ሁለቱ ተቋማት የዜጎች ሀብትና ንብረት በሕገ ወጦች እንዳይመዘበር የሚያስችል ስምምነት አደረጉ

አዲስ አበባ፦ ስኬት ባንክ እና የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የዜጎች ሀብትና ንብረት በሕገ ወጦች እንዳይመዘበር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ ባንኮች በሃሰተኛ ሰነድ እንዳይጨበረበሩ እና ደንበኞች ይዘውት የሚመጡት ሰነድ በሕጋዊ መንገድ ከተቋሙ የመነጨ መሆኑን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው። ይህንን ማድረግ የዜጎች ሀብትና ንብረት በሕገ ወጦች እንዳይመዘበር ያደርጋል ተብሏል።

የስኬት ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳምጠው አለማየሁ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ባንኩ ሰነዶችንና ውክልናዎችን ለማረጋገጥ እና ለማጣራት ወደ ሰነዶች ማረጋገጥና ምዝገባ አገልግሎት በአካል መሄድ ያስፈልገው ነበር። አሁን ግን ከአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ጋር በተደረገ ስምምነት የቴክኖሎጂ ግንኙነት መፍጠር ተችሏል። በዚህም ባንኩ ሰነዶችን በቀላሉ ማረጋገጥ የሚችልበት ሥርዓት ፈጥሯል።

ከዚህ በፊት የብድር አገልግሎት አሰጣጥ እና ውክልና የማጣራት ሥራ ላይ የማንነት ማጭበርበርና መሰል ተግዳሮቶች ያጋጥሙ እንደነበር አውስተው፤ ይህም ባንኩ ብድር ለማስመለስ የሚያደርገው ሂደት ላይ እንቅፋት ይፈጥር እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ግን ማንነትና ሰነድ ማረጋገጥ ሥራ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በቀላሉ መለየትና አፋጣኝ ውሳኔዎችን መውሰድ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል። ይህም ይህም ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀሚድ ኪኒሶ በበኩላቸው፤ ከስኬት ባንክ ጋር የተፈራረምነው ስምምነት የቴክኖሎጂ ትስስር ለመፍጠር ያስቻለ ነው። በዚህም ባንኩ በአገልግሎቱ የሚሰጡ አገልግሎቶችና ውክልናዎች ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥበት ሥርዓት መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

ይህም በአካል መገኘት ሳያስፈልግ የሚከናወን መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም ባንኮች ውክልናዎችን የሚያረጋግጡት በደብዳቤዎች፣ በቀጠሮና በአካል መገኘት ያስፈልግ ነበር። ይህም ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ይዳርግ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህም በአገልግሎቱና በደንበኞች መካከል ያለው ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከመፍጠሩ ባለፈ ለአጭበርባሪዎች እድል የሰጠ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አገልግሎቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ዲጂታል በማድረጉ የነበሩ ክፍተቶችን መሙላትና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በተፈጠረ ትስስር ሀሰተኛ ሰነዶችንና ማንነት የማረጋገጥ ሥራ ቀላል መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ በኦንላይን ለሚሰጡ አገልግሎቶች ትክክለኛና ተዓማኒ እንዲሆኑ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ገልጸዋል።

ነሐሴ ወር 2015 ዓ .ም የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም አክሲዮን ማህበር ስኬት ባንክ አከሲዮን ማህበር በሚል ስያሜ ወደ ባንክነት መሸጋገሩ ይታወቃል።

ሳሙኤል ወንደሰን

 

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You