የኢንስቲትዩቱ ምርምር ውጤት – የአቦካዶ ዘይት መጭመቂያ ቴክኖሎጂ

የምርምር ተቋማት የማህበረሰቡን በአጠቃላይ የሀገሪቱን ችግሮች በጥናትና ምርምር መለየት፣ ለችግሮቹ መፍትሄ ማመላከት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን በማውጣትና የፈጠራ ውጤቶቹ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ ላይም መሥራት ይኖርባቸዋል።

ከዚህ አኳያም ተቋማቱ ሀገር በምትፈልገው ልክ ሲንቀሳቀሱ ብዙም አይስተዋልም፤ በዚህም በተደጋጋሚ ተተችተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እነዚህ ተቋማት በጥናትና ምርምሩም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት በኩልም ለውጦች እየታዩ ይገኛሉ። በእዚህ በኩል የግብርና ምርምር እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ይጠቀሳሉ።

ከእዚህም መካከል የባዮና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዩት ይጠቀሳል። ኢንስቲትዩቱ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ያደርጋል። በቅርቡም በ 11 የምርምር ውጤቶቹ የአእምሮዊ ንብረት ጥበቃ ባለቤትነት መብት አግኝቶባቸዋል። ከእነዚህ የምርምር ውጤቶች አንዱ አቦካዶ በመጭመቅ ዘይት ማምረት የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ነው፡፡

እንደሚታወቀው አቦካዶ በርካታ ጥቅሞች ያሉት የፍራፍሬ አይነት ነው። አቮካዶ ለምግብነት የሚውልና ለጤና ተስማሚ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በሀገራችን ተልጦ ለምግብነት ከመዋሉ ባሻገር፣ ጭማቂው /ጁሱ/ ደግሞ በእጅጉ ተወዳጅ ነው። ለተለያዩ ምግቦች መሥሪያነትም ይውላል። በተጠቀሱት መንገዶች ለምግብነት ከመዋሉ ባሻገር ዘይት ይመረትበታል፤ ለኮስሞቲክስ አገልግሎትም ይውላል።

በባዮና ኢመርጂንግ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር እዮቤል ሙሉጌታ በተለምዶ አቦካዶን ለምግብነትና ለጁስ ከማዋል ውጪ በሌላ መልኩ ተሠርቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ሲደረግ ብዙም አይታይም ይላሉ።

ኢንስትቲዩቱ ከምግብነት ባሻገር ለብዙ ጥቅሞች ሊውል በሚችለው በዚህ የፍራፍሬ አይነት ላይ ምርምር ሲያደርግ መቆየቱንም ይገልጻሉ፤ በዚህ ምርምሩም በአነስተኛ ደረጃ አቦካዶ በመጨመቅ ዘይት ማምረት የሚያስችል ቴክኖሎጂ /ማሽን/ እውን ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የአቮካዶ መጨመቂያ ማሽኑን ከመሥራት ጀምሮ ዘይት እስከ ማውጣት ድረስ ባለው ሂደት (ፕሮሰስ) ላይ ምርምር ተካሂዷል። በተጨማሪ ከዘይቱ የውበት መጠበቂያዎችን ማምረትና ተረፈ ምርቱን ወደ ሌላ ምርት መቀየር የሚያስችሉ ምርምሮችም ተካሂደዋል። የአቮካዶ ልጣጭና ፍሬንም ወደ ከሰልና ማዳበሪያነት ለመቀየር የሚያስችል ምርምር ተደርጓል፡፡

የፕሮጀክቱ መነሻ የተገኘው ለጉብኝት ወደ ይርጋለም ኢንዱስትሪያል ፓርክ የተሄደበት አጋጣሚ ነው። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በፓርኩ የተተከለውን የአቦካዶ ዘይት መጨመቂያ ኢንዱስትሪ መመልከት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በኢንዱስትሪ ፓርኩ አቦካዶ ተጨምቆ ዘይቱ ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብ ጠቅሰው፤ በሀገሪቱ ይህንን ዘይት የመጠቀም ምንም አይነት ልምድ እንደሌለ ይናገራሉ።

