የውጤታማነት ፈተና የገጠመው የትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በቻይና ምርቶች ላይ የጣለውን ከፍተኛ የታሪፍ ክፍያ ለመቀነስ እያሰበ እንደሆነ “ዎል ስትሪት ጆርናል” ጋዜጣ የዋይት ሃውስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል። በዘገባው መሰረት፣ አስተዳደሩ በቻይና ላይ የተጣለውን የ145 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ከ50 እስከ 65 በመቶ ዝቅ ሊያደርገው አቅዷል፡፡

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት በትራምፕ አስተዳደር ሊደረግ የታቀደው የታሪፍ ቅነሳ ምን ያህል እንደሆነ ባይጠቅሱም፣ ቅናሽ ሊደረግ መታሰቡ የሚያስገርም እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ሁለቱም ሀገራት አሁን ያለው የታሪፍ ምጣኔ ከፍተኛ እንደሆነ እንደሚገነዘቡ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ “መደበኛ የንግድ ድርድሮች ከመጀመራቸው በፊት ስክነት ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ ድርድር መቼ እንደሚጀመር እርግጠኛ ሆነው መናገር እንደማይችሉም ቤሰንት ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደራቸው ስላቀደው የታሪፍ ማሻሻያ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፤ በቻይና ምርቶች ላይ የጣሉትን ከፍተኛ ታሪፍ ለመቀነስ እቅድ  እንዳላቸው ገልጸው፤ የታሪፍ ቅነሳው ተግባራዊነት የሚወሰነው ቻይና በምትወስዳቸው ርምጃዎችና በሚደረጉ የንግድ ድርድሮች ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በቀጣዮቹ ሳምንታት ቻይናን ጨምሮ ለሌሎች የአሜሪካ የንግድ አጋሮች አዲስ የታሪፍ ምጣኔ ይፋ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ ይህም አሜሪካ ከሀገራቱ ጋር በምታደርገው የንግድ ድርድር ውጤት ላይ የሚመሰረት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

“ከንግድ አጋሮቻችን ጋር ጥሩ ስምምነቶችን የምናደርግ ይመስለኛል፡፡ ከቻይና ጋር ንግግሮችን እያደረግን ነው፡፡ ፍትሐዊ የንግድ ልውውጥ ይኖረናል” ብለዋል፡፡

ይህ የፕሬዚዳንቱ ንግግር የተሰማው ከሦስት ሳምንታት በፊት ይፋ ያደረጉትን የታሪፍ ጭማሪ በድጋሚ በማስተካከል ሊቀንሱ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ከገለጹ ከሰዓታት በኋላ ነው፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከቀናት በፊት ባደረጉት ንግግር፣ በቻይና ላይ የተጣለው የ145 በመቶ ታሪፍ ከፍተኛ እንደሆነ በይፋ የተናገሩ ሲሆን፤ የታሪፍ ምጣኔው ዝቅ ሊል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተውም እንደነበር ይታወሳል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአሜሪካ የንግድ አጋሮች፣ በተለይም በቻይና ላይ የጣሉትን የታሪፍ ምጣኔ በድጋሚ ለማስተካከል ፍላጎት ማሳየታቸው ከሣምንታት በፊት የወሰዱት ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ ርምጃ ውጤታማነቱ ጥያቄ እንዲነሳበት እያደረገ ነው።

በተለይም ቻይናና አሜሪካ ካላቸው ግዙፍ የንግድ ልውውጥ አንፃር የታሪፍ ውሳኔው የሀገራቱን ንግድ ሊጎዳው እንደሚችል በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር፡፡

ባለፈው ዓመት አሜሪካ የ438 ቢሊዮን ዶላር ምርት ከቻይና ያስገባች ሲሆን፤ ቻይና ደግሞ 143 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ከአሜሪካ ሸምታለች፡፡ በእዚህም አሜሪካ ከቻይና ጋር በምታደርገው የንግድ ልውውጥ የ295 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ጉድለት ገጥሟታል።

