ባለጉዳዮች የሚንገላቱበት ተቋም

አብዛኛዎቹ የተቋሙ የቢሮ በሮች ጥርቅም ብለው ተዘግተው ይታያሉ። በተዘጉ የቢሮ በሮች ላይ ማንን ምን መጠየቅ የሚጠቁም አንዳች ነገር አይስተዋልም። በርከት ካሉ ባለጉዳዮች መካከልም ገሚሱ ግድግዳውን ተደግፎ ሌላው ደግሞ የቢሮውን በር የሙጥኝ ብሎ ቆሞ ይስተዋላል። ከተገልጋዮች ፊት የሚነበበው ድካምና መሰላቸት ነው። ምድረ ግቢው እራሱ የሚስተዋልበት የደበዘዘ ተቋማዊ ገጽታ ነው። የኤፌዴሪ የትምህርት ሥልጠና ባለሥልጣን፡፡

ባለጉዳዮቹ ወደተቋሙ የመምጣታቸው ምስጢር የትምህርት ማስረጃቸውን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ለደረጃ ዕድገትም ሆነ ለውጭ ሀገር ጉዞ አስፈላጊ የሆኑ የትምህርት ማስረጃዎቻቸውን ለማረጋገጥ ነው። እነዚህ ባለጉዳዮች ከተለያዩ የሀገሪቱ ጫፍ የመጡ ናቸው። በአጭር ቀን አገልግሎት አግኝተው ወደየመጡበት ተመልሰው ለመሔድ አልመው ይምጡ እንጂ እንዳሰቡት አለመሆኑን ጠይቀናቸው ማረጋገጥ ችለናል። የእነርሱ ሕልም በአግባቡ ተስተናግደው መመለስ ቢሆንም፤ በተቋሙ የጠበቃቸው አገልግሎት ግን በተቃራኒው ነው።

ቀን ቀንን እየወለደ በሔደ ቁጥር ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረግን መጥተናል ያሉን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለጉዳዮች፣ ጉዳያቸው እልባት የሚያገኘው መቼ እንደሆነ ግራ መጋባታቸውን ይናገራሉ። የዝግጀት ክፍላችን፣ መረጃ ፍለጋ በተለያየ ጊዜ ወደ ተቋሙ ባመራበት ጊዜ ከተገልጋዮች አንደበት የሰማው የብሶት ድምጽ ነው። የኢፌዴሪ ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ከአራቱም የሀገሪቱ ማእዘናት የመጡ ዜጐች ለእንግልት የሚዳረጉበት ተቋም ሆኗል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከጅማ የመጡ ተገልጋይ እንደሚገልጹት፤ ለልጆቻቸውና ለባለቤታቸው ቶሎ እንደሚመለሱ ነግረዋቸው ቢመጡም በተቋሙ የገጠማቸው ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ የአገልግሎት አሰጣጥ ነው። ማስረጃቸው እንዲረጋገጥላቸው ባለሥልጣኑን ሲጠይቁ የተማራችሁበት ተቋም የትምህርት ማስረጃችሁን አልላከም የሚል ምላሽ ይሰጣቸዋል። ወደተማሩበት የትምህርት ተቋም ተጨማሪ ወጪ አውጥተው ሔደው ሲጠይቁ ደግሞ ለተቋሙ መላኩን ጠቅሶ ያንኑ የሚያሳይ የላኩበትን ደብዳቤ በማስረጃ አስደግፈው ይነግሯቸዋል።

ቅሬታ አቅራቢዋ እንደሚሉት፤ ድጋሚ ወደ ባለሥልጣኑ በማምራት ሲጠይቁ የተሰጣቸው ምላሽ “ምን አልባትም የትምህርት ማስረጃችሁ ፎርጅድ ወይም ሀሰተኛ” ሊሆን ይችላል የሚል ሞራል የሚነካ መልስ መሆኑን እየተናነቃቸው ይናገራሉ።

የትምህርት ማስረጃቸውን ለማረጋገጥ ወደ ተቋሙ ያቀኑት ሌላኛው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ተገልጋይ በበኩላቸው፤ በተቋሙ የትኛውም ቢሮ ምን አይነት አገልግሎት የትኛው ዘንድ እንደሚገኝ መረጃ የሚሰጥ አካል የለም ይላሉ። ነገር ግን መግቢያው ላይ የሚገኙ የጥበቃ ሠራተኞች ሰሌዳ ላይ የተለጠፈ ነገር እንዳነብ ጠቁመውኝ አንብቤያለሁ። በሰሌዳው ላይ የተለጠፈው መረጃ ምዝገባ የሚካሄድበትን ድረ ገጽ ብቻ ተጠቅማችሁ ተመዝገቡና በስልክና ኢ-ሜይል መረጃ ሲገለጽላችሁ ትመጣላችሁ የሚል ነው። ተመዝገቡ የተባለበት ድረገጽ በሞባይልና በኮምፒውተር በተደጋጋሚ ሲሞከር በቀላሉ ተደራሽ የሚደረግ አይደለም።

