በእውቀት የታነጸ ግብር ከፋይ ለማፍራት

ከትርፍ ግብር ከፋዮች 66 በመቶ የሚሆኑት በኪሳራ ወይም ያለትርፍ የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ አድርገው የሚያሳውቁ መሆናቸውን በገቢዎች ሚኒስቴር የምስራቅ አዲስ አበባ አነስተኛ ግብር ከፋይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል።

ችግሩን ለመፍታት የሕግ ማስከበር ሥራ በመሥራት ግብር ከፋዩን ከማስጨነቅ ይልቅ፤ ግብር ከፋዩ ግንዛቤ ኖሮት፤ ለግብር ሕግ ተገዢ እንዲሆን ለማስቻል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ለደንበኞች ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል። የዘንድሮውን ዓመት ጨምሮ ሥልጠናው መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአጠቃላይ 2ሺህ 168 ግብር ከፋዮች ሥልጠና መውሰዳቸውን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት አንድ ሺህ 128 ግብር ከፋዮች በሶስት የሥልጠና ዘርፎች፤ ለሶስት ወራት ሥልጠና በመስጠት፤ ባለፈው ሳምንት አስመርