በክልሉ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከቀረበው የአቡካዶ ምርት ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

አዲስ አበባ፡– በሲዳማ ክልል በምርት ዘመኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ሺህ 500 ቶን የአቡካዶ ምርት ለተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በማቅረብ 1.1 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮ ኃላፊው አቶ መምሩ ሞኬ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሰብሎችና ስራስሮችን በስፋት ከማምረት ባለፈ ገበያን በሚመለከት የቡናና አቡካዶ ምርቶችን በብዛት ለማልማት በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

በክልሉ ከቡና ቀጥሎ አቡካዶ የኤክስፖርት ምርት መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት ከ21 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ ነባር የአቡካዶ ተክል እንደሚገኝ ገልጸው፤ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆን አዳዲስ የአቡካዶ ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑንም አስታውቀዋል።

እንደ አቶ መምሩ ገለጻ፡ በክልሉ በተያዘው የምርት ዘመንም 10 ሺህ ቶን የአቡካዶ ምርት ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማቅረብ ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአንድ ዙር ብቻ ከ3 ሺህ 500 ቶን በላይ ምርት ማቅረብ ተችሏል። ከዚህም 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

በክልሉ አቡካዶን በብዛት የማልማት አቅም ቢኖርም ሁሉም ምርት ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ እንደማይገባና ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ለገበያ እንደሚቀርብና በቀጥታም ኤክስፖርት እንደሚደረግ ጠቁመው፤ ለገበያ በሚቀርቡ ምርቶች፣ በዋናነት በአቡካዶና ቡና ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ አቡካዶና ቡና በ19 ወረዳዎች እንደሚለሙና አርሶ አደሩም በተለይም አቡካዶን በተሻሻለ ዝርያ በማዳቀል ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ተደራሽ እንደሚያደርጉ ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅትም ስድስት የአቡካዶ ዝርያዎችን በኩታገጠም እርሻ የማስፋት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ምርቱም ከቡና ቀጥሎ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነት እየቀረበ ይገኛል፤ በዚህ መነሻም በክልሉ በተለይም በይርጋዓለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ አቡካዶን የሚያቀነባብሩ ፋብሪካዎች ቁጥር 3 መድረሱንና ፋብሪካዎቹም ድፍድፍ ዘይት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅትም 172 ሺህ ሄክታር የቡና ተክል ይገኛል ያሉት ኃላፊው፤ ከዚህ ውስጥ 149 ሺህ ሄክታር ላይ የሚገኘው ምርት መስጠት የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህ ዓመትም በዋናነት 40 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ መያዙንና እስካሁን ባለው ሂደትም 37 ሺህ ቶን የቡና ምርት የመሰብሰብ ሥራ መከናወኑንም አመልክተዋል ።

ባለፈው የምርት ዘመን 25 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን አስታውሰው፤ ምርቱ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ12 ሺህ ቶን በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

የቡና ምርታማነት በሄክታር 9 ነጥብ 8 ኩንታል ከነበረበት ወደ 11 ነጥብ 04 ኩንታል የማድረስ ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል።

አምሳሉ ፈለቀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You