ከሸማችነት ወደ አምራች

ዜና ሐተታ

እንደሀገር በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሰማርተው ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አምራቾች እየተበራከቱ ነው፡፡ እነዚህም ግብርን በታማኝነት በመክፈል ሀገርን ታሪክ እየሠሩ ያሉ ምስጉን አምራቾች ሀገርን ለማሻገርም ጉልህ ሚና እያበረከቱ ነው።

በዘንድሮው ዓመትም ፈርጀ ብዙ የምርታማነት ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ቃል በተሠራ የንቅናቄ ሥራ ለዓመታት ተቀናጅቶ ባለመሥራት ተዘግተው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎች ዳግም ማምረት ጀምረዋል፡፡

አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ሥራ መግባት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ተተኪ ምርቶች እንዲመረቱ፣ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረና የኢንዱስትሪዎች የመወዳደር አቅም እየጎለበተ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ይህንን መሠረት ባደረገ መልኩ የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ “የኢትዮጵያ – አዲስ አበባ ታምርት” በሚል ንቅናቄ የፈጠራ ባለቤቶችን በማበረታታት እና ለአምራች ዘርፉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።

በዚህም ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 4 /2017 ዓ.ም ድረስ በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከተማ አቀፍ አውደርዕይ አካሂዷል። በወቅቱም ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገትና የዜጎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጉልህ ሚና እንዳላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዣንጥራር ዓባይ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዣንጥራር ዓባይ እንደገለጹት፤ በከተማዋ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በተደረገው ድጋፍ የማምረት አቅማቸውን ከአምናው 60 በመቶ ወደ 64 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የማምረት አቅም እያደገ ቢመጣም አሁንም በርካታ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል። ከአምስት ዓመት በኋላም የማምረት አቅምን ወደ 85 በመቶ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው ፤ ለዚህም የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ፖሊሲው የባለድርሻ አካላት ሚና፣ ለአምራቾች ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ቅድሚያ የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙበት ሥርዓት መፍጠር፣ የገበያ ትስስር እና የሕግ ማሕቀፎችን ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኒው ዊንግ አዲስ ጫማ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢቫኖ መስፍን በበኩላቸው፤ ፋብሪካው ጫማና ቆዳ እያመረተ ለአሜሪካ ገበያ የሚያቀርብ መሆኑን ገልጸው አሁን ላይ ሴፍቲ ጫማና ጓንት በስፋት እያመረተ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህንንም ሁለት ጊዜ ለጣሊያን ገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

አሁን ደግሞ ለመንግሥትና ለተለያዩ የግል ተቋማት ጫማዎቹን ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸው፤ ማህበረሰቡ ለሀገር ውስጥ ምርቶች ያለው አመለካከት የተሳሳተ ነው። ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ጥራት ያላቸው ምርቶች በኢትዮጵያ እየተመረቱ በመሆኑ ይህንን አመለካከት መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል።

የይርጋለም አዲስ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ዳይሬክተር ይርጋለም አሰፋ በበኩላቸው፤ ፋብሪካውን አሁን ያለበት ደረጃ ለማድረስ በርካታ ውጣ ውረዶች በማለፍ ቢሆንም ውጤቱ አስደሳች ነው። በዚህም መንግሥት የእውቀት ሽግግር እንዲደረግልን፣ ባዛሮች ላይ እንድንሳተፍ እና የገበያ ትስስር እስከመፍጠር ድረስ ድጋፎች አድርጎልናል ነው ያሉት።

ፋብሪካው ግብዓቶችን በቀጥታ ከገበሬ ተቀብሎ እሴት በመጨመር ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ያቀርባል። ይህም ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲተኩ ያደረገ ነው ያሉት ወይዘሮ ይርጋለም፤ በዘርፉ ያለው አመራር የአምራቾች እንዱስትሪዎችን ችግር ለመፍታት ትኩረት ቢያደርጉ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል። ይህም ምርትና ምርታማነት በማሳደግ እና ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠን ይረዳል። ሲሉ ተናግረዋል።

በአውደርዕይ ማጠቃለያ ፕሮግራሙ ከጥቃቃቅን ወደ አነስተኛ፣ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ለተሸጋገሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አምራቾች እና ለዘርፉ ጉልህ ሚና ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

ፕሮግራሙ ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት፣ በየደረጃው ላሉ የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች ምስጋና ቀርቧል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You