ዘላቂ የምርት ዕድገት ለማስመዝገብ የአርሶ አደሩን ክህሎት ማጎልበት እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡- ዘላቂ የምርት ዕድገት ለማስመዝገብ የአርሶ አደሩን እውቀት ማጎልበት ክህሎት ማዳበር እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሦስተኛው የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ውይይት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ በክልሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አተገባበር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ጥሩ ጅማሮ ታይተዋል፡፡እነዚህን ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎችና ዘላቂ የምርት ዕድገት ለማስመዝገብ የአርሶ አደሩን እውቀት ለማጎልበት ክህሎት ለማዳበር አሁንም በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ በግብርና የሚተዳደር እንደመሆኑ ዘርፉ ላይ ከእዚህም በላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዕቅድ አተገባበሩ ላይም በየክላስተሩ የተሠሩ ሥራዎችን መገምገም ፣ የታዩ ክፍተቶች እንዲሻሻሉ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ አንዱ ቁልፍ ጉዳይ እውቀትን ማጎልበት እና ክህሎትን ማዳበር መሆኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ፤ ከእዚህ አኳያም የአርሶ አደሩን፣ የግብርና ባለሙያዎችን እውቀታቸውን ማዳበርና ክህሎታቸውን ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ክልሉ ምክር ቤቱን በመቋቋም ጥናት አድርጎና ፎኖተ ካርታ አስቀምጦ ወደ ሥራ መግባት የሚደነቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ባስቀመጠው ፍኖተ ካርታ መሠረትም ተለይተው የተቀመጡ ዘርፎች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ሁሉም የምክር ቤቱ አባላትና የዞን አስተዳዳሪዎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ተቀራርበው በመሥራት እንደ ችግር የሚነሱ ክፍተቶችን መቅረፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ የግብርና ግብዓቶች አጠቃቀም ላይ መሻሻል እንዲኖር ፣የአፈር ጤናማነትን ለመጠበቅ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም እንደ መፍትሔ የተነሱ መሆናቸውን አመልክተው፤ በኩታ ገጠም (በክላስተር) ማረስ መበረታታት የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል፡፡የኩታ ገጠም እርሻ የሚበረታታው በምርት ሂደት ብቻ ሳይሆን ወደ ገበያ እስከሚሰራጭበት ድረስ ሥርዓቱ መቀጠል እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የምርት አያያዝ ለብክነት የተጋለጠ በመሆኑ፤ ይህንን በማሻሻል ረገድ ምክር ቤቱ በትኩረት ሊሠራበት ይገባል፡፡ ከሰብል ጥበቃ ጋር በተያያዘ ከምርት በኋላ በተለያዩ ተባዮች የሚጠቁ ምርትና ሰብሎችን አስቀድሞ ለመከላከል የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ማሻሻልና ዘመናዊ ማድረግ ይገባል፡፡

በመድረኩም በግብርና ትራንስፎርሜሽን የታየው ለውጥ፣ ያስገኛቸው ውጤቶች እና በትኩረት መሠራት ያለባቸው ዘርፎች ላይ የተደረገ ጥናት በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ቀርቧል። ጥናቱን ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ የጥናት ቡድን መሪ አቶ አማኑኤል፤ በዘርፉ የተለዩ የግብርና እሴት ሰንሰለትን የሚሸፍኑ ቴክኖሎጂ ፣ የመስኖ አጠቃቀም ፣ ሜካናይዜሽን፣ ኤክስቴንሽን ፣ ፋይናንስ ፣ የንግድ ሥርዓት ፣ የተፈጥሮ ሀብት እና እነዚህን የተለዩ ዘርፎች ማብቃት የሚያስችል ጥናት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ የግብርና ምርትና ምርታማነትን መጨመር፣ የአርሶ አደሩን ገቢ ማሳደግ እና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲሁም ለአግሮ ኢንዱስትሪ እና ለውጭ ገበያ የሚደርጉትን አስተዋጽኦ ማሳደግ ዋና ዓላማው በማድረግ ስኬቶችን እና መሻሻል የሚገባቸውን ዘርፎች ለይቶ አስቀምጧል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You