በአገሪቱ ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ ፍትሃዊ የንግድ ሥርዓቱን እያዛባ መሆኑን ይጠቀሳል፡፡ የታክስ አስተዳደሩንም ቢሆን ይኸው ህገወጥ ተግባር እየተፈታተነ ከመሆኑም ባሻገር ለማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ መነሻ እየሆነ ይገኛል፡፡ በተለይ በህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ ሥራ ላይ የሚሳተፈው ህገወጥ ኃይል እየጨመረ መምጣቱና በህገወጦች ላይ ተመጠጣኝ እርምጃ እየተወሰደ ያለመሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ 3 ነጥብ 16 ቢሊዮን ብር የሚገመት ዕቃ ከውጭ በኮንትሮባንድ ገብቷል፤ ከአሀገር ውስጥ ደግሞ 537 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ዕቃዎች ሊወጡ ሲሉ በመቆጣጠሪያ ጣቢያዎችና ኬላዎች ተይዘዋል፤ 1 ቢሊዮን 586 ሚሊዮን 507ሺ544 ዕቃዎች ወደ በኮንትሮባንድ መልክ ገብተዋል፤ በዚህም 14 ቢሊዮን 398 ሚሊዮን 575ሺ279 ብር ቀረጥና ታክስ ሳይሰበሰብ ቀርቷል፡፡
ከሰሞኑ በሐዋሳ ከተማ የገቢዎች ሚኒስቴር በኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ዙሪያ ከመላው አገሪቱ ከመጡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በመድረኩ የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ « የኮንትሮባንድ ንግድ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እያሳረፈ ያለው አሉታዊ ጫና በአጭሩ ካልተቀጨ መወጣት ከማይቻልበት አዘቅት ውስጥ ይከተናል» ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በህገወጥ መንገድ እየገባም ሆነ እየወጣ ያለው ምርት መጠን በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ የንግድ ሥርዓቱንና የታክስ አስተዳደሩ በማዛባት ኢኮኖሚውን እያናጋ ይገኛል፡፡ በተለይም መንግሥት ከህጋዊ ንግዱ ማግኘት የነበረበትን ቀረጥና ታክስ እንዲያጣ ያደረገ ከመሆኑም ባሻገር የሀገር ውስጥ ገበያን እንዳይረጋጋ በማድረግም ህጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ ውጭ እንዲወጡ አስገድዷቸዋል፡፡
« ህገወጥ ንግዱ ጥቁር ገበያን በማስፋፋት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በመፍጠር የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን እያዳከመ ይገኛል» ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ባለሀብቶቹ በሀገር ውስጥ ያመረቱትን ምርት ገበያ በመሻማት አጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱን ፍትሐዊነት እንዲያጣ ማድረጉን፣ መንግሥታዊ አሠራር በሙስና እንዲዘፈቅና ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዳይነግስ እንቅፋት መፍጠሩን ይጠቅሳሉ፡፡
በኮንትሮባንድ የገቡ ዕቃዎች የግብይት ደረሰኝ ስለማይቆረጥላቸው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሰብሰብ እንዳይችል በማድርግ አሉታዊ ሚና እያሳረፈ ስለመሆኑ አቶ ዘመዴ ይናገራሉ፡፡ይህም ህገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ነው የሚገልፁት፡፡ «በአጠቃላይ ኮንትሮባንድ ህጋዊ የንግድ ሥርዓቱን በማሽመድመድ ኢንቨስትመንትን እያዳከመ የውጭ ምንዛሬ ገበያን እያዛባና መንግሥት ከዘርፉ መሰብሰብ የሚገባውን ገቢ በማሳጣት የሀገር ልማትና ዕድገት ላይ እንቅፋት ሆኗል» በማለት ያስረዳሉ፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ ወደ አገሪቱ የሚገቡ መጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ መድኃኒቶችና ምግብ ነክ ሸቀጣ ሸቀጦች እንዲሁም ሀሺሽና ልዩ ልዩ አደንዛዥ ዕፆች በመሆናቸው በህዝቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም አገር የሚገነባውን ወጣት ጤና፣ ጉልበትና አዕምሮ በመስለብ እንዲዳከም እያደረገ ሲሆን፤ ለወንጀል ድርጊትም የሚገፋፋበት ዕድልም ሰፊ ነው፡፡ ዜጎችን ገበያ በማሳጣት ከአምራችነትና ከሥራ ፈጣሪነት ጎራ አስወጥቶ ሥራ አጥ እንዲሆኑ በማድረግ ለአስከፊ ማህበራዊ ቀውስ እየዳረገ ነው ፡፡