ይህንን በሚገባ በማጥናት ለምንድነው የአቦካዶ አምራች አርሶ አደሮች በአቦካዶ ምርት ላይ እሴት ጨምረው ዘይቱን እያመረቱ ራሳቸውም ተጠቅመው ለገበያ ማቅረብ የማይችሉት? በሚል ሃሳብ መነሻነትም ጭምር ወደ ምርምር መገባቱን ያመላክታሉ። ‹‹አርሶ አደሮቹ የአቦካዶ ዘይት አምርተው ለገበያ እያቀረቡ ተጠቃሚ መሆን ለምን አይችሉም? ብለን አሰብን ወደ ምርምር ሥራው ገባን ›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡

ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ አይነት ተሞክሮ ስለሌለ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መመልከት የግድ ነበር ሲሉም ጠቅሰው፣ በዚህም የኬንያ ፣ የታንዛንያና የኡጋንዳ አርሶ አደሮች ተደራጅተው የአቦካዶ ዘይት እየጨመቁ ለአካባቢው ሱፐር ማርኬቶች፣ ጸጉር ቤቶች እና ትላልቅ ሆቴል እያቀረቡ ያሉበትን ሁኔታ መመልከት ተችሏል ብለዋል። ይህንን ተሞክሮ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት በፕሮጀክቱም በመጀመሪያ በአነስተኛ ደረጃ በጎጆ ኢንዱስትሪ የመጭመቂያ ማሽን ዲዛይን በማድረግ ሥራ ላይ እንዲውል መደረጉን አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱ ከትልቁ የዘይት መጭመቂያ ኢንዱስትሪ ጋር ሲነጻጻር ውጤታማነቱ ከፍተኛ ነው የሚሉት ከፍተኛ ተመራማሪው፤ የሚሰጠውም ምርት ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጸሉ። በኢንዱስትሪ ደረጃ የሚገኘው የዘይት መጠን አምስት በመቶ ያህል መሆኑን ተናግረው፣ በምርምር በአነስተኛ ደረጃ የተገኘው ቴክኖሎጂ ስምንት በመቶ ያህል ነው ብለዋል። በዚህም ከ100 ኪሎ ግራም አቦካዶ ስምንት ሊትር ዘይት ማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል። በምርምሩ የተገኘው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ከዚህ በላይ ማሻሻል እንደሚገባና የምርምር ሥራውም መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

‹ዋናው ትኩረታችን ለወጣቶች የሥራ እድል ሊፈጥሩ በሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ምርምር ማድረግ ነው›› ያሉት ተመራማሪው፣ በአነስተኛ ደረጃ አቦካዶ በመጭመቅ ዘይት ማምረት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ዘይቱን እንዲያመርቱ በሲዳማና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለተደራጁ ወጣቶች ሥልጠና በመስጠት በማሽኑ ተጠቅመው ዘይት እንዲጨምቁ ተደርጓል ብለዋል። በተለይ ዳውሮ ዞን ላይ 30 የሚሆኑ ወጣቶችን በማሠልጠን በአጠቃላይ አራት ማሽኖች በመስጠት አራት ኢንተርፕራይዞች እንዲቋቋሙ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

የአቡካዶ ዘይቱ ለምግብነት የሚውል ስለመሆኑ የማረጋገጥ ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል። በተስማሚነት ምዘና ድርጅት ላብራቶሪ ተመርምሮ የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃ ስታንደርድ እንደሚያሟላና ለምግብ ዘይትነት እንደሚውል መረጋገጡን አመላክተዋል። የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን እውቅና ለማግኘትም ጉዳዩ በሂደት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የአቡካዶ ዘይትን በውስጡ የሚገኙ ነጥረ ነገሮች ከሌሎች የዘይት አይነቶች ለየት ያደርጉታል የሚሉት ተመራማሪው፤ በተለይ የደም ግፊት፣ የልብ ህመም፣ የስኳር ህመም ላለባቸው ሰዎች ጠቃሚ ስለመሆኑ በሕክምናው ዘርፍ እንደሚመከር ተናግረዋል።

እንደ ከፍተኛ ተመራማሪው ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ የአቡካዶ ምርት በዓመት ሁለት ጊዜ ማግኘት ስለሚቻል ምርቱ ወደ ዘይት ቢቀየርና ጥቅም ላይ ቢውል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል። አንደኛ ከጤና አንጻር ተጠቃሚ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደግሞ ኤክስፖርት በማድረግ ገቢ ማግኘት ያስችላል፡፡

