የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምን የሚያግዘው የከተማ ግብርና

ዜና ሐተታ

በአሁኑ ጊዜ በፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም በኤክስቴንሽን ሥርዓት እየተመራ ባለው የከተማ ግብርና በተደራጁ ማኅበራት፣ በተቋማት አማካኝነት ክፍት ቦታዎች ሁሉ የአትክልት ልማት፣ የእንስሳት እርባታ በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛል። በዚህ በተዘረጋው ሥርዓት የከተማው ነዋሪ የአትክልት ፍጆታውን እንዲሸፍን የሚያስችል ከመሆኑ በተጨማሪ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ አካባቢንም ከብክለት በመከላከል፣ ለእይታም ጥሩ ገጽታ በመፍጠርና የሥራ ባህልን በማዳበር ረገድ ከፍ ያለ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑ በመልካም ጎኑ ይነሳል።

የከተማ ግብርና በመልካም ጎኑ ከሚነሳባቸው አንዱ ትምህርት ቤቶች ከሚያከናውኑት የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር ጋር እንዲቀናጅ መደረጉ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የከተማ ግብርና ትምህርት ቤቶች ከሚያከናውኑት የምገባ ፕሮግራም ጋር መቀናጀቱ የትምህርት ቤቶችን የግዥ ወጪ ከመቀነሱ በተጨማሪ ከግቢያቸው ውስጥ ትኩስ አትክልት ለማግኘት፣ እንዲሁም ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር ለማወቅ ያስችላቸዋል። ስለግብርና አጠቃላይ መረጃም ይኖራቸዋል። በአሁኑ ጊዜም በከተማ ግብርና 152 ትምህርት ቤቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በልማቱ ከሚሳተፉ ትምህርት ቤቶች አንዱ በሆነው ደጃዝማች ወንድይራድ ቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተን ቅኝት አድርገናል። በትምህርት ቤቱ የተቀናጀ የግብርና ሥራ ከተጀመረ ሦስት ዓመታት ሆኖታል። ትምህርት ቤቱ ያለውን ክፍት ቦታ ሁሉ በጎመን፣ በድንችና የተለያዩ አትክልቶች ለምቶ፣ ጎን ለጎንም የወተት ላም፣ በግ እና የዶሮ እርባታ ሥራ በማከናወን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን አይተናል። ለትምህርት ቤቱም መልካም ገጽታ ፈጥሯል። የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ በልማቱ የሚያደርገውን ተሳትፎ አይተናል።

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ሰለሞን ክቤ፤ በሦስት ዓመት ሥራ የተገኘውን ውጤት ሲያዩ ሳይሠራበት ባለፈው ጊዜ ይቆጫሉ። አሁን በአትክልት የለማው ክፍት ቦታ በአረም የተወረረና ተሳቢ ነፍሳት ሳይቀሩ የነበረቡት እይታንም የማይስብ እንደነበር አስታውሰዋል። በተሠራው ሥራ ለተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር የአትክልትና እንቁላል አቅርቦትን በራስ አቅም ማሟላት መቻሉንና ትኩስ ግብዓት መቅረቡም ጤናማ ምግብ ለማዘጋጀት ማገዙን ያስረዳሉ። በአሁኑ ጊዜም 2000 የእርባታ ዶሮች አሉ። ከነዚህ ዶሮዎችም በቀን በአማካይ እስከ 1920 እንቁላል ይገኛል።

በመሆኑም ትምህርት ቤቱ የእንቁላል አቅርቦቱን ሙሉ በሙሉ በመሸፈን፣ የአትክልት አቅርቦቱን ደግሞ 60 በመቶውን በትምህርት ቤቱ ልማት በመሸፈን የምገባ መርሐ ግብሩን በማከናወን ላይ ይገኛል። በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥም ወደ 3ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ እንቁላል ለገበያ ማቅረብ ተችሏል። በምገባ ፕሮግራሙ ወተት ባይኖርም ትምህርት ቤቱ ካለው ውስን የወተት ልማት ቅድመ መደበኛ ላይ በተለያየ መስፈርት የለያቸው 21 ሕፃናት እንዲጠቀሙ እያደረገ ነው። አንድ ሕፃንም በሳምንት አንድ ሊትር ወተት ያገኛል። በአትክልት ልማት በኩልም፤ 19ሺ300 ካሬ ሜትር መሬት በተለያዩ የአትክልት ዘሮች ተሸፍኗል። አልፎ አልፎም ፍራፍሬዎች ተተክለዋል።

በትምህርት ቤቱ እየተከናወነ ያለው የግብርና ሥራ ለተግባር ተኮር ወይንም እይታና ክወና ጥበብ ትምህርት እያገዘ ነው። ተማሪዎች ስለአትክልት ልማት፣ ከብት ማድለብ፣ ንብ ማነብ በተግባር ያረጋግጣሉ። የአካባቢ ሥነምሕዳር በመጠበቅና አረንጓዴ ገጽታን በማላበስ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት እንዲኖር በማድረግ የሚያሳልጥ ሆኖ ተገኝቷል። ቆሻሻን ወደሀብትነት በመቀየር ተሞክሮ መገኘቱንና ቆሻሻ ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ተቀይሮ መልሶ ለአትክልት ልማት እየዋለ መሆኑን ርዕሰ መምህሩ ገልፀዋል።

ልማቱ ዘላቂ እንዲሆን በትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ እንዲከናወን መደረጉን የጠቆሙት ርዕሰ መምህሩ፤ በልማቱ የሚሳተፉት ለምገባ ፕሮግራም በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ እንዲሁም ከሚያገኙት ገቢ 10 በመቶ ያህሉን በኑሮ አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ እንዲያግዙ የማድረግ አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም ማኅበራዊ መደጋገፍንና አብሮነትን በማጠናከር መልካም ተሞክሮ እያስገኘ ነው ብለዋል። ትምህርት ቤቱ የመሬትና አንዳንድ ድጋፎችን በማድረግ እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

የጉድጓድ ውሃ አለመኖርና በአንዳንድ የአትክልት አይነቶች ላይ አልፎ አልፎ የሚያጋጥመው የዘር እጥረት ካልሆነ እስካሁን ባለው ጥሩ የልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መምህሩ በተለይ የጉድጓድ ውሃ ለማውጣት እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀዋል። ትብብርም ጠይቀዋል። ትምህርት ቤቱ 6458 ተማሪዎች እንዳሉትና ቁርስና ምሳ የምገባ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን በአሁኑ ጊዜ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ወደ 2199 የሚሆኑ ተቋማት እንዲሳተፉ እያደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ አቶ ባዩ ገልፀዋል። ከጥር ወር እስከ ኅዳር 2017 ዓ.ም. በሌማት ትሩፋት የተሠሩ ሥራዎች መገምገማቸውንና ወደ ንቅናቄ ሥራ መገባቱን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በዚህም ከዚህ ቀደም በግብርና ሥራ ውስጥ ያልተሳተፉ አዲስ 198 ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ግብዓት ለማሟላት መንግሥት በጀት ይመድባል። 40 በመቶ መንግሥት፣ ቀሪው ሀብት ደግሞ ከባለሀብቶች፣ ከግብረሠናይ ድርጅቶች ይሰበሰባል። በዚህ መንገድ ወደ 386ሚሊዮን ብር በሦስት ወር ሥራ ላይ ውሏል።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You