በዚሁ ኢኮኖሚያዊ ውንብድና ምክንያት የግልፅነትና የተጠያቂነት አሠራር እንዳይሰፍን በማድረግ ሲቪል ሰርቪሱ በሕግ የተሰጠውን ተግባር በአግባቡ እንዳይወጣ ከፍተኛ እንቅፋት መሆኑንም አቶ ዘመዴ ሲያስረዱ «ከሌሎች አገራት ተሞክሮ እንደምንረዳው ኮንትሮባንድ አሸባሪነትን በገንዘብ በመደገፍ አካባቢን፣ አገርና አህጉን የማተራመስ ሚና ይጫወታል፤ ለዕርስ በዕርስ ግጭት ምክንያት ይሆናል፤ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን ይፈጥራል፡፡ በኢትዮጵያም ህገወጥነትን የሚያብሱ አሠራሮች በመስፋታቸው ምክንያት ሁኔታ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ባሻገር የደህንነት ሥጋት እየሆነ መጥቷል » ብለዋል፡፡
አቶ ዘመዴ « ከመሃል አገር ለሚርቁና የመሰረተ ልማት ለማይደርስባቸው ጠረፍ አካባቢ ላሉ ማህበረሰቦች የዕለት ፍጆታ ዕቃዎችና ባህላዊ አልባሳት በቀላሉ እንዲያገኙ ታስቦ በህግ የተፈቀደው የፍራንኮቫሉታ መብት ከታለመለት አላማ ውጭ የመዋል ችግር እንደሚታይ፣ ለጠረፍ አካባቢ ማህበረሰብ የማይደርሰውና መዳረሻቸው መሃል አገር ብቻ የማድረግ ሁኔታ ላይ የአመራር አካላት እጅ ያለበት መሆኑ የአገር ውስጥ ምርትና ኢንቨስትመንትን እያደናቀፈ ነው፤ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ2018 አጋማሽ ድረስ ከ14 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ከቀረጥ ነፃ ሸቀጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ይህም ለጥቂት ግለሰቦች ማበልፀጊያ እየሆነ መምጣቱን ያመላክታል» ብለዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ ከውጭ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በየዓመቱ በአማካኝ በ3 ነጥብ 82 በመቶ ቅናሽ እያሳየ ነው፡፡ ወደ ውጭ የተላኩ ዕቃዎች መጠን በየዓመቱ በአመካኝ 5 ነጥብ 35 በመቶ ጭማሬ ብቻ ነው እያሳየ ያለው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች በኮንትሮባንድ እየተንቀሳቀሱ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው ዕቃዎች በህጋዊ መልኩ ወደ ውጭ እንዲላኩ የሚደረግበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
«በተለይም የቁም እንስሳት፣ ጫትና የቅባት እህሎች በወጪ ንግዱ እየቀነሱ የመጡ ሲሆን፤ በአንፃሩ በሕገወጥ መልኩ ሲወጡ የሚያዙ የወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች ከፍተኛ ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ማዕድናት በተለይም የወርቅ ንግድ ከፍተኛ ማሽቆልቆል እያሳየ ከመሆኑም በላይ በሕገወጥ መልኩ የሚንቀሳቀሰውም ተገቢው ቁጥጥር እየተደረገበት ባለመሆኑ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል ይላሉ አቶ ዘመዴነህ፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴርና ጉምሩክ ከተልዕኮአቸው አንዱ ኮንትሮባንድ ዝውውርን፣ የታክስ ማጭበርበርንና ስወራን በመከላከልና በመቆጣጠር የታክስና የጉምሩክ ህግጋትን ማስከበር ነው፡፡ ተልዕኮውን ለመወጣት በስሩ ባሉ ሁሉም ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን በመሥራት የገቢና የወጪ ኮንትሮባንድ ፍሰት አቅጣጫዎችን በመሥራት ላይ መሆኑን የሚገልፁት አቶ ዘመዴ፤ የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድና ፍሰት አቅጣጫዎችን አጥንቶ በመለየት በየደረጃው ያሉትን ፀረ ኮንትሮባንድ ድርጊቶች ለመከላከል አደረጃጀቶችን የማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
የመቅረጫና የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን አደረጃጀት የማስተካከል፣ አመራሩን እንደገና የመመደብና ኬላዎችን መልሶ ለማደረጃት የሚያስችል ጥናት ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሥራት ረገድ ግን ብዙ የሚቀር መሆኑን አቶ ዘመዴ አልሸሸጉም፡፡
«የሚደገው የቁጥጥር ሥራ ዋና ኮንትሮባንድ ላይ ከማተኮር ይልቅ ትናንሽ ቋጠሮዎች ላይ ማተኮር ያመዝናል» የሚሉት አቶ ዘመዴ፤ የሚደረጉት ጥረቶችም ችግሩን ከመሰረቱ የሚቀርፉ አለመሆናቸውና የባለድርሻ አካላት ቅንጅትም ጉድለት ያለበት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ የአቅምና የሎጅስቲክ፣ የአመራር ስምሪት ፣ የአሰራር ክፍተት፣ የኬላዎች ጥናትን ወደ ተግባር ማሻገር አለመቻል በዘርፉ ከሚታዩ ችግሮች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ነው የሚያመለክቱት፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በማቋቀሚያ አዋጅ ቁጥር 587/2000አንቀፅ 18 እና ጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006አንቀፅ 151 መሰረት የፌዴራል ፖሊስ የጉምሩክና ታክስ ህጎችን በመተላለፍ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያስችል የፖሊስ ኃይል የማደራጀትና የማሰማራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይሁንና ራሱን የቻለ የጉምሩክ ፖሊስ አደራጅቶ የመከላከል ሥራውን በባለቤትነት አለመያዝና በተወሰኑ ኬላዎች የሰው ኃይል ያለመመደብ ሁኔታ በስፋት ይታያል፡፡ አልፎ አልፎ ከበላይ አካል ትዕዛዝ ካልመጣ በሚል ሥራን ማጓተት፣ ታች ላይ ሥራውን የሚያከናውኑ ሠራተኞች እንደራስ ሥራ አድርጎ አለመውሰድ፣ ተጠርጣሪ ለሚመለከተው የሕግ አካል ከማስተላለፍ ይልቅ ለጉምሩክ ሠራተኛ ተቀበሉን የማለትና የመልቀቅ ሁኔታ በመኖሩ ውንብድናው እንዲባባስ በኮንትሮባንድ የከበረውን ሕገወጥ ነጋዴ እያበረታታ ይገኛል፡፡
ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ተወክለው በመድረኩ የተሳተፉ አካላት በበኩላቸው እንዳስረዱት፤ በየደረጃውያሉ የመስተዳደር አካላት በቅንጅት ለመሥራት ፍቃደኛ ያለመሆናቸውና በቁርጠኝነትና በባለቤትነት ያለመሥራት ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ አመራሮች በኮንትሮባንድ ንግዱ ተዋናይ የመሆንና አገራዊ ጉዳቱን አለመረዳት እንደሚስተዋልም ያነሳሉ፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የኮንትሮባንድ ንግዱን የኑሮ መደጎሚያ አድርጎ የመመልከትና እርምጃ አለመውሰድ ኮንትሮባንድ እንዳይያዝ እንቅፋት የመሆንና የፖሊስ ሥራ ብቻ አድርጎ የመመልከት የአደረጃጀትና የቅንጅት ችግር መኖሩንም ነው ተሳታፊዎቹ ያመለከቱት፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለፃ ፤ በአራቱም በሮች በግልፅና በጠራራ ጸሐይ ኮንትሮባንድ ሲገባና ሲወጣ ሃይ ባይ የለም፡፡
ኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተይዘው አስተላላፊው አካል የማይያዝበትና በነፃ የለቀቀው አካልም የሚጠየቅበት አሠራር አይስተዋልም፡፡ በተለይም ደግሞ ለአገር ደህንነት ሥጋት እየሆነ የመጣውን የህገወጥ መሣሪያ ዝውውር ጉዳይ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው በየደረጃው ያለው አመራር አካል ነው፡፡ በዋናነት የፍትህ አካላት ትዕዛዝ አልተሰጠንም በሚል ህገወጥ ዕቃዎች ሲገቡ ቸል የሚሉበት አጋጣሚ አለ፡፡ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ይከፈል የነበረው የፖሊስ ወሮታ በመቆሙ ምክንያት የቸልተኝነት ችግር ተባብሷል፡፡ በሌላ በኩልም በየደረጃው ያለው አመራር በየፍተሻ ጣቢያው የሚያዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ህጋዊነት አላብሶ እንዲተላለፍ የማድረግ ዝንባሌ እንደሚታይባቸው ተሳታፊዎቹ ያነሳሉ፡፡
ይህም በስልክ ጭምር ጫና በመፍጠር ባለሥልጣናቱ በሕግ ማስከበር ሥራው ላይ ጣልቃ ይገባሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በዝምታ የሚታለፍ ከሆነ አገሪቱ ልትወጣው ከማትችለው አዘቅት ውስጥ እንደምትገባ አያጠያይቅም ፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ «አገር ወዳድ የሆነ ህዝብ በራስ ላይ የተቃጣ ኢኮኖሚያዊ ውንብድና መሆኑን ተገንዝቦ ከመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ጋር በመሆን የማስቆም አቅም ስላለው ኮንትሮባንዲስቶችንና ህገወጦችን በማጋለጥ ኢኮኖሚያችን ላይ የተቃጣውን አደጋ ዛሬም እንደትናንቱ ሊያከሽፍ ይገባል» ይላሉ፡፡
በተለይም አገር ተረካቢ ወጣቶች በመጣው አገራዊ ለውጥ ውስጥ ታላቅ ዋጋ ከፍለው የለውጥ ተስፋ እንደጫሩት ሁሉ በህጋዊና ጨዋነት በተሞላበት መንገድ መረን የለቀቀውን የኮንትሮባንድ ንግድና ህገወጥ እንቅስቃሴ በመከላከል ረገድ አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ሚኒስትሯ ያስገነዝባሉ፡፡
«ከምንም በላይ የአገር ኢኮኖሚ የሚገነባው አድርግ አታድርግ ወይም ክፈል አትክፈል በሚል ንትርክ ሳይሆን የንግዱ ማህበረሰብ ከማንምና ከምንም በላይ የሚከፍለው ግብር የሚውለው ለራሱ ጥቅም መሆኑን አውቆ ግብሩን እንዲከፍል፣ ከህገወጥነት እንዲቆጠብና ከህገወጥነት መንገድ ወደ ህጋዊነት እንዲመጣ በክብር ለመጠየቅ እንወዳለን» ይላሉ ሚኒስትሯ፡፡
ሁሉም ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ የአገርን ጥቅም ከመሸጥ ያልተናነስ ፀያፍ የሌብነት ተግባር መሆኑን አውቆ በጋራ ሊዋጋውና ሊከላከለው ይገባል፡፡ ከሁሉ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው በፍቅርና በሠላም በመግባባት ሕግን ማክበር ቢሆንም የሕግ ተገዥነት ላጡ ሠላምና ደህነታችን እስከሚፈታተን ድረስ በህገወጥ መንገድ ለመክበር የሚደረገውን ጥረት ለመግታት የሕግ የበላይነት ማስከበር የግድ ይላል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያሉ የሕግ አካላት በፍፁም አገር ወዳድነት የአገሪቱን ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ በኩል እያደረጉ ካሉት አኩሪ ተግባር በተጨማሪ ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በማስቆም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከሌቦችና ከዘራፊዎች መታደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በመንግሥት የሚደረገውን የመቆጣጠር አቅም ማሳደግ ይቻል ዘንድ ጉምሩክና ገቢዎች ራሳቸውን ችለው እንዲደራጁ መደረጉን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ በተለይም ጫፍ የወጣውን ህገወጥ ንግድን ትኩረት ሰጥቶ ለመታገል የሚያግዝ አደረጃጀት እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
«ከተሳታፊዎቹ እንደተነሳው አሁንም ቢሆን ኮንትሮባንድ ምርቱን ከመያዝ ባሻገር ኮንትሮባንዲስቶችን በሕግ ተጠያቂ የማድረጉ ጉዳይ ገና ብዙ መሥራት የሚጠይቀን ነው። ወንጀለኞች እንዲያመልጡ የሚደረግበት ለዚህ ደግሞ የተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ችግር በየደረጃው ይታያል፤ ዋናው ችግር ግን ህዝብ ሳይሆን ያበረታታውና የልብልብ የሰጠው የመንግሥት አካላት በተባለው ደረጃ ኃላፊነታችንን ባለመወጣታችን ነው፡፡
አሁን ግን እነኚህን ችግሮች ተሸክመን መሄድ አንችልም፤ በህገወጥ መንገድ ከብሮ መኖር ከዚህ በኋላ አይቻልም» በማለት ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ አዳነች ማብራሪያ፤ ህገወጥነት በአገሪቱ ስር የሰደደ ጉዳይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የማስቆሙ ሥራ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ድምፅ በሌለው መሣሪያ እንደመግደል የሚቆጠር ነው፡፡ በመሆኑም ቁጥጥሩ መጀመሪያ ከተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት ሊጀምር ይገባል፡፡ ሕዝቡም የመንግሥትን ቆራጥነት ካየ ከጎኑ ቆሞ በፀረ ኮንትሮባንድ ትግሉ ላይ ይረባረባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሣሥ 5/2011
ማህሌት አብዱል