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው በአነስተኛ ደረጃ ምርቱ በሚገኝበት አካባቢ ወጣቶችን አደራጅቶ ዘይቱን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በማምረት ለሆቴሎችና ሌሎች ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ተደራሽነቱን ለማስፋት ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂውን ለመሥራት ሦስት ዓመታትን ያህል ፈጅቷል። ቴክኖሎጂው በጣም ቀላልና ተንቀሳቃሽ ማንም ሰው ሊጠቀምበት የሚችል ነው። በተለይ ሴቶችን ያማከለ ሲሆን፣ ከቦታ ቦታ በቀላሉ እንዲንቀሳቀስ ታስቦ የተሠራም ነው። ምንም አይነት ኬሚካል ሳያስፈልገው በጉልበት ብቻ መጭመቅ ይችላል። ኤሌክትሪክና ነዳጅ የማይፈልግ በመሆኑም በሀገሪቷ ገጠር አካባቢ ድረስ አገልግሎት መስጠት ይቻላል። በአንድ የዘይት መጨመቂያ ማሽን በቀን መቶ ሊትር ዘይት ማምረት ይቻላል። እነዚህ አገልግሎቶች ቴክኖሎጂውን ተመራጭ ያደርጉታል፡፡

የአቦካዶ የውስጡ ክፍል /ፍሬው/ ዘይት ቢኖረውም ከድንጋዩ ላይ ዘይት መጨመቅ አዋጭ እንዳልሆና እስከ አሁንም እንዳልተሞከረ ገልጸዋል። ድንጋይና ልጣጩን እንደ ማዳበሪያ፣ ከሰልና የእንስሳት መኖ ላሉ ምርቶች ለማዋል ታሰቦ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ አቦካዶ ከፍተኛ ምርት የሚገኝባቸው ሁለት ወቅቶች እንዳሉ የጠቆሙት ከፍተኛ ተማራማሪው፤ ቀደም ሲል በእነዚህ ወቅቶች ህብረተሰቡ ለምግብነትና ለሌላ ለሚፈልገው አገልግሎት ተጠቅሞ የተረፈውን ሲጥል ይመለከቱ እንደነበር አስታውሰዋል። ወቅቱ ሲያልፍ ደግሞ እጥረት ይከሰት እንደነበርም ገልጸዋል። አቦካዶው ወደ ዘይትነት ቢቀየር ከብክነት መታደግ እንደሚቻል ታምኖበት ፕሮጀክቱ መጀመሩን ገልጸዋል።

ተመራማሪው እንዳስታወቁት፤ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ የፋይናንስ እጥረት አጋጥሞ ነበርም፣ በሁለት ክልሎች የተወሰነ ቦታ ላይ ናሙና በመውሰድ ተሠርቶበታል። አቦካዶ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ቦታዎች ይመረታል፤ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል በብዛት የሚመረት ቢሆንም፣ ይህንን ቴክኖሎጂ ግን ሌሎች ቦታዎች ተደራሽ ለማድረግ የፋይናንስ እጥረት አጋጥሟል፡፡

በፕሮጀክቱ የተሠሩት ሦስት አይነት የዘይት መጨመቂያ ማሽኖች መሆናቸውን አመላክተው፣ የመጀመሪያው እንደ ብሎን እየጠበቀና እየላላ የሚጨምቅ (ስክሩፕረስ) መሆኑን ገልጸዋል። ይህን ለመሥራትም 76 ሺ ብር ያህል ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።

ይህ ማሽን ስክሩፕረሱ ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ በሃይድሮሊክ ፕረስ በመጠቀም በቀላሉ መጭመቅ የሚያስችለው ሁለተኛውን ትውልድ (ሁለተኛው ማሽን) ተሠራ ሲሉ አስታውቀዋል። ለዚህ ማሽንም 36ሺ ብር ያህል ወጪ መደረጉን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ የሁለቱ ማሽኖች ችግሮች በሚገባ ከተለዩ በኋላ ሦስተኛውን ትውልድ ማሽን መሥራት ተችሏል። ቀድሞ የተሠሩት ሁለት ማሽኖች በማዳቀል ሦስተኛውን መሥራት የተቻለ ሲሆን፤ ይህ ማሽን በጣም ቀላል አንድ ሰው ሊያነሳው የሚችል በጣም ርካሽ ከሆኑ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የብረት ቁርጥራጮች የተሠራ ነው። ማሽኑን ለመሥራት ሃምሳ ሺህ ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ሦስተኛው ቴክኖሎጂ አሁን ላይ እየተሸጋገረ ያለ ነው፡፡

እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በማምረት ለተጠቃሚው ለማድረስ ከኢንስቲትዩቱ ጋር ሊሠሩ የሚችሉ ትልልቅ ወርክሾፕ ካላቸው የመንግሥትና የግል ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የሚሠሩ ሥራዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

የበጀት ድጋፍ ያደረጉልን የውጭ ድርጅቶች ናቸው ሲሉም ጠቅሰው፣ በዚህም ሁሉም አምስት ማሽኖችን በመሥራት አራቱ ለተጠቃሚ ተደራሽ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል። እነዚህም ለባለድርሻ አካላት ተሰጥተው በትብብር የተሠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል። የክልል የሥራ እድል ፈጠራ ቢሮዎችም ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ኢንስቲትዩቱ የሚልኩበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰው፤ ኢንስቲትዩቱ ለወጣቶቹ ሥልጠና በመስጠት ቴክኖሎጂውን እያሸጋገረ መሆኑን አመላክተዋል።

የአቦካዶ ዘይት ዋጋ በጣም ውድ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በውጭ ሀገራት የአንድ ሊትር አቦካዶ ዘይት ዋጋ እስከ አራት ሺህ ብር መሆኑን ተናግረዋል። በሀገር ውስጥ ከአቡካዶ ዘይት የተቀመመ ኮስሞቲክስም በውድ ዋጋ እንደሚሸጥ መመልከት ችለናል ሲሉም ከፍተኛ ተመራማሪው አስታውቀዋል።

‹እንደ ስካይላይትና ሃያት ሪጀንሲ ያሉ ሆቴሎች ምግባቸውን በአቦካዶ ዘይት እንደሚሠሩና ይህንንም ተጠቃሚዎች በደስታ እንደሚቀበሉት ሲናገሩ ይደመጣል› ብለዋል።

‹‹የአቦካዶ ዘይት ብዙ ትኩረት ተሰጥቶት አልተዋወቀም፤ ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ ሳይቀር አይገኝም፤ አብዛኛውን ጊዜ የሚገኙት የወይራ ዘይት አይነቶቹ ናቸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እየመጣ ነው፡፡›› ሲሉ አብራርተው፣ የአቡካዶ ዘይት እየጨመቁ ለኮስሞቲክስ ምርት የሚያቀርቡ ሁለትና ሦስት ድርጅቶች እኛ ጋር መጥተው ተነጋግረዋል ብለዋል።

ዘይቱ አሁን ወደ ገበያ እየመጣ ነው ማለት እንደሚቻል ጠቁመው፣ እየተለመደ ሲሄድና በብዛት ሲመረት ደግሞ ዋጋውም በዚያው ልክ እየቀነሰ ይመጣል ተብሎ እንደሚታሰብ አስታውቀዋል።

እሴት ያልተጨመረበትን አቡካዶ ከመሽጥ ይልቅ ዘይቱን አምርቶ መሸጥ 50 በመቶ ያህል ትርፍ እንደሚያስገኝ ጠቁመዋል። አሁን በሁለቱ ቦታዎች ላይ በአነስተኛ ኢንዱስትሪ ደረጃ የአቦካዶ ዘይት እየመተመረ መሆኑንና በዚህም ለ30 ሰዎች የሥራ እድል መፈጠሩን አስታውቀዋል። የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች በቦታው ድረስ በመሄድ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እየሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በቀጣይ ለወጣቶቹ የተሰጠው ማሽን የምርት ጥራትና ያለው የገበያ ትስስር ምን እንደሚመስል በመከታተል ያንን መነሻ በማድረግ መሻሻል ያለበት እንዲሻሻል ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል። እነዚህ ማሽኖች በቀን መቶ ሊትር ዘይት እንደሚያመርቱ ጠቅሰው፣ በቀጣይ ከፍተኛ መጠን ያለው የአቦካዶ ዘይት ማምረት የሚያስችል ማሽን ለመሥራት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

በኤሌክትሪክ አንድ ማዕከል ላይ ሆኖ በቀን ብዙ ሺህ ሊትር ዘይት የሚያመርት ማሽን ለመሥራት መታቀዱንም ጠቅሰው፤ ይህንንም ኢንስቲትዩቱ ዲዛይኑን እየሠራ ለግል አምራች ድርጅቶች በማቅረብ እነርሱ ማሽኑን እያመረቱ ለተጠቃሚ ተደራሽ እንዲያደርጉ ታሳቢ የተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You