አሜሪካ ከቻይና የምታስገባቸውን ምርቶች ከሌሎች ሀገራት በአጭር ጊዜ ለመተካት መቸገሯ አይቀርም፡፡ ቻይናም ብትሆን ለምጣኔ ሀብቷ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የውጭ ንግዷ በታሪፍ ጫና ውስጥ ሲወድቅ ቀላል የማይባል ፈተና እንደሚገጥማት ግልጽ ነው፡፡

በሌላ በኩል 12 የአሜሪካ ግዛቶች ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያለኮንግረሱ ፈቃድ ታሪፍ መጣል አይችሉም ብለው ኒው ዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት ክስ መስርተዋል። ግዛቶቹ ባቀረቡት ክስ “ትራምፕ የአሜሪካን ምጣኔ ሀብት ለቀውስ እያጋለጡት ነው” ብለዋል፡፡

ክሱን ካቀረቡት ግዛቶች መካከል አንዷ የሆነችው የአሪዞና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ክሪስ ሜይስ ባወጡት መግለጫ፤ “የፕሬዚዳንቱ የታሪፍ ውሳኔ ምጣኔ ሀብታዊ ግዴለሽነት ብቻ ሳይሆን ሕገወጥ ተግባርም ጭምር ነው” ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፕሬዚዳንት ትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ርምጃ በአሜሪካ ኢኮኖሚ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ረቡዕ ዕለት አስታውቋል፡፡

የፕሬዚዳንቱ ርምጃ በመላው ዓለም የምጣኔ ሀብት እድገት እንደሚቀንስና የብድር ጫናን እንደሚጨምር የገለጸው ድርጅቱ፤ ርምጃው በ2025 የአሜሪካ ኢኮኖሚ እድገት ከአንድ ነጥብ ስምንት በመቶ ያልበለጠ እንዲሆን ሊያደርገው እንደሚችል ተንብዮአል፡፡ ይህም ድርጅቱ ቀደም ሲል ይዞት ከነበረው የሁለት ነጥብ ሰባት በመቶ ትንበያ በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡

ከእዚህ በተጨማሪም የታሪፍ ውሳኔው አጠቃላይ የዓለም የምጣኔ ሀብት እድገትን ቀድሞ ተገምቶ ከነበረው ሦስት ነጥብ ሦስት በመቶ ወደ ሁለት ነጥብ ስምንት በመቶ ዝቅ ሊያደርገው እንደሚችልም የድርጅቱ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ምጣኔ ሀብታዊና ሕጋዊ ጫናዎች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሳምንታት በፊት የጣሉትን ከፍተኛ ታሪፍ በድጋሜ ለማጤን እንዳስገደዷቸው በይፋ የተገለፀ ነገር ባይኖርም፣ ትራምፕ ግን የታሪፍ ምጣኔውን የመከለሱ እቅድ የታሰበው ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በእርግጥ ቻይና የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ደጋግማ የኮነነችና እስከመጨረሻው ድረስ እንደምትፋለም የገለፀች ሲሆን፣ ከአሜሪካ ለተጣለባት 145 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ፣ በአሜሪካ ምርቶች ላይ 125 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ በማድረግ የአፀፋ ምላሽ መስጠቷ ይታወቃል፡፡

‹‹መዝገበ ቃላት ውስጥ ካሉ ቃላት መካከል በጣም የምወደውና ደስ የሚያሰኘኝ ‹ታሪፍ (Tariff )› የሚለው ቃል ነው›› ብለው የተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ የታሪፍ ጭማሪ የአሜሪካን አምራች ኢንዱስትሪ ለመጠበቅና ምርትን ለማሳደግ ይጠቅማል ብለው ያምናሉ፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ግን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በየጊዜው ይፋ የሚያደርጓቸው የታሪፍ ጭማሪዎች ለዋጋ ንረት፣ ለምጣኔ ሀብት መዳከምና ለዓለም አቀፍ የንግድ ጦርነት እንደሚያስከትሉ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል፡፡ እንደባለሙያዎቹ ማብራሪያ፣ የታሪፍ ጭማሪው ለአሜሪካውያን ሸማቾች የምርቶች ዋጋ እንዲንር ያደርጋል፤በሌሎች ሀገራትም የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ይፈጥራል፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You