
አዲስ አበባ፡- ዓመቱ በታሪካችን ትልቁን የኢኮኖሚ ሪፎርም ያደረግንበት ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ አስታወቁ። መንግሥት ከድጎማ አንጻር በጣም ሰፊ ሥራ በመሥራቱ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተረጋጋ ማኅበራዊ እና ሀገራዊ ሁኔታ እንዲኖር አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ አመለከቱ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ የ2017 በጀት ዓመት የ3ኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈጻጸም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ያለፉትን ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ዓመቱ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ መርሐ ግብር ያደረግንበትና በታሪካችን ትልቁን የኢኮኖሚ ሪፎርም ያካሄድንበት ነው። መርሐ ግብሩም በሁሉም ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ እድገት አመላካቾች ሲታይ በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ብለዋል።
የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ፤ ደረጃ በደረጃ በገበያ የሚወሰን የወለድ ተመንን የሚመራ የሞኒተሪንግ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆኑ፤ ገቢያችንን ለማሳደግና ወጪያችንን ውጤታማ ለማድረግ የፊሲካል ፖሊሲ መነደፉ እንዲሁም የእድገት አማራጮችን ለማስፋት የግሉን ሴክተር ሚና ማሳደግ መቻሉ ለውጤቱ መገኘት ወሳኝ አቅም መፍጠሩን አመልክተዋል።
ኢንፊሌሽንን በመቆጣጠር ረገድ በጣም ጥሩ ውጤት መታየቱን፤ ከባለፉት ወራት አሁንም የቀነሰበት ሁኔታ መኖሩን ያስታወቁት ሚኒስትሩ፤ የመጣው ፈጣን እድገት እንዲሁም ኢንፊሌሽንን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት የተመዘገበው ውጤት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤታማ መሆን መጀመሩን የሚያሳይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ የገቢ አቅማችንን በማሳደግ ረገድ ጥሩ ውጤት እየመጣ ነው፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ሪፎርም ማድረጋቸው የዘንድሮ ገቢያቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ማስቻሉን ጠቁመዋል። በኤክስፖርትም ላይ እንዲሁ የተሻለ አፈጻጸም ስለመኖሩም አስታውቀዋል።
ምንዛሪ ክምችት፤ በብሔራዊ ባንክም ሆነ በባንኮች የምንዛሪ ግኝት እየተሻሻለ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በፊሲካል ደረጃ በፊት ከነበረው የተሻለ ገቢን ለማሳደግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት ተሰጥቶና ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን እና ሌሎችም ተቋማት ባሉበት በግብረ ኃይል መልክ ሲሠራ መቆየቱን ጠቁመዋል።
የታክስ አስተዳደርን በማሻሻልና ክትትልን በማሳደግ እንዲሁም የታክስ ሕግ ተገዢነትን በማሳደግ ረገድ በጣም ጥሩ ውጤት እየመጣ ስለመሆኑ፤ በዚህ ረገድም የዘጠኝ ወር እቅዱን መቶ በመቶ ማሳካት እንደተቻለ አስታውቀዋል።
«G-20 ክሬዲተር ኮሚቴ” ከሚባል የኢትዮጵያ አበዳሪ ቡድን ጋር ሰፊ ውይይት ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰው፤ በመርሕ ደረጃ ከስምምነት መደረሱን ጠቁመዋል። በስምምነቱም ኢትዮጵያ የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ እፎይታ ወይም ሽግሽግ የምታገኝበት ሁኔታ ላይ በመርሕ ደረጃ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል። በቅርቡ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ እንደሚፈረምም አመልክተዋል።
ከኮሚቴው ጋር በጠቅላላው እና በሂደት ደግሞ ከእያንዳንዳቸው አበዳሪ ሀገራት ጋር ዝርዝር ውይይት የሚደረግ ስለመሆኑ ጠቁመው፤ ይህም የዕዳ ጫናን በመቀነስ ረገድ በዚህ ዓመት የተገኘ ትልቅ ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙን ተከትሎ የምንዛሪው ተመን በገቢው በመወሰኑ ኢምፖርቱ በማኅበረሰብ ላይ የሚያመጣውን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል ከፍተኛ ድጎማ መደረጉንም ጠቅሰዋል። ለማዳበሪያ፣ ለነዳጅ፣ ለምግብ ዘይት እና ለመሠረታዊ የመድኃኒት አቅርቦቶች ከፍተኛ ድጎማ መደረጉን ገልጸዋል። ለመንግሥት ሠራተኞች ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪ መደረጉን አስታውሰዋል። በግብርና ምርት አቅርቦት ረገድ ከፍተኛ ሥራ በመሥራት የምግብ አቅርቦት እንዲሻሻልና የኢንፊሌሽን ጫና እንዳይከሰት ጥሩ ሥራ ስለመሠራቱም አንስተዋል። መንግሥት ከድጎማ አንጻር በጣም ሰፊ ሥራ በመሠራቱ የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተረጋጋ ማኅበራዊ እና ሀገራዊ ሁኔታ እንዲኖር አስተዋፅዖ እያበረከተ እንዳለ ገልጸዋል።
የየሴክተሮች የኢኮኖሚ እድገትም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል። የግብርናን አፈጻጸምና በኢንዱስትሪው ዘርፍ የታየው የአቅም አጠቃቀም ማሻሻል ውጤት የታየባቸው እንደሆኑም ለአብነት ጠቅሰዋል። የአገልግሎት ዘርፍን በማስፋፋት ረገድና በኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽንን በማሳደግ ረገድ ያለው መሻሻልም በጣም ጥሩ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የተጀመሩት የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ምርታማነትን ማሻሻል፣ የንግድ ሥርዓትን ማሻሻል፣ ኤክስፖርትን ማሳደግ፣ ገቢን ማሳደግ፣ የወጪ ቁጠባን እና ውጤታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸምን በማሳደግ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው መግባባት ላይ መደረሱንም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ ገልጸዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም