የሚገኙበት ነው፡፡ ቀጣናው ለበርካታ አስርተ ዓመታት በአምባገነን ሥርዓት፣ በእርስ በርስ ግጭት እና የፈረሰ መንግሥት ያለበት በመሆኑ ይህን ክፍተት ለመሙላት በርካታ ታጣቂ ቡድኖች እና ቡድኖች የሚፈጠሩበት ነው።

የብሔር እና የሃይማኖት ክፍፍል በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ግጭት አባብሶታል። የአፍሪካ ቀንድ የተለያየ ቋንቋ እና ባሕል ያላቸው ጎሣዎች ይገኙበታል። እነዚህ ልዩነቶች ለፖለቲከኞች መጠቀሚያ ይሆናል። ወይም በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለመመጣጠን በሚባባሱበት ወቅት በጎሣዎች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ያደርጋሉ። የሃይማኖት ልዩነቶችም እንዲሁ በቀጣናው የግጭት ምንጭ እየሆነ ነው።

የፖለቲካ አለመረጋጋት በአፍሪካ ቀንድ ግጭት እንዲከሰት ከፍተኛ ሚና አለው። ደካማ የመንግሥት መዋቅር፣ ሙስና እና አካታች የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት አለመኖር ተቀናቃኞች እንዲፈጠሩ እና የሥልጣን ሽኩቻ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

የባሕር ላይ ውንብድና፤ የሽብር ድርጊቶች፤ የእርስ በርስ ጦርነቶች፤ መፈናቀል እና ስደት፤ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና የመሳሰሉት የአካባቢው መለያዎች እስከ መሆን ደርሰዋል፡፡

ከዚሁ የቀጣናው ባሕሪ ባሻገር በሌሎች ሀገራት የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች እና ግጭት አባባሽ ድርጊቶች ምክንያት ቀጣናው በማያባራ የሰላም እጦት ውስጥ እንዲቆይ አድርጎታል፡፡ በጣልቃ ገብነቶች እና በሴራዎች ምክንያት የአካባቢው ሀገራት በማያባራ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንዲዘልቁ የተፈረደባቸው ይመስላል፡፡

ለዚህ እንደማሳያ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት፤ ብልጭ ድርግም የሚለው የደቡብ ሱዳን ሰላም እና በሽብርተኝነት የምትናጠው ሶማሊያን ማንሳት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን ከህዳሴ ግድብ ጋር ጥያቄ አለን የሚሉ ሀገራት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጥምረት በመፍጠር ቡድኖችን በማስታጠቅ ሀገሪቱን ለማወክ የሚደረጉ ሴራዎች ሀገሪቱን ፈተና ውስጥ መክተቱ አልቀረም፡፡

በጣልቃ ገቦች ምክንያት ሱዳን በማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች፡፡ የሱዳንን መደበኛ ጦር በሚመሩት ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃንና የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉን በሚመሩት ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) መካከል በተነሳ አለመግባባት የተቀሰቀሰው ጦርነት በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት በማስከተል ላይ ይገኛል፡፡ ሦስት ዓመታት ሊሞላው በተቃረበው በዚሁ ግጭት ምክንያት በርካቶች ከመሞታቸውም ባሻገር፤ ወደ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ እንደተፈናቀለና ከእነዚህ ውስጥ 1ሚሊዮን የሚሆኑት ሀገር ጥለው መሰደዳቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በጦርነቱ ሳቢያ የመኖሪያ አካባቢዎች ዒላማ በመሆናቸው በርካታ ንጹሐን ዜጎች በእጅጉ የተጎዱ ሲሆን ሆስፒታሎችን ጨምሮ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችም ወድመዋል። የተለያዩ ሰብዓዊ ርዳታዎችም ለተጎጂ ወገኖች ማድረስ በእጅጉ ፈታኝ ሆኗል፡፡

ይህ ግጭት እንዲያበቃ በርካታ ጥረቶች ቢደረጉም አንዳችም ተጨባጭ ውጤት ሳያመጣ ጦርነቱ ዛሬ ድረስ ዘልቋል፡፡ ይህ ደግሞ በዋነኝነት ቀጣናውን ለማመስ ፍላጎት ባላቸውና ዘወትር በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ከመግባት በማይቆጠቡ የጎረቤት ሀገራት ጣልቃ ገብነት የተነሳ ነው፡፡

በተመሳሳይም ደቡብ ሱዳን በሳልቫኪር እና በሪክ ማቻር ደጋፊዎች መካከል በሚነሳ አለመግባባት የውጭ ረጃጅም እጆች ታክለውበት ሁኔታውን አባብሶታል፡፡ በሽብርተኝነት የምትናጠውም ሶማሊያ ያለመረጋጋቷ ምንጭ ሌላ ሳይሆን ከሰሜን አፍሪካ ድረስ መጥተው አካባቢውን ማመስ በሚፈልጉ ሀገራት ጣልቃ ገብነት የሚፈጠር ነው፡፡ እነዚህ የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ከጎረቤት አምባገነን መንግሥታት ጋር በማበር የአፍሪካ ቀንድን ሲዖል ለማድረግ ተኝተው አያድሩም፡፡

በጎረቤት ሀገራት የሚነሱ አለመግባባቶች ቶሎ እንዲፈቱና ሀገራቱ በፍጥነት ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለችው ሚና መተኪያ የሌለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ማግስት ጀምሮ በሱዳን፤ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ወደ ግጭት የገቡ ኃይሎችን በመሸምገል ውጤታማ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡

ግጭት ባልቆመባቸው በሱዳን የአብዬ ግዛትና በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ኢትዮጵያ ለአባል ሀገራቱ ጥላና ከለላ መሆን ችላለች፡፡ በቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን ወደ ሰላም ለመመለስም በብቸኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመጀመሪያው ትኩረት የጎረቤት ሀገራት በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከየትኛውም ዓለም አቀፋዊም ሆነ አሕጉራዊ ጉዳዮች በበለጠ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ ትኩረት ትሰጣለች። ይህንኑ መነሻ በማድረግም ግጭት እና ሁከት ውስጥ የሚገኙትን ሶማሊያ፤ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በመሪዎች መካከል ተደጋጋሚ ውይይት እንዲደረግ ኃላፊነትን በመውሰድና አልፎ ተርፎም የሰላም አስከባሪ በመላክ ሀገራቱ አንጻራዊ ሰላም እንዲኖራቸው አበክራ በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡

ሶማሊያ መንግሥት አልባ ሆና ለዘመናት ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ ባደረገችው ጥረት እኤአ ከ2008 ጀምሮ ሶማሊያ መንግሥት መሥርታ አንጻራዊ ሰላም አግኝታ ቆይታለች፡፡ ለሶማሊያ መረጋጋትና የሶማሊያን ሕዝብ ለመታደግ ሲባልም ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን አጥታለች፡፡

ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ እምብርትና የስበት ማዕከል ናት፡፡ ሀገሪቱ ሁሉንም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች በማዕከልነት የምታማክል እና ከሁሉም የቀጣናው ሀገራት ጋር የጋራ ድንበር ያላት ብቸኛ ሀገር ነች፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላት አቀማመጥ፤ የሕዝብ ብዛት፤ እያደገ ያለ ኢኮኖሚዋ ትኩረት የምትስብ እና የምትፈለግ ሀገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡

ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትስስሮሽ በሚፈጥሩ የጋራ በሆኑ የባቡር፣ የመንገድና የወደብ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ለቀጣናው የኃይል አቅርቦት ዋና ምንጭ በመሆን ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረገች ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከ13 ዓመታት በፊት የጀመረችው ታላቁ የዓባይ ግድብ ከ97 በመቶ በላይ ተጠናቋል። ግድቡ ከወዲሁ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የኃይል ምንጭ በመሆን ምሥራቅ አፍሪካን በማስተሳሰር ላይ ይገኛል፡፡ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ የቀጣናውን ሀገራት በኃይል በማስተሳሰር የጋራ ኢኮኖሚ እንዲገነቡ በር የሚከፍት ይሆናል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራትም ወደ ጎረቤት ሀገራት ከላከችው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ61 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷ የቀጣናዊ ትስስሩ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ለጎረቤት ሀገራት በተለይም ለጅቡቲ በመላክ ቀጣናዊ ትስስሮሽን በማጎልበት ላይ ትገኛለች፡፡ ከ258 ኪ.ሜ በላይ የውሃ መስመር ዝርጋታ በማከናወን ኢትዮጵያ በየቀኑ ለጅቡቲ እያቀረበች ያለችውን ከ20ሺህ እስከ 30ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ወደ 100 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር የንጹሕ መጠጥ ውሃ ለማሳደግ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ይህም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿን ጭምር በመስጠት ቀጣናዊ ትስስሩን ለማጠናከር እየሠራች መሆኑን አመላካች ነው፡፡

በግብርናው ዘርፍም ቀጣናዊ ትስስሩን የማጠናከር ሥራ በስኬታማነት በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ ስንዴ ምርት ነው። ኢትዮጵያ ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ስንዴ ላኪነት እራሷን በመለወጥ ታሪክ ሠርታለች፤ ለቀጣናው ሀገራትም ኩራት ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያ ባለፈው የምርት ዘመን 129 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የስንዴ ምርት አምርታለች፡፡ 97 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ሲሆን 32 ሚሊዮን የሚጠጋው ወደ ውጭ መላክ ችላለች፡፡ ይህም ጥረቷም በምግብ እጥረት ለሚሰቃየው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና መድኅን እንድትሆን የሚያስችላት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ስንዴ አምራች መሆን ችላለች፡፡ በዚህም ስንዴን ለመግዛት የሚፈልጉ ሀገራት ቁጥር በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ስድስት ሀገራት ጋር የ3 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት ተፈራርማለች። ይህ ኢትዮጵያ ከኃይል አቅርቦት ባሻገር በምግብ ሰብልም የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናን በማስተሳሰር በኩል ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን አመላካች ነው፡፡

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ሚና በአግባቡ ለመወጣትም ነፃ የንግድ ቀጣና በድሬዳዋ መሥርታለች፡፡ ይህ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ደረቅ ወደብን ከዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት፣ ከባቡርና ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት፣ ምርቶችን በቀላሉ ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመላክ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናን /AfCFTA/ በማጠናከር ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች፡፡ በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሻነት የተመሠረተው አሕጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ካሉት መርሆዎች ውስጥ “የአንድን ሀገር ምርት ከሌላው ሀገር ምርት ጋር እኩል ማስተናገድ”፣ “የሀገር ውስጥ ምርትን ከአባል ሀገራቱ ከሚገቡ ምርቶች ጋር እኩል ማስተናገድ” የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በዚህ መሠረትም ለሀገራችን ኢንዱስትሪዎች እና የንግድ ማኅበረሰብ አካላት ምርቶቻቸውን በሀገር ውስጥም በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም እኩል የመወዳደር ዕድል ከመስጠቱም ባሻገር ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በጋራ የመነገድን ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡

በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ከማምጣት አኳያ ኢትዮጵያ እየተጫወተችው ያለው ሚና መተኪያ የሌለው ነው፡፡ በተለይም የቀጣናው ዋነኛ ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነትን በመዋጋት የሚስተካከላት የለም፡፡

አልሻባብ ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ዋናው የደም መፋሰስና የሞት ምንጭ ነው፡፡ ቡድኑ ከአልቃኢዳ ጋር ባለው ኅብረትም ለቀጣናው ብቻም ሳይሆን ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ዋና ስጋት ከሚባሉ ሽብር ቡድኖች አንዱ ነው፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ይህንን የሽብር ቡድን እገባበት እየገቡ የሽብር ውጥኑን ሲያመክኑ ቆይተዋል፡፡

ሽብርተኝነትን ከመዋጋት ጎን ለጎን ኢትዮጵያ በማንም ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባትና ለዓለም አቀፋዊ ሰላምና ደኅንነት በጋራ የመቆም የጥንት የውጪ ግንኙነት ፖሊሲዋን በማስቀደም ዲፕሎማሲዋን ስትመራ የቆየች ሀገር ነች፡፡ ሆኖም የቀጣናው ሀገራት በችግር ውስጥ በወደቁበት ወቅት ቀድሞ በመገኘት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ሀገራቱ እንዲረጋጉ እና ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የማይነጥፍ ድጋፍ የምታደርግ ሀገር ነች፡፡

ከዚህ አንጻር ግጭት ባልቆመባቸው በሱዳን የአብዬ ግዛትና በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይልን በመላክ ኢትዮጵያ ለአባል ሀገራቱ ጥላና ከለላ መሆን ችላለች። በቀውስ ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን ወደ ሰላም ለመመለስም በብቸኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡

በተለይም ደግሞ ላለፉት 17 ዓመታት የሰላም አስከባሪ ኃይሏን ጭምር በመላክ መንግሥት አልባ ሆና የቆየችውን ሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት እንድትመሠርት እና አንጻራዊ መረጋጋት እንዲኖራት የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ቀጣናዊ ግዴታዋን ተወጥታለች፡፡

ሆኖም አንዳንድ የቀጣናው ሀገራት አለፍ ሲልም የሀገራትን ድንበር ተሻግረው የሚመጡ ሀገራት ቀጣናውን ለማወክ እና ያልተረጋጋ አካባቢን ለመፍጠር ሌት ተቀን ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ በተለያዩ ሀገራት ውስጥ በተለይም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጭምር በመግባት ሰላም እና መረጋጋት የራቃት ሀገር እንድትሆን ሌት ተቀን ያለመታከት የሚሠሩ የቅርብ እና የሩቅ ሀገራት አሉ፡፡

እነዚህ ሀገራት ታጣቂዎችን በማሠልጠን፤ በማስታጠቅ እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ኢትዮጵያ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትዳክር እና አለፍ ሲል ቀጣናዊ ሚናዋን እንዳትወጣ የበኩላቸውን አሉታዊ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሆኖም ኢትዮጵያ እነዚህ ሁሉ ጫናዎችን በመቋቋም የሀገር ውስጥ ሰላሟን እያረጋገጠች፤ በልማት ጎዳና እየተጓዘች እና አልፎ ተርፎም ለቀጣናው ሰላም እና እድገት ቁልፍ ሚና እየተጫወተች የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ትገኛለች፡፡

አሊ ሴሮ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You