ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ ግንኙነታቸውን ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ ተስማሙወደ

አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ ተስማሙ። የሀገራቱን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ወዳጅነታቸውን ማጠናከር በሚያስችሉ የትብብር መስኮች ላይ የመግባቢያ ስምምነቶችም ተፈራርመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በ5ኛው የኢትዮጵያና የአልጄሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ እንዳስታወቁት፤ በኢትዮጵያ እና በአልጄሪያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነት ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ነው።

የሀገራቱን ግንኙነት ማጠናከር የፖለቲካ አጋርነት እና የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ ወሳኝ ነው ያሉት ጌዲዮን (ዶ/ር)፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ለማሳደግ በጤና፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውንም ገልፀዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ለረዥም ዓመታት የቆየውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተው፡- የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና አጋርነት ለመሸጋገር የሚኒስትሮች የጋራ ስብሰባው ወሳኝ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል። የአልጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ በበኩላቸው፤ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

እ.ኤ.አ. በ2022 የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የርስ በእርስ ጉብኝት ማድረጋቸው ግንኙነቱ ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከፍ እንዲል እና የኢኮኖሚ ትብብሮች እንዲሻሻሉ ማድረጉን ጠቁመዋል። ሁለቱ ሀገራት በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በግብርና፣ በኢነርጂ እና በሌሎች ዘርፎች በትብብር እና በአጋርነት ለመሥራት ትልቅ አቅም እንዳላቸውም አመልክተዋል።

ሁለቱ ሀገራት ከአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ ጀምሮ በአሕጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያሏቸውን ጠንካራ አቋም ዳግም ማንፀባረቅ እንዳለባቸው አመልክተዋል። የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ሀገራቸው ትኩረት ሰጥታ እንደምትሠራም አረጋግጠዋል። በጋራ ስብሰባው ማብቂያም የሀገራቱን ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ወዳጅነታቸውን ማጠናከር በሚያስችሉ የትብብር መስኮች ላይ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራርመዋል።

የሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን የቴክኒክ ኮሚቴ በስብሰባው፡- የሀገራቱን ታሪካዊ ወዳጅነት በማጠናከር በትብብር መሥራት በሚያስችሉ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ በመምከር ከስምምነት እንደተደረሰ ተገልጿል።

በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በሳይንስና አካዳሚ፣ በኃይልና ማዕድን፣ በጋራ የቢዝነስ ምክር ቤት፣ በግብርና፣ በፈጠራ፣ ስፔስ ሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በጤና እና ፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ፣ በባህልና ስፖርት መስኮች የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቶቹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ከአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ ጋር ተፈራርመዋል።

5ኛው የኢትዮጵያና የአልጄሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ትናንት ተጠናቋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You