የጉራጌ ሴቶች ተምሳሌትነት

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ፣ ባሕላዊና ፖለቲካዊ መብቶቻቸው ለማስከበር ለረዥም ዓመታት ትግል አድርገዋል። ከተለያዩ መረጃዎች እንደምንገነዘበው በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በሌሎችም ሀገሮች ለፆታ እኩልነት መከበር በተገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ጥሪዎችና ንቅናቄዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡

እኤአ በ87ዐዎቹ መጀመሪያ በማናቸውም ሁኔታ ሴቶችን የበታች የማድረግ አመለካከቶች እንዲቀየሩ የተደረጉት ጥረቶች፣ በ908 ለተሻለ የሥራ ሁኔታ እና የድምጽ መስጠት መብት መከበር ኒውዮርክ ከተማ ላይ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ፣ በአጠቃላይም ከአስራ ዘጠነኛው ምዕት ዓመት አጋማሽ በኋላ የሴቶችን ጥያቄ ከአጽናፍ አጽናፍ የማስተጋባት ጥረቶች እና የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር በየጉባኤዎቹ ላይ የቀረቡት ከረር ያሉ ሃሳቦች ወይም ጥያቄዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተደራጀ የሴቶች የመብት ንቅናቄ ፋና ወጊ መሪነታቸው አንጸባራቂ ሥማቸው በመላው ዓለም ሲናኝ የኖረው የሴቶች መብት ተከራካሪዎች ክላራ ዜትኪን፣ ሮዛ ሉክሰምበርግ፣ ሌሎችም በታሪክ ይታወቃሉ። ክላራ ዜትኪን እ.ኤ.አ በ90 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በየዓመቱ እንዲከበር ሃሳብ ያቀረበች ብርቱና ወኔያም ሴት ናት።

በዓለም ላይ የሴቶች የመበት እና የእኩልነት ጥያቄዎች በተደራጀ መልኩ በይፋ መነሳት የጀመሩት ከመቼ ጀምሮ እንደሆነና እነማን እንደጀመሩት በስፋት ሲፃፍ ወይም ሲተረክ ቆይቷል። እኛም ከዚህ ያለፈ መረጃ ስለሌለን በደፈናው ተቀብለነው ኖረናል። በዓለም፣ በአኅጉር፣ በሀገርም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ የተሰጠን መረጃ ከሌለን ደግሞ ጥያቄ ሊያስነሳብን፣ ፀፀትም ሊያድርብን አይችልም። ከባነንን ያለው ብቸኛ አማራጭ እርምጃችንን ማሳመር ነው፡፡

ከዚህ አንጻር በአንድ በኩል በየሀገሮቹ የተካሄደው የሴቶች የፆታ ትግል አጀማመርና ያገኘው ዓለም አቀፍ ዕውቅና በአጭሩ ከፍ ብሎ የቀረበውን ይመስላል። በሌላ በኩል ደግሞ በሀገራችንና ምናልባትም (ጨዋነት በተላበሰ አገላለፅ) በምድራችን ላይ የመጀመሪያውን የሴቶች የተደራጀ የመብት ትግል ከጀመሩት ውስጥ በተለይ ካላደጉት ወይም ከሰሀራ በታች ከሚገኙት ሀገሮች ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡

የጉራጌ ሴቶችን አመጽ እና የአመጹን መሪ ወይም በንቅናቄው በአብሪ ጥይት ተኳሽነቷ ቢያንስ ከክላራ ዜትኪንና ከሮዛ ሉክሰምበርግ በጣም ቀዳሚ የሆነችውን ታጋይ የእኛዋን የቃቄ ውርድወትን ዓለም ቀርቶ እኛም ባለቤቶቹ እንኳን በአግባቡ አላወቅናቸውም። ለማወደስ አልተሰለፍንም። እምብዛም አልተነገረላቸም። የጀግኒቷ የተደራጀ እንቅስቃሴ፣ ፈር ቀዳጅና ተምሳሌታዊ ተጋድሎ ነጋሪት ሲጎሰምለት፣ ከበሮ ሲመታለት አይሰማም ወይም አይታይም፡፡

ተጨባጭ መረጃ እጃችን ላይ እያለ ኢትዮጵያ የተዛባ የፆታ መብት አያያዝን በመቃወም ቀዳሚ ንቅናቄ ከተደረገባቸው ሀገሮች አንዷ መሆኗን አላስተዋወቅንም። በቅርቡ ተጀምረው የነበሩ አንድና ሁለት ተጨባጭ ጥረቶችም እንደገና የተቀዛቀዙ መሆኑ የሚቆጭ ነው። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ግን ጥረቱ ስር እንዲሰድ በተገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ንቅናቄ ለመፍጠር አምርሮ ከተነሳ ሰነባብቷል።

በዚህ አጋጣሚ እንዳለጌታ ከበደ (ዶ/ር) “የቃቄ ውርድወት እምቢታ በሚል ርዕስ በ2006 ዓ.ም አሳትሞ ለንባብ ያበቃውና የውርድወትን ሙሉ የሕይወት ታሪክ የያዘው እና የጉራጌን ሴቶች አመፅ ገድል የያዘ ታሪካዊና ፎክሎራዊ ልቦለድ መጽሐፍ የጀግናዋ ተጋድሎ ህያው ምስክር ነው። የቃቄ ውርድወት በሚል ርዕስ በጸሐፌ ተውኔት ጫንያለው ወ/ጊዮርጊስ ተደርሶ፣ በዳግማዊ ፈይሳ ዳይሬክተርነት ተዘጋጅቶ እና በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የባሕል ዋና አማካሪነት ተደራጅቶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ለ3 ዓመታት ያህል በሕዝብ ሲታይ የቆየው ቲያትር፣ ኢትዮጵያ በዓለም የሴቶች የመብት ትግል ውስጥ ቀዳሚ አስተዋጽኦ እንዳላት ጉልህ ማረጋገጫ ስለሆኑ ባለሙያዎቹ ለተነሳሽነታቸውና ለላቀ ጥረታቸው ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

የጉራጌ ሴቶች እንደማይረባ እቃ ያለምርጫቸው ሥሙንም መልኩንም ለማያውቁት ባል ይሰጣሉ ወይም ይዳራሉ። ባል ካሻው 2 አልፎም 3 ሚስቶችን ያገባል፣ ያስተዳድራል፣ ባስፈለገው ጊዜ ከአንዷ ወደ ሌላኛዋ እየተዟዟረ ይዝናናል። በተቃራኒው ሚስት ግን ከአንድ በላይ ባሎችን ልታገባና ከቆላ ደጋ፣ ከደጋ ወይና ደጋ እየተዟዟረች ልትዝናና ቀርቶ ልታስበውም አትችልም።

አልፎ ተርፎ ባል ካልፈለጋት ያለምንም የሀብት ድርሻ ክፍፍል ጥራ ግራ ከገነባችው ኑሮዋ ባዶ እጇን ያሰናብታታል። ሚስት ግን ባሏ ወዶና ፈቅዶ ፈትቼሻለሁ-የፈለግሽውን ባል ማግባት ትችያለሽ“ ብሎ መርቆ ካላሰናበታት በስተቀር ጥላው ሄዳ ሌላ ባል እንዳታገባ አንጅት የሚባል የማሕበረሰቡ ጥንታዊ የባሕል ማዕቀብ ተጥሎባታል፡፡

ውርድወት የጉራጌ ሴት ከባልዋ ጋር እኩል መብት ያላት “ሚስት“ ሳትሆን የባሏ እቃ ተደርጋ መታየቷን አምርራ ተቃወመች። በዓፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት (የዛሬ 16 እስከ 170 ዓመት ግድም መሆኑን ልብ ይሏል) ከጉራጌ ማሕበረሰብ የተገኘችና በአካባቢዋ ማሕበረሰብ ዘንድ የተከበረ ሥም ካላቸው አባትና እናት የተወለደች ናት።

አባቷ ዳሞ ቃቄ (ዳሞ በጉራጌ የወንዶች ባሕላዊ የማዕረግ ሥም ነው የምሁር ቤተ ጉራጌ ተወላጅ እና በምሁር የውድማጠረ ቤተሰብ፣ የጉራጌ ታዋቂና ሥመጥር ጀግና፣ በታሪክ የሚታወቁት የአጋዝ ሸበታ ወንድም ናቸው። (አጋዝ የጀግና ወንዶች ከፍተኛው ባሕላዊ የማዕረግ ሥም ነው፡፡) እናቷ አጅየት አሚና ደግሞ የወለኔ ቤተ ጉራጌ ተወላጅ እንደሆኑ ከታሪኳ

እንረዳለን። (አጅየት ባሕላዊ የሴቶች የማዕረግ ሥም ነው) ውርድወት ልጅነቷ እጅግ ጣፋጭ የነበረና በወላጆቿ ቤት ተቀማጥላ ያደገች ልጅ ናት። ቁንጅናዋን በቃላት ለመግለጽ ከሚቻለው በላይ ነው ይላሉ ታሪክ አዋቂዎች። የቆንጆዎች ቆንጆ፣ የውቦች ሁሉ ውብ ናት። በዚህ ላይ በራሷ እጅግ የምትተማመን ወጣት ነበረች፡፡

ከሁሉም በላይ አስደናቂው ነገር ውርድወት እንደሌሎቹ የሰለጠኑ ሀገሮች የሴቶች መብት ታጋዮች፣ ለምሳሌም እንደ ሮዛ ለከሰምበርግና እንደ ክላራ ዜትኪን ዲግሪ የጫነች ሳትሆን እንኳንስ የከፍተኛ ትምህርት ይቅርና አንድም ቀን የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ደጃፍ አልረገጠችም።

እንደ ቀድሞዎቹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ፈደልም አልቆጠረችም። የፖለቲካ ድርጅት መሪ ወይም የጋዜጣ አዘጋጅ ልትሆን ቀርቶ በእሷ ዘመን በጉራጌ ምድር ትምህርትም፣ የፖለቲካ ፓርቲም ጋዜጣም አይታወቅም። አንድም ቀን መጽሐፍ ወይም ጋዜጣና መጽሄት አላነበበችም። ሬድዮ አላዳመጠችም። ቴሌቪዥን አልተመለከተችም። በበቅሎና በፈረስ እንጂ በመኪና፣ በባቡርና በአውሮፕላን አልተጓዘችም። የኩበትና የማገዶ ጭስ እንጂ የኢንዱስትሪ ጭስ አይታ አታውቅም፡፡

እንደ ኒውዮርክ፣ ዋሸንግተን፣ በርሊን፣ ስቶኮልም፣ ኮፐንሀገን፣ ለንደን፣ ፓሪስ፣ እና መሰል ውብ አውራ ጎዳናዎች ላይ ተመላልሳ አይደለም ትግሉን የመራችው። ተራራውን ወጥታ፣ ቁልቁለቱን ወርዳ፣ በየሸለቆውና በጥሻው ውስጥ አልፋ የታገለች፣ ከዚያ በፊትም ከጫካው፣ ከወንዙ፣ ከዱር እንስሳትና ከአዕዋፋት ድምጽ ጋር ያደገች የገጠር ልጅ ናት ውርድወት። ይህ በገጠር የሚኖሩ የዚያ ዘመን የጉራጌ ሴቶች ሁሉ ያለፉበት ታሪክ ነው፡፡

የጉራጌን ሴቶች ትግል እና የመሪያቸውን የውርድወትን ስብእናና ወኔ ከሰለጠነው ዓለም የፆታ ትግል የሚለየው ዋነኛው ይሄ እውነታ ነው። ውርድወት ዕድሜዋ ለጋብቻ ሲደርስ አጋዝ ፍርችየ ለተባለ የኧዣ ጀግና ተዳረች። የሕግ ባለቤቷ እንደሌሎቹ የጉራጌ ታዋቂ ወንዶች ሁሉ ባሕሉ ስለሚፈቅድለት ከእርሷ በፊት ሌላ ትዳር ነበረው።

ከአንድ በላይ ትዳር (በትዳር ላይ ትዳር) ክልክል ስላልነበረ ውርድወትን ተደራቢ ሚስት አደረጋት። ጀግኒት ግን ይህ ጉዳይ ክፉኛ አስከፋት። አሳመማት። አቆሰላት። በትዳር ላይ ትዳር እምቢዮ አለች። አመጸች። ከልጅነቷም ጀምሮ የሴትን ልጅ መጠቃት ትጠየፍ የነበረችው ሴት ፈጣሪ የሰጣትን የማነሳሳት ጥበብ ተጠቅማ ዮጉራጌን ሴቶች አሳመጸች፡፡

በትዳር ላይ ትዳር የማይፈልጉት ድርጊት በመሆኑ በይቻላል መንፈስ በደላቸውን በግልጽ አይቃወሙት እንጂ ጉዳዩ የሌሎቹም የአካባቢው ሴቶች ጥያቄ ሆኖ ኖሯል። የኢትዮጵያም እንጂ። የጉራጌ ባሎች ሚስታቸውን ወደውና ፈቅደው (ተገደውም ቢሆን “ስርጥ የሕርሕ ሚኒም ምስ ያግባሕ” ማለትም አንቕቱ ተነስቶልሻል ፈትቼሻለሁ ማንም ወንድ ያግባሽ ብለው ካላሰናበቷት በስተቀር ሌላ ባል ማግባት አትችልም። አንቕት የተባለ በሴቶች ላይ የተጣለ ልማዳዊ ክልከላና ገደብ ነበር፡፡

ይህች በጉራጌ የገጠር መንደሮች ውስጥ ሀገር ያንቀጠቀጠ ትግል የጀመረች፣ የጥንካሬ ተምሣሌት፣ የብርቱዎች ብርቱ፣ የጀግና ሴቶች ቁንጮ የሆነች እንስት በራሷና በጉራጌ ሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ፆታዊ ጭቆና በዝምታ ልታልፈው አልፈቀደችም። ተከታዮቿን አሰልፋ፣ ከመኖርያ ሰፈሯ ተነስታ፣ መኪና ወይም ጋሪ እንኳን በሌለበት በእግሯም በበቅሎም በየቀበሌዎቹና በየወረዳዎቹ ተዘዋውራ የጉራጌን ሴቶች ቀስቅሳ፣ አስተባብራና አደራጅታ፣ ለመብታቸው አምርራ አደባባይ ወይም ጀፈር ላይ ወጥታ ታገለች። አታገለች። (ጀፈር የጉራጌ አደባባይና የገጠር አውራ ጎዳና መሆኑ ነው፡፡)

የድሃ ሀገር ተወላጅ በመሆኗ የትግል ታሪኳን የሚያጮህላት፣ ዘምሮ የሚያዘምርላት እምብዛም ባይታይም እንደሌሎቹ ዝነኛ የዓለም የሴቶች ትግል መሪዎች ሁሉ ውርድወትም ያፈራት ማሕበረሰብ፣ የሀገሯ፣ የአኅጉሯና የዓለምም ጀግና ናት። ይሄ በታሪክ የተረጋገጠ ተጨባጭ ዕውነታ ነው። ተወልዳ ያደገችበትም፣ ተድራ የተቀላቀለችበትም ቀዬ እና የግራና የቀኝ ትውልዷም አሁንም በቦታው አለ፡፡

በጭቆና በተሞላ ማሕበረሰብ ውስጥ ተወልዳ አድጋ ጭቆናው እየታወቃትና እያደር ደም ስሯን እየመዘመዘው ሲሄድ የጉራጌን ሴቶች የጦር መሳሪያ ሳይሆን የሀሳብ ትጥቅ አስታጥቃ ከጎኗ በማሰለፍ የበዙኃን ሴቶች አመጽ ቀሰቀሰች። አቀጣጠለች። አፋፋመች። አቤቱታዋ በይግባኝ የቀረበለትና የጆካ ላይ የተሰየመው የጉራጌ የመጨረሻው የቍጫ ሸንጎ ወይም ባሕላዊ ፍርድ ቤት ቀርቶ ማንም ምድራዊ ኃይል ትግሏን ሊያስቆም አልቻለም፡፡

ሴት ልጅ በወላጆቿ ውሳኔ ራሷ ላልፈቀደችው ወይም ላልመረጠችው ወንድ መዳር የለባትም፣ ሚስት በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ባል ማግባት እንደማይፈቀድላት ሁሉ ባልም በአንዲት ሚስት ይወሰን፤ ከአንድ በላይ (በሚስት ላይ) ሚስት ማግባት የለበትም፣ባሎች በፈለጉበት ጊዜ ከሚስታቸው ስምምነት ውጭ በራሳቸው ፈቃድ ሚስታቸውን የሚፈቱበት፣ ሚስቶች ግን ይህንን እኩል መብታቸውን የሚያሳጣቸው ልማድ ተነስቶላቸው ባላቸው ቢፈቅድም ባይፈቅድም፣ የፍች መብት ቢሰጣቸውም ባይሰጣቸውም ባልተመቻቸው ጊዜ ትዳራቸውን ፈትተው፣ ቤታቸውን ትተው ሄደው የመረጡትን ሌላ ባል እንዳያገቡ የሚከለክለው ገደብ ወይም ኋላ ቀር ባሕል ይነሳልን፤

በፍች ወቅት ሚስት የጋራ ንብረቷን ከባሏ እኩል የመካፈል የኢኮኖሚ መብቷ ይከበር፣ሴቶች እንደወንዶቹ ሁሉ በአደባባይ የመሰብሰብ፣ የመወያየት፣ በባሕላዊ ችሎቶች የመሳተፍ መብታችን ያለ ገደብ ይከበርልን፣ ልጅ ባባቱ ሥም ብቻ ለምን ይጠራል? 9 ወር በሆዷ ተሸክማ፣ አምጣ ወልዳ፣ መከራዋን በልታ የምታሳድገው ልጇ በእናቱም ሥም ይጠራ፣ የሚሉና ሌሎችንም በርከት ያሉ የጉራጌ ሴቶች መሰል የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ ጥያቄዎች ከመንደር ሸንጎ ጀምራ በጉራጌ ባሕል መሰረት በየደረጃው ለተሰየሙ ችሎቶች አቅርባ ሞገተች።

“የጉራጌ ሴቶች ተነሱ፤ የእስካሁኑ የወንዴው ሥርዓት ጭቆና ይበቃናል፤ አብረን ታግለን መብታችንን እናስከብር፤ እኩልነታችንን በእጃችን እንጨብጥ! የሚለው ድምጿ በጉራጌ ምድር አስተጋባ። ሠማየ ሠማያት ድረስ እስኪሰማ ጮኸች። አምርራ ተከራከረች። ከፆታ ጭቆና ነፃ ለመውጣት፣ እንደ ተራ ዕቃ ሳይሆን እንደሰው ለመቆጠር፣ ዝቅ ተደርጋ ላለመታየትና ክብሯን በመዳፏ ለመጨበጥ ተሟገተች ብቻ ሳይሆን ተፋለመች፡፡

የብሶት ድምጿን፣ የመከፋት እንባዋን እንኳንስ ትንንሾቹ ኮረብታዎች ዘቢዳርን የሚያህለው ግዙፉ የጉራጌ ሰንሰለታማ ተራራም ከመደመጥ ሊያግደው አልቻለም። የትግል ጥሪዋን ሐሬበ፣ጐታም፣ መጘቻ፣ ዋቤ እና ሌሎቹም ጉራጌ ውስጥ የሚፈሱ ወንዞች ሊያስቆሙት አልቻሉም። ለነፃነታቸው ያመፁት ሴቶቹ ብቻ ሳይሆኑ ደኖቹ ሜዳዎቹና ሸለቆዎቹ ሁሉ ከጎኗ ተሰለፉ፡፡

እዚህ ላይ የውርድወትን ተጋድሎ ክብደት የሚያሳዩ አንዳንድ አስደናቂ ክስተቶችን እናንሳ። መብታቸውን ለማስከበር አብረዋት የተሰለፉት የድሀ ባሎች ሚስቶች ብቻ ሳይሆኑ የሀብታም፣ የባላባት፣ የታዋቂ ባሎች ሚስቶችም በሚገርም ሁኔታ ከጎኗ የተሰለፉ መሆናቸው አንድ ልዩ ነገር ነው። (ድሮም ቢሆን ሁለትና ሦስት ሚስቶችን የሚያገቡት የደላቸውና በደጋ፣ በወይናደጋ እና በቆላ መሬት፣ ቤትና ንብረት ያላቸው ታዋቂ ወንዶች ስለሆኑና የጭቆናው ገፈት ቀማሽ ይበልጡንም የትልልቅ ወንዶች ሚስቶች የመሆናቸውን ጉዳይ ልብ ይሏል፡፡)

ውርድወት የመብት ጥሰቱ ያንገሸገሻት በደሉ በራሷ ላይ ከደረሰ በኋላ አይደለም። ገና ከጅምሩ በሌሎች ሴቶች ላይ ሲደርስ ይታይ የነበረው በደልና ጭቆና በውስጧ ሞልቶ እስኪፈስ ደርሶ አንገሽግሿት ስለነበር፤ በውስጧ ታብሰለስለውና አደባባይ ባትወጣም ቢያንስ በሰፈሯ ተቃውሞዋን በይፋ ታቀርብ ነበር። እልሁና ቁጭቱ ወደ ትግል ሜዳ እንድትሰማራ ቀድሞም ቢሆን መደላድል ሆኗታል፡፡

ከትልቅ ቤተሰብ የተገኘችና ለትልቅ ሰውም የተዳረች ቅምጥል ሴት ሆና ሳለ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጭቆና ለማስወገድ ምቾቷን ሁሉ ትታ፣ ክረምትና በጋ ሳትለይ፣ ዝናቡና ሃሩሩ ሳይፈትናት፣ ረሀብና ጥማቱ ሳይበግራት፣ ከሰፈር ሰፈር፣ ከቀበሌ ቀበሌ፣ ከወረዳ ወረዳ አብዛኛውን ጊዜ በእግሯ እየተንከራተተች አመጹን በተደራጀ መልኩ በብቃት መምራትና ማስተባበር መቻሏ የተለየች ሴት ያሰኛታል።

ውርድወት የሰፈሯን ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆን ታዋቂው ዴሰነ ጀፎረ ላይ የተሰየመውን የኧዣውን ሸንጎ አንቀጠቀጠችው። ፍትህ ያጣችው የሴቶች ትግል አስተባባሪ አጋሮቿን እየመራች በይግባኝ ሙግቷን ቀጠለች። የጆካ ላይ የተሰየመውን ከፍተኛውን ወይም ይግባኝ ሰሚውን የጉራጌ ሸንጎ መላ አሳጣችው። ፈተነችው። ተፈታተነችው። የማኅበረሰቡን ጎታች ልማዶች አጥብቃ ረገመች። አማረረች። ኮነነች። በመድረክ ላይ የቀረበ ቲያትር ወይም ፊልም የሚመስል አጓጊ፣ ሳቢና ማራኪ ክርክር፣ ወይም እንደዛሬው መደበኛ ፍርድ ቤት መራር ሙግት ነበር ውርድወትና የትግል አጋሮቿ በየጆካው የጉራጌ ቕጫ ችሎት ፊት ያካሄዱት፡፡

በመጨረሻው የቝ ባሕላዊ ሸንጎ ችሎት ወቅት ከዚያ ቀደም አብረዋት ሲታገሉ የቆዩት ሴቶች በተለያየ የባሎቻቸው ተንኮል (መደለያ፣ ማስፈራርያ፣ ድብደባ፣ ወዘተ) ተጠልፈው በመራራው ትግል ወቅት እስከፍጻሜው ከጎኗ ሆነው አብረዋት ዳር ሊደርሱ አልቻሉም። ይህም ሆኖ ግን ውርድወት ካነሳቻቸው የሴቶች የመብት ጥያቄዎች ከፊሎቹ ተመለሱላት።

በመልካም አስተዳደር፣ በፍትሐዊነት፣ ጎጂ ልማዶች እንዲከስሙና ጠቃሚ ባሕሎች ከትውልድ ወደትውልድ እንዲሸጋገሩ በሚሠራው አኩሪ ተግባሩ በጉራጌ ሕዝብ ዘንድ እጅግ የሚከበረው ሸንጎ ምንም አማራጭ ስላልነበረው በጥያቄዋ መሰረት ለውርድወት አንቱ እንዲነሳላት ወሰነ፤ ተነሳላት፤ ረታች፤ ኣሸነፈች፤ ነጻነቷን ተቀዳጀች። የመጀመሪያውን ባሏን ፈትታ ሁለተኛው ባሏ የሆነውን ኤሰሓርብ ፍጋን አገባች። ከዚህ የተነሳ እስከዛሬ ለኢኮኖሚ፣ ለፖለቲካና ለማኅበራዊ መብቶቻቸው ሊታገሉና ወደፊትም ለሚታገሉ የኢትዮጵያና የዓለም ሴቶች የፆታ ተጋድሎ ፋና ወጊ የሆነች ቆራጥ ታጋይ ኢትዮጵያዊት ናት ውርድወት፡፡

በደልን ወይም ጭቆናን ያለመቀበል ተፈጥሮ፣ አንሶ ያለመታየት ስሜት፣ እልህ ወይም ቁጭት፣ አስተዋይነት፣ የተጋድሎ ፈቃደኛነትና ተነሳሽነት፣ በራስ መተማመን፣ ጠንካራ የይቻላል መንፈስና የትግል ወኔ፣ መስዋዕትነት የመክፈል ዝግጁነት፣ ለሌሎች ምቾት ራስን አሳልፎ የመስጠት ቁርጠኝነት፣ የለውጥ ፍላጎት፣ አሻግሮ ነገን የማየት አቅም፣ የፆታ እኩልነትና የመብት መከበርና የአካታችነት ጥያቄ፣ ወዘተ. በዚያች በውበቷ ወደር ለሌላት ወጣት የሀብታም ልጅ፣ የጀግና ሚስት የትግል መነሳሳት አቀጣጣይ መነሻዎች ነበሩ። የኋላ ኋላ የባሎቻቸውን ተንኮል አሸንፎ መውጣት ቢሳናቸውም በአመጹ ለተሳተፉት ለአብዛኞቹ ሴቶችም ይህን ባሕርይዋን በተወሰነ ደረጃ አውርሳ ነበር።

በመጨረሻም ሃሳባችንን ስናጠቃልል የጉራጌ ሴቶች ያነሷቸውን ጥያቄዎች ቀደምት የሴቶች የመብት ትግል አነሳሾች ካነሷቸው ጥያቄዎችና ካነሱበት ወቅት ዓውድ ጋር በጥቂቱ አዛምደን ብንመለከተው የተነሳንበትን ዓላማ ይበልጥ ያጎላልናል። ከ9ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የሴቶች የፆታ እኩልነት ጥያቄ (ንቅናቄ) በአንዳንድ የአውሮፓና የአሜሪካ ሀገሮች ብቅ ብቅ ሲል ታይቷል። በኢትዮጵያም በጉራጌ ምድር እንዲሁ በተመሳሳይ ጊዜ ወይም እንዲያውም ትንሽ ቀደም ብሎም ሊሆን ይችላል፡፡

የተነሱትም ጥያቄዎች ሴቶች ተገቢው ክብር ይሰጠን፤ ጭቆናውና አድልዎው ይብቃን፤ የኢኮኖሚ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ መብቶቻችን ሳይሸራረፍ ይከበሩ፤ እኩልነታችን ይጠበቅ፤ በማሕበረሰቡ ውስጥ ያለን የማይተካ ሚና እውቅና ይሰጠው፤ የሚሉና የመሳሰሉ ነበሩ። በቃቄ ውርድወት የተመራው የጉራጌ ሴቶች አመጽም ከሞላ ጎደል እነዚህ መብቶች እንዲከበሩ የሚጠይቅ ነበር፡፡

ስለዚህ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ (በተለይም ለመገናኛ ብዙሃን፣ ለምሁራን፣ ለኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ለሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለባሕል ሚኒስቴር በተለይም ለፌዴራል ቅርስ ጥናትና ልማት ባለስልጣን፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ላላቸው ሌሎችም አካላት በአክብሮት የሚጠይቀው ወይም የሚያሳስበው ወይም የሚያቀርበው አቤቱታ አለው። ይኸውም የጉራጌ ሴቶች አመጽ በወቅቱ ወደሌሎች ግዛቶችና ጎረቤት ሀገሮች ሳይስፋፋ የተቀጨ ቢሆንም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በጉራጌ ሴቶች አማካኝነት በተደራጀ እና በአደባባይ በተካሄደ የሴቶች የመብት ትግል አቀጣጣይነት ያደረገችው አስተዋጽኦ በየመድረኮቹና ቢያንስ በራሳችን የውስጥ የታሪክ ድርሳናት እውቅና እንዲያገኝ ቢደረግ እንደ ሀገር የጋራ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል ደፋር አስተያየት ያቀርባል። በቅድሚያ ግን የተነሳውን ትልቅ ሃሳብ ወይም መረጃ ከዚህም በላይ አንጥሮ የማረጋገጥ ሥራ መሠራት ሊኖርበት ይችላል። በዚህ ጉዳይ ላይ የጉራጌ ማሕበረሰብ ባለድርሻዎች ሚና ግን ከሁሉም የበለጠ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

በተስፋዬ ጐይቴ

Recommended For You