የወረዳው አርብቶና አርሶ አደሮች ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው

ባቢሌ፡የባቢሌ ወረዳ አርብቶ እና አርሶ አደሮች በተደረገላቸው የቤት ለቤት ድጋፍ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ተቋቁመው ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ሲሉ የባቢሌ ወረዳ የቆላማ አካባቢዎች አየር ንብረት ለውጥ አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ ተናገሩ።

አቶ ሀብታሙ ከሰሞኑ በባቢሌ ወረዳ የመስክ ምልከታ ላደረጉ ጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ የቆላማ አካባቢዎች አየር ንብረት ለውጥ ሲቋቋም ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎችን ይዞ ነው። የመጀመሪያው ኅብረተሰቡ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ ችግሮችን መቋቋም እንዲችል ማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው አርብቶ እና አርሶ አደሩ ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነው። በእዚህ መሠረትም የወረዳው አርብቶ እና አርሶ አደሮች ንብ በማነብ፣ ዶሮ በማርባት እና ቋሚ ፍራፍሬዎችን እና የጓሮ አትክልቶችን በመትከል ከአየር ንብረት ተጽእኖ እንዲላቀቁ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በባቢሌ ወረዳ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በርካታ ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ በተለይም መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ ካለው የሌማት ትሩፋት ጋር በማያያዝ በተሠሩ ሥራዎች ኅብረተሰቡን የማንቃትና የመደገፍ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም እያንዳንዳቸው 30 እማ ወራዎች የተሰጧቸውን 5 ፍየሎች አርብተው በአሁኑ ጊዜ በቁጥር ከአሥር እስከ አስራ ሦስት ማድረሳቸውን ተናግረዋል። የሚያረቧቸውን ፍየሎች እየሸጡ ከፊሉን ገንዘብ ለቤት ፍጆታ እያዋሉ ከፊሉን እየቆጠቡ ናቸው ብለዋል።

በባቢሌ ወረዳ አንድ ቦታ ላይ ሼድ በመሥራት 30 ዘመናዊ የንብ ቀፎ ከሙሉ ግብዓቱ ጋር እና 30 ባህላዊ የንብ ቀፎ ከነ ንቡ ለ30 ሰዎች በመስጠት ከሚሠሩት ሥራ በተጨማሪ ንብ በማነብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ከዶሮ እርባታ ጋር በተገናኘም እንዲሁ አንድ ሺህ 510 ዶሮዎችን ለ310 አባ ወራዎች በማከፋፈል ልጆቻቸው እንቁላል እንዲመገቡና ከፍጆታ የተረፋቸውን ሸጠው ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ከሌማት ትሩፋት ጋር በተያያዘ በወረዳው ለተመረጡ ሦስት አርሶ አደሮች የውሃ ማቆሪያ ሸራ በመስጠት በግቢያቸው ውስጥ የዓሳ ዕርባታ እንዲጀምሩ እና ለሌሎች ሞዴል እንዲሆኑ ስለመደረጉም ጠቅሰዋል።

እንደየ መልክዓ-ምድሩ እና የአየር ጸባዩ ሁኔታ ለአርሶ እና አርብቶ አደሮቹ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርጥ ዘሮችን በመስጠት እያመረቱ እንዲጠቀሙ ተደርጓል ብለዋል። እስከ አሁንም 920 የሚሆኑ አርሶ አደሮች ችግኞችን እየወሰዱ ማሳቸው ላይ በመትከል ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ የከርሰ ምድር ውሃን እየቆፈረ በዲናሞ በመታገዝ ከጉድጓድ ስቦ ለችግኞቹ እንዲጠቀም መደረጉን ገልጸው፤ በእዚህም ድርጅቱ 14 የውሃ ጉድጓዶችን እንደቆፈረና በእዚያው ልክ ዲናሞ እና ሸራ እንደገዛ ተናግረዋል።

ለምግብነት የሚያገለግሉትን በማሳዎች ላይ ለደን ሽፋን የሚሆኑትን በተመረጡ ቦታዎች ላይ መትከላቸውን አስረድተዋል። ለከብት መኖ የሚሆኑ የሳር አይነቶችንም በችግኝ ጣቢያዎች በመትከል አርሶ እና አርብቶ አደሩ በማሳው ላይ እያስፋፋ እንዲጠቀምበት ተደርጓል ብለዋል። በችግኝ ጣቢያዎቹ ለበርካታ እማወራዎች የሥራ እድል ስለመፈጠሩም ጠቅሰዋል።

168 ለሚሆኑ አርሶ አደሮችም እንዲሁ እንደ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ካሮት የመሳሰሉትን ዘሮች በመስጠት በ86 ሄክታር ላይ እያመረቱ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ስለመቻሉም ገልጸዋል። በተደረገላቸው ድጋፍ የጓሮ አትክልቶችን አልምተው በመሸጥ ባቢሌ ከተማ ላይ ቤት እስከ መሥራት የበቁ አርሶና አርብቶ አደሮች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

ድርጅቱ ለ182 አርሶ አደሮች የስንዴ ዘር በማቅረብ በ116 ሄክታር መሬት ላይ የበጋ ስንዴ አምርተው 3ሺህ 16 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

ወቅታዊ የአየር ንብረት መረጃን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ረገድም ድርጅቱ ከአዋሽ ተፋሰስ መልስ ስምንት የአየር ጸባይ ሁኔታዎችን መለካት የሚችል አውቶማቲክ ዌዘር ስቴሽን ( Automatic weather station ) የተሰኘ የአየር ትንበያ ጣቢያ አቋቁሞ ለአርሶ አደሩ ተገቢውን መረጃ እየሰጠ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው የዝናባማ ፣ ሞቃታማ፣ የእርጥበታማ፣ ፀሐያማ ፣ ነፋሻማ እና ሌሎችንም የአየር ጸባይ ሁኔታ እየመዘገበ እና እየተነተነ በአካባቢው ላሉ አርሶ አደሮች መረጃ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም ለተመረጡ መቶ አርሶ አደሮች ስማርት ስልክ በመግዛት ከአየር ትንበያ ጣቢያው የሚላክላቸውን መረጃ በቀጥታ ስልካቸው ላይ በማንበብ ግብርናቸውን በአግባቡ እንዲመሩ ይደረጋል ሲሉ የባቢሌ ወረዳ የቆላማ አካባቢዎች አየር ንብረት ለውጥ አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ አስረድተዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You