ድረ ገጹን ለመክፈት በተደጋጋሚ መሞከራቸውን የጠቆሙት ተገልጋዩ፤ ሊሠራላቸው አልቻለም። ድረ ገጹን ለሳምንት ቢሞክሩም ሊሳካላቸው ባለመቻሉ ከተቋሙ ውስጥ ለሚያውቁት ሰው ደውለው “ኢንተርኔት ቤት ሂደው ይመዘገቡ” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ያስረዳሉ። ያንኑ የተሰጣቸውን መረጃ ተቀብለው በተቋሙ በር አካባቢ የኢንተርኔት አገልግሎት ወደሚሰጡ ቤቶች በማምራት በመቶዎች የሚቆጠር ብር ከፍለው እንደተመዘገቡ ያስረዳሉ። ይህ ሁኔታ ዌብሳይቱ ለተገልጋይ የማይከፍት ለኢንተርኔት ቤቶች ግን የሚከፍትበት መንገድ ጥያቄ እንደሆነባቸው ይናገራሉ። ድረ ገጹ ግን ማንኛውም ሰው በቀላሉ በስልኩ ሊያገኝ የሚችል መሆን ሲገባው ለእንግልትና ለብዝበዛ የሚዳርግበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይላሉ። በመሆኑም በተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅር መሰኘታቸውን ይገልጻሉ። ተገልጋይ ሲቸገር ምን ላግዝህ ብሎ መረጃ የሚሰጥ አንድም ሰው ፈጽሞ የለም የሚሉት ተገልጋዩ፤ ተከፍሎም ቢሆን መረጃዎች ሲጫኑ በጣም እንደሚያስቸግር ያመለክታሉ፡፡

ውጣውረዱን አልፈው ካመለከቱ በኋላም ለወራት ምንም አይነት መረጃ በኢ-ሜልም ሆነ በስልክ እንዳልተላከላቸው የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢው፤ መረጃው “የት ደረሰ?” ብሎ ለመጠየቅ ያስቀመቱት አጭር የስልክ ኮድም ማይሠራ መሆኑን ይገልጻሉ። ስለዚህም በኢ-ሜል መረጃ ይመጣል በሚል ከስድስት ወራት በላይ ጠብቀዋል።

ምድረ ግቢው ከገጽታው ጀምሮ ተገልጋይ ለመቀበል ምቹ ሁኔታ የለውም የሚሉት ተገልጋዩ፤ በተለይም ደግሞ ከለውጡ ወዲህ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ተቋማት ለሥራ አመቺ ሁኔታ እንዲኖራቸው የተጀመረው ሥራ ብዙ ቢሮዎች ላይ ፍሬው እየታየ ቢሆንም፤ ባለሥልጣኑ ግን ገጽታውን ያልቀየረ በድሮው ገጽታው ያለ ነው። ስለዚህ ተቋሙ ወቅቱንና ዘመኑን የሚመጥን አይደለም። አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ገና ምን አይነት መረጃ እንደሚጠየቁ ሳያውቁ በተሰላቸ መንፈስ “ሲስተም የለም” የሚል ምላሽ እንደሚሰጡም ያብራራሉ። በአጠቃላይ የትምህርት መረጃው የተረጋገጠላቸው ባመለከቱ አንድ ዓመት ሊሞላው በተቃረበ ጊዜ ውስጥ ነው። ይህ የሚያሳየው አገልግሎቱ ብልሽት ያለበት እና መንግሥት ሊፈትሽው የሚገባ መሆኑን ነው ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ተቋሙ የሕዝብ ለቅሶና ሮሮ በተለይም ከሩቅ አካባቢ ከሚመጡ ተገልጋዮች በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰማበት ነው። ተቋሙ በዚህ ዘመን ሊኖርና ሊታይ የማይገባው አገልግሎት እየሰጠ ያለ ነው። ስለዚህ የሚመለከተው አካል ተቋሙን ፈትሾ ማስተካከል ይገባዋል ሲሉ ይናገራሉ።

የተቋሙ ሠራተኛ የሆኑ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አንድ የትምህርት ተቋም ይሰጥ የነበረውን የትምህርት መርሃግብር ሲዘጋ ምን አይነት የትምህርት ዓይነት እንደሆነ ለሕዝብ መግለጽ አለበት። በተቋማት ላይ የሚወሰደውን ርምጃም ለሕዝብ ከማሳወቅ ይልቅ አፍኖ የመያዝ ሁኔታ ይስተዋላል። ከሥርዓቱ እየወጡ ያሉ ተቋማት በምን ምክንያት እንደወጡ መግለጽ እየተገባ ይህ ግን አይደረግም።

የተቋሙ የውስጥ አደረጃጀት ተቋማዊ ሥራዎችን በብቃትና በጥራት ለመወጣት የተደራጀ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ሁሉም በራሱ ቢሮውን ቆልፎ የተቀመጠ ከመሆኑም በተጨማሪ ግላዊና ቡድናዊ መልክ ይዟል። ይህም ከተቋማዊ አሠራር ውጭ ሆኖ እየታየ ነው። ይህ አይነቱ ሁኔታ ደግሞ የተቋሙን ራዕይና ተልእኮ ለማሳካት የሚያስችል ቁመና ላይ አለመሆኑን አመላካች ነው። በአጠቃላይ ለተገልጋዮች ፈጽሞ ክብር የሌለው ተቋም ሆኗል ሲሉም ሃሳባቸውን ይገልጻሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ምላሽ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ በቃልም ሆነ በደብዳቤ ብንጠይቅም ምላሽ ሊሰጡን ፈቃደኛ አይደሉም። ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑ በማንኛውም ጊዜ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You