አገልግሎት ለማግኘት ተቋሙን በእንባ ደጅ የሚጠኑ ቅሬታ አቅራቢዎች

ምድረ ግቢው የደበዘዘ ተቋማዊ ገጽታ ይስተዋልበታል። ወደዚሁ ሪፎርም የዳበሰው ወደማይመስለው የትምህርት ስልጠና ባለስልጣን መረጃ ፍለጋ ለቀናት መለስ ቀለስ ባልንባቸው ጊዜያት ሁሉ በቅጥር ግቢ ውስጥ በርከት ያሉ ባለጉዳዮችን አስተውለናል። ወደ ቢሮ ስንመለከትም አብዛኛዎቹ በሮች ጥርቅም ብለው ተዘግተው ይታያሉ። በተዘጉት የቢሮ በሮች አካባቢ ባለጉዳዮች ወዲህ ወዲያ ይላሉ። ማንን ምን መጠየቅ ጥፍት ያለባቸው ይመስል ግራ ተጋብተዋል። ፊታቸው በድካም ከመጠውለጉ በተጨማሪ ስልችት ብሏቸው በየጥጋጥጉ ይታያሉ። ከተገልጋዮች ፊት የሚነበበው ድካምና ተስፋ መቁረጥ ነው፡፡

የምርመራ ቡድኑ ጋዜጠኞች ይህን ያስተዋልነው በአንድ ቀን አሊያም በሁለት ቀን እይታ ሳይሆን በብዙ ቀናት ምልልስ ነው። የመመላለሳችን ምክንያት ደግሞ ልክ ዜጎች፣ የትምህርት ማስረጃቸውን ትክክለኛነት በማረጋገጥ ለደረጃ እድገትም ሆነ ለውጭ ሀገር ጉዞ አስፈላጊ የሆኑ የትምህርት ማስረጃዎቻቸውን ለማረጋገጥ ከተለያዩ የሀገሪቱ ጫፍ እንደመምጣታቸው እኛም ተቋሙ መረጃ ይሰጠን ዘንድ ነው። ታድያ በአጭር ቀን የተቋሙን አገልግሎት አግኝተው እና ሀሳባቸውን አሳክተው ወደየመጡበት ለመመለስ አልመው የመጡ ባለጉዳዮች በተቋሙ የጠበቃቸው አገልግሎት ቢኖር ካሰቡት በተቃራኒው ያለው ነው፡፡

ብዙዎቹ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ አገልግሎት ፍለጋ የመጡ ናቸው። ቅጥር ግቢው ከብዙዎች ተቋማት አኳያ ሲታይ ገና ያልታደሰ በመሆኑ ባለጉዳዮች በየውሃ ልኩ ኩልኩል ብለው ይቀመጣሉ፤ ገሚሱም ማለቂያ ለሌለው ቀጠሮ እንደሚዳረግ ቢያውቅም ሰዓቱን በመቆም ያሳልፋል። በግቢው የሚታዩ ባለጉዳዮች ከወጣት እስከ ጡረታ ለመውጣት በጣት የሚቆጠር ዓመታት የቀራቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ ሕጻናት ያዘሉም ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የምርመራ ቡድን ጋዜጠኞች ባለስልጣኑ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በመጠየቅ ለሕዝብ ለማድረስ ጥረት ሲያደርግ የነበረው ለወራት ያህል ሲሆን፣ በእነዚያ ጊዚያት ሁሉ ጥቂት ለማይባሉ ቀናት ወደባለስልጣኑ በመመላለስ ልክ እንደ ባለጉዳዮቹ ሁሉ ደጅ ለመጥናት ተገድዷል፡፡

ልጇን አዝላ የባለስልጣኑን ደጅ ስትጠና ካገኘናት መካከል አንዷ፣ ‹‹ሲስተም የለም›› በሚል ምክንያት በመመላለስ አንድ ሳምንት ያስቆጠረች መሆኗን በምሬት ትናገራለች። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የቅርቤ የምትለው ዘመድ ስለሌላትም ገላን ካለችው እህቷ ቤት በማረፍ ከገላን የባለስልጣኑ መሥሪያ ቤት የሚገኝበት ሽሮ ሜዳ በነጋ ጠባ ትመላሳለች። ልጅ አዝላ መመለሱ ስልችት ሲላት ‹‹ገብቼ አልቅሼ ለመንኳቸው›› ስትል ትገልጻለች፤ ይሁንና “ሲስተም የለም” የሚሉት ነገር በመኖሩ ሊሳካልኝ አልቻለም›› ስትል ሀሳቧን በሲቃ ትገልጻለች፡፡

እርሷ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በጥበቃ ሥራ ላይ የተሠማራች ሲሆን፣ ከምታገኘው ብር እንደምንም በመቆጠብ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ለመማር በቃች። ይህንኑ የትምህርት ማስረጃዋን ለማረጋገጥ ወደ ባለስልጣኑ መጣች። እንዳሰበችው ግን ማስረጃዋን አረጋግጣ ፈጥና ወደ ሥራ ገብታዋ መመለስ አልቻለችም። ሕጻን ልጇን ይዛ የባለሥልጣኑን ደጅ በመጥናት ሳምንት አስቆጥራለች። ወዲያ ደግሞ የእራሷንም ሆነ የቤተሰቧን ፍላጎት አፍና ካለቻት ጥቂት ገንዘብ ዲግሪዋን የመማሯ ምስጢር ከጥበቃ ሥራ ለመላቀቅ ነበር። ይሁንና ጉዳይዋ ቶሎ ባለመፈጸሙ ልትወዳደር ያሰበችበት ጊዜ ሊተላለፍባት በመሆኑ ጭንቅ ብሏታል። ‹‹ዲግሪ ይዤ ዛሬም በር ላይ ልቀመጥ ነው›› ስትል ታማርራለች፡፡

ሌላዋ ቅሬታ አቅራቢ ደግሞ ከኅዳር ጀምሮ እስከ ሚያዚያ ድረስ መመላለሷን ትናገራለች። ‹‹የተማርንበት ኮሌጅ ችግር ቢኖርበት እንኳ መጠየቅና ማስተካከል የሚገባው እራሱ ኮሌጁ ሲሆን፣ ይህን ደግሞ ጠይቆ ማስተካከል የሚኖርበት ባለስልጣኑም ጭምር ነው›› ስትል ምልልሱ አማርሯት ትናገራለች። ‹‹ይህ ጎደለ፤ ያኛውም የለም” በሚል ባለጉዳይን ለወራት ያህል ማመላለስ አግባብነት የለውም›› ስትል ትገልጻለች። ይህ የኦንላይን ምዝገባ ይሉት ነገር ደግሞ የተቀመጠው ሊንክ የማይከፍት መሆኑ በእራሱ አንዱ አንከራታች ነው በማለት ታስረዳለች።

ሌሎች ከጅማ የመጡ ባለጉዳዮች ደግሞ ከቤታቸው ከወጡ ድፍን አስራ አምስት ቀን እንዳለፋቸው ይናገራሉ። እነዚህ የሪፍት ቫሊ ኮሌጅ ተመራቂ የሆኑ የመንግሥት ሰራተኞች፤ ሶስቱም ሴቶች ናቸው። የመጡትም የትምህርት ማስረጃቸው እንዲረጋገጥላቸው ነው።

ከመካከላቸው አንዷ ባለችበት መስሪያ ቤት የምትሠራው በሰው ሀብት ውስጥ ነው። ‹‹ዲግሪዬን የተማርኩት የሥራ ደረጃዬን ከፍ ለማድረግ ነው፤ እዚያው ሰው ሀብት ውስጥ የመቅረት ሕልም የለኝም። ቶሎ የትምህርት ማስረጃዬ ተረጋግጦ ተወዳድሬ ቡድን መሪ መሆን እሻለሁ። ምክንያቱም የተማርኩት ባለሁበት እንድረግጥ አይደለም። ካለሁበት እልፍ ለማለት ነው›› ትላለች። ሰው ሀብት ላይ ተመድባ መሥራት ከጀመረች ሰባት ዓመታት እንዳለፋት ተናግራ፤ አሁን ግን የቡድን መሪነት መወዳደር የሚያስችለኝ ደረጃ ላይ እገኛለሁ ስትል ታስረዳለች። ይሁንና የትምህርት ማስረጃዬ ቶሎ የማይረጋገጥ ከሆነ ሕልሜ ይጨነግፋል ስትል ስጋቷን በእንባ ጭምር ገልጻልናለች።

ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ እንደምትለው፤ ከጅማ ስንመጣ በአንድ ቀን ቢበዛ ደግሞ በሁለት ቀን ጉዳዬን ጨርሼ እመጣለሁ በሚል ብንመጣም ጉዳያችን ሳይፈጸም ሁለት ሳምንት ተቆጠረ። የተማርነው ሪፍት ቫሊ ሲሆን፣ ሪፍት ቫሊ የእናንተን ነገር ጨርሻለሁ ብሎ በደብዳቤ ወደ ባለስልጣኑ መርቷል። ባለስልጣኑን ስናናግር ደግሞ ከእነርሱ መካከል ‹‹እንዲያውም እናንተ የትምህርት ማስረጃችሁን ገዝታችሁ ነው›› እስከማለት የደረሱ አሉ ስትል ትገልጻለች። እኛ የትምህርት ማስረጃችንን ገዝተን ቢሆን ‹አረጋግጡልን› በሚል ወደባለስልጣን መስሪያ ቤት ለምን እንመጣ ነበር? ስትል ትጠይቃለች። በጉዳዩ እና በምልልሱ ተሰላችተን ስናለቅስ እንኳ ምላሻቸው ‹‹ብታለቅሱ ምን ታመጣላችሁ›› የሚል ነው ትለናለች፡፡

እኛ የተማርነው ከልጆቻችን ጉሮሮ ነጥቀን ነው። አሁን በመሥሪያ ቤታችን ምደባ አለ ሲባል መጣን፤ የመጣነው ለትራንስፖርት እንኳ ተበድረን ነው። እዚህ ለአንድ ቀን አዳር የምንከፍለው አንድ ሺህ ብር ነው። በዚህ መልኩ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ይባስ ብሎ በባለስልጣኑ እየታየን ያለው እንደ ሕገ ወጥ እና ዱርዬ ነው ስትል ቅር ተሰኝታ ትናገራለች። እኛ ያለንበትን ሁኔታ ቤተሰብ እራሱ አይረዳንም ስትልም ሳግ እና እንባ በተቀላቀለው ንግግር የውስጧን ትገልጻለች፡፡

አንደኛዋ ቅሬታ አቅራቢ አዲስ አበባ ከሳምንታት በላይ በመቆየቷ ባለቤቷ ሊያናግራት ፈቃደኛ አልሆነም። ስልክ ስትደውልለት አያነሳም፤ መልሶም አይደውልላትም። እርሷ ግን ጠዋት ጠዋት በብርድ እና ቁር የባለስልጣኑን ደጅ ትጠናለች። የያዘችውንም ገንዘብ በመጨረሷ ግራ ተጋብታለች።

ሴቶቹ የመጡት፤ ሥራ፣ ልጅ፣ ቤት እና ኑሯቸውን ትተው ነው። ከእነርሱ ጋር የመጡ በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎችም ነበሩ። እነዚያ ሰልችቷቸው ወደመጡበት መመለሳቸውን ይናገራሉ። ቢችሉ በእነርሱ ውክልና ጉዳያቸውን ያስፈጽሙላቸው ዘንድ አደራ ትተው መሄዳቸውን ነው የሚናገ ሩት።

ቤተሰቦቻቸውን በአጭር ቀን ጉዳያችንን ፈጽመን እንመለሳለን ብለው ተስፋ ሰጥተው የመጡ ተገልጋዮች፤ በዛሬ ነገ ያለሙት ያሰቡት ሳይሳካ ለትራንስፖርት እንግልትና ለአላስፈላጊ ወጭ የተዳረጉ መኖራቸው የዝግጀት ክፍላችን በተለያየ ጊዜ ወደ ተቋሙ በማምራት ከተገልጋዮች አንደበት የሚሰማ የብሶት ድምጽ ነው። ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የመጡ ዜጐች እንግልት የሚዳረጉበት ተቋሙ የኢፌዴሪ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ነው።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከጅማ የመጡ ተገልጋይ እንደሚገልጹት፤ ልጆቻቸውና ባለቤታቸው ቶሎ እመለሳለው ብለው ቢመጡም፤ በተቋሙ የገጠማቸው ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። ማስረጃቻው እንዲረጋገጥላቸው ባለስልጣኑን ሲጠይቁ የተማራችሁበት ተቋም የትምህርት ማስረጃችሁን አልላከም የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸው ወደተማሩበት የትምህርት ተቋም ተጨማሪ ወጭ ተዳርገው ሲጠይቁ ለተቋሙ መላካቸውን የሚያሳይ የላኩበትን ደብዳቤ በማስረጃ አስደግፈው እንደነገሯቸው ያስረዳሉ።

ቅሬታ አቅራቢዋ እንደሚሉት፣ ድጋሚ ወደ ባለስልጣኑ በማምራት ሲጠይቁ የተሰጣቸው ምላሽ የለም፣ ምን አልባትም የትምህርት ማስረጃችሁ ፎርጅድ ወይም ሀሰተኛ ሊሆን ይችላል የሚል ሞራል የሚሰብር ምላሽ እንደተሰጣቸው እምባ እየተናነቃቸው ይናገራሉ።

የትምህርት ማስረጃቸውን ለማረጋገጥ ወደ ተቋሙ ያቀኑት ሌላኛው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ተገልጋይ እንደሚናገሩት፤ በተቋሙ የትኛው ቢሮ ምን አገልግሎት እንደሚገኝ መረጃ የሚሰጥ አካል የለም። ነገር ግን ጥበቃዎች የሚመጣውን ተገልጋይ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈ ነገር እንዲያነብ ይጠቁማሉ። እርሳቸውንም

የገጠማቸው ይኸው ነው፡፡

ሰሌዳው ላይ የተለጠፈው ምዝገባ የሚካሄድበት ድረ ገጽ ብቻ ተጠቅማችሁ ተመዝገቡ እና በስልክና ኢ-ሜል መረጃ ሲገለጽላችሁ ትመጣላችሁ የሚል ነው ይላሉ። በመረጃው መሰረት በሞባይል እና በኮምፒውተር በተደጋጋሚ ሲሞከር የተለጠጠፈው መጠቆሚያ በቀላሉ ተደራሽ የሚሆን አይደለም። ከዚህ የተነሳ የሚሉትና የለጠፉት ነገር የሚገናኝ አለመሆኑን ይገልጻሉ።

ድረ ገጹ ለተደጋጋሚ ጊዜ መሞከራቸውን የጠቆሙት ተገልጋዩ፤ ሊሠራላቸው አልቻለም። ድረ ገጹ ለሳምንት ቢሞክሩም ሊሳካላቸው እንዳልቻለና ከተቋሙ ውስጥ ለሚያውቁት ሰው ደውለው ኢንተርኔት ቤት ሂደው ይመዝገቡ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ያስረዳሉ። እዚያው በተቋሙ በር አካባቢ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ ስላሉ ወደ እነርሱ በማምራት በመቶዎች የሚቆጠር ብር ከፍለው እንደተመዘገቡ ያስረዳሉ። ጉዳዩን ባጤኑ ጊዜ ይህ ሁኔታ ለሌላ ሰው የማይከፍት ለእነርሱ ሲሆን የሚከፍትበት መንገድ ቅሬታ የሚያስነሳ ሆኖ እንዳገኙት ያመለክታሉ። ድረ ገጹ ማንኛውም ሰው በቀላሉ በስልኩ እንዲሞላ መሆን ሲገባው ለእንግልት እና ለብዝበዛ የሚዳርግበት ሁኔታ መኖር እንደሌለበት ያላቸውን ቅሬታ ይገልጻሉ።

ተገልጋይ ሲቸገር “ምን ላግዝህ?” ብሎ መረጃ የሚሰጥ አንድም ሰው ፈጽሞ የለም የሚሉት ተገልጋዩ፤ ተከፍሎም ቢሆን መረጃዎች ሲጫኑ በጣም ያስቸግራል። ስለዚህ መጀመሪያ መረጃውን ለማስገባት ጨለማ ነው። ምክንያቱም በራስ ስልክ ወይም ኮምፒውተር ለመግባት አይቻልም።

ውጣ ውረዱን አልፈው ካመለከቱ በኋላም ለወራት ምንም አይነት መረጃ በኢ-ሜልም ሆነ በስልክ እንዳልተላከላቸው የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢው፤ “የት ደረሰ?” መረጃው ብሎ መጠየቅ አይቻልም። ኢ-ሜል ከስድስት ወራት በላይ ጠብቀዋል።

ምድረ ግቢው ከገጽታው ጀምሮ ተገልጋይ ለመቀበል ምቹ ሁኔታ የለውም የሚሉት ተገልጋዩ፤ በተለይም ደግሞ ከለውጡ ወዲህ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት ተቋማትን ለሥራ አመቺ ሁኔታ እንዲኖራቸው የተጀመረው እንቅስቃሴ ቢኖርም፤ ባለስልጣኑ ግን ገጽታውን እስካሁን ያልቀየረ እና በድሮው ገጽታው ያለ ነው ይላሉ። አገልግሎቱም በተመሳሳይ እንደሆነም ነው የሚናገሩት። ስለዚህ ተቋሙ ወቅቱን እና ዘመኑን የሚመጥን አይደለም። አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ገና ምን አይነት መረጃ እንደሚጠየቁ ሳያውቁ በተሰላቸ መንፈስ “ሲስተም የለም” የሚል ምላሽ እንደሚሰጡ ያብራራሉ። በአጠቃላይ መረጃቸው የተረጋገጠላቸው ባመለከቱ አንድ ዓመት ሊሞላ ሲል ነው። ይህ የሚያሳየው አገልግሎቱ ብልሽት ያለበት መሆኑን ነው ይላሉ።

እርሳቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሆነው የገጠማቸውን እንግልት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መጥተው አገልግሎት ከሚፈልጉት ጋር በማነጻጸር ሲገልጹ፤ የገጠማቸው ወደ ተቋሙ መጥተው የሚያለቅሱ በርካታ ናቸው። ቅሬታ እንኳን የማቅረቢያ ሥርዓት ተቋሙ አልዘረጋም። ተቋሙ የሕዝብ ለቅሶና ሮሮ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰማበት ነው። አጭር የመልዕክት መቀበያቸው ለይስሙላ የተቀመጠ አንድ ቀን እንኳን ተነስቶ ምን እንደሚጠየቅ የማይቀበሉበት ነው። በዚህ ዘመን ሊኖርና ሊታይ የማይገባው አገልግሎት እየሰጠ ያለ ተቋም ነው። ስለዚህ የሚመለከተው አካል ተቋሙን ፈትሾ ማስተካከል ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የተቋሙ ሠራተኛ የሆኑ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ በበኩላቸው፤ አንድ የትምህርት ተቋም ይሰጥ የነበረውን የትምህርት መርሃግብር ሲዘጋ ምን አይነት የትምህርት አይነት እንደሆነ ለሕዝብ መግለጽ አለበት ይላሉ። በተቋማት ላይ የሚወሰደውን ርምጃ ለሕዝብ ከማሳወቅ ይልቅ አፍኖ መያዝ ይስተዋላል ሲሉም ይናገራሉ። ከሥርዓቱ እየወጡ ያሉ ተቋማት በምን ምክንያት እንደወጡ መግለጽ እየተገባ አልተገለጸም።

የተቋሙ የውስጥ አደረጃጀት ተቋማዊ ሥራዎችን በብቃትና በጥራት ለመወጣት የተደራጀ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ሁሉም በራሱ ቢሮውን ቆልፎ የተቀመጠ ግላዊና ቡድናዊ መልክ የያዘ መስሏል። ይህም ከተቋማዊ አሠራር ውጭ ሆኖ እየታየ ነው። ስለሆነም የተቋሙን ራእይና ተልእኮ ለማሳካት የሚያስችል ቁመና ላይ አይደለም። ለተገልጋዮች ፈጽሞ ክብር የሌለው ተቋም ሆኗል ሲሉ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ።

የአገልግሎት አሰጣጡን በድጂታል አድርገናል የሚለው ተቋሙ፣ አገልግሎት ለማግኘት ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወር ጊዜ የሚወስድ አገልግሎት ምን ይሉት ድጂታል አገልግሎት ነው የሚሉት መረጃ ሰጪው፤ ከጅማ፣ ሐረር፣ ድሪዳዋ እና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ረጅም ርቀት ተጉዘው በመምጣት ከ15 በላይ ቀናት ቆይተው ገንዘባቸውን ጨርሰው ምንም አገልግሎት ሳያገኙ ተመልሰው በመሄድ ድጋሚ ለአገልግሎት የመጡ ዜጐች የተቋሙ አገልግሎት ምን ያህል የወረደ መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉ በቁጭት ያነሳሉ።

በአሁኑ ጊዜ በተቋሙ ለግላቸው የተመቻቸው ሰዎች በዝምታ የሚኖሩበት አገልግሎት አሰጣጡ ገደል የገባበት ተቋም ሆኗል። በየዳይሬከቶሬቱ የተመደቡ ሰዎች ለግል ፍላጐት በሚመች መልኩ እንጂ ተቋሙ ለሚሰጠው አገልግሎት በሚመች መልኩ የተመደቡ አይደሉም። ተቋሙን ወደፊት የሚወስድ ሀሳብ ማራመድ እንደ ሀጢአት የሚታይበት ነው። ለተገልጋይ ተቆርቋሪ መሆን የሚችል ሰው ተቋሙ ውስጥ እየጠፋ ነው ይላሉ።

ሌሎች ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚሉት፤ የትምህርት ማስረጃቸውን ለማረጋገጥ ከመላ ኢትዮጵያ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠን ከመጣን በኋላ ከፍተኛ እንግልት ይገጥመናል። ለምሳሌ መረጃ የሚያረጋግጡት ባለሙያዎች መረጃው መላኩን ወደ ዳታቤዝ ዲፓርትመንት ቢሮ ቁጥር 238 ሂዱ ይሉናል፤ ስንሄድ መልሰው ወደ ቢሮ ቁጥር 109 ሂዱ ይላሉ። ከሄድን በኋላም ስሙ በመረጃ ቋቱ ውስጥ አልገባም የሚል ምላሽ ይሰጠናል። ይህ ምላሽ ለእኛ አይገባም። ምክንያቱም የተማርንበት ተቋም መረጃ ልኪያለው ብሎን ነው የምንመጣው። ነገር ግን የለም ማለታቸው ለሙስና በር የሚከፍት መሆኑን ምላሻቸው ለጥርጣሬ ዳርጎናል ይላሉ፡፡

ተቋሙ፣ በትምህርት ተቋማት ላይ በሚያደርገው የቁጥጥር ሥራ በበርካታ ኮሌጆች ላይ የማስተካከያ የእርምት እርምጃ የወሰደ ቢሆንም በአዋጁ መሰረት ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አልቻለም። ነገር ግን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አደረጃት፤ ስልጣንና ተግባር መወሰን ደንብ ቁጥር 515/2014 እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 60 (2) መሰረት ባወጣው ደንብ አንቀጽ 21 እንደሚገልጸው፤ የተሠሩ ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶች እንዲሁም የተወሰዱ ሕጋዊ እርምጃዎችን በተገቢ መንገድ መረጃዎችን በልዩ ልዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለማሕበረሰቡ ተደራሽ ያደርጋል።

የተቋሙ የውስጥ የመረጃ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፤ ተቋሙ አገልግሎት ሰጭ ቢሆንም እያከናወነው ያለው ተገልጋይን ማጉላላት ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ከለውጡ ወዲሀ በርካታ የመንግሥት ተቋማት ሪፎርም አድርገው ብዙ ለውጥ አምጥተዋል። ባለስልጣኑ ሪፎርም ያደረገበት መንገድ ግን የተቋሙን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ አሁን ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ውስጥ እንዲገባ አድርጓል።

ሕዝቡ ማግኘት ያለበትን መረጃ እያገኘ ስላልሆነ ኮሌጆች ምን አይነት ፕሮግራም በምን እንዳላቸው አውቆ እንዲማር እየተደረገ አይደለም።

ከሰነድ የተገኙ ማስረጃዎች

ባለስልጠኑ ስለአገልግሎት አሰጣጡ ማብራሪያ እንዲሰጠን በደብዳቤ ቁጥር TL1/2/4031 በቀን ሕዳር 04/2017 ተቀቋማችን ለሕዝብ ሚዛናዊ ዘገባ ያድርስ ዘንድ ቢጠይቅም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። የዝግጅት ክፍላችን ተቋሙ በቀጣይ ምላሽና ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሲሆን የትምህርት ሚኒስቴርን እና ተቋሙን የሚከታተለውን ቋሚ ኮሚቴ በማናገር መረጃውን ለሕዝብ የምናደርስ ይሆናል።

የጋዜጠኞች ትዝብት

የዝግጅ ክፍላችን ባለስልጣኑ እያከናወነው ስላለው የሥራ እንቅስቃሴ እንዲሁም ዜጎች ላቀረቡት አቤቱታ ምላሽ እና ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ተቋሙ በተደጋጋሚ ብንደርስም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው የአገልግሎት አሰጣጡ ችግር ያለበት መሆኑ፤

የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ስለተቋሙ የሥራ እንቅስቃሴ ማብራሪያ እንዲሰጡን እንዲሁም የሚመለከተውን አመራር እንዲያገናኙን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው በተቋሙ ተናብቦና ተግባብቶ የመሥራት ባሕል እንደሌለ መታዘብ ችለናል።

በምርመራ ቡድን ጋዜጠኞች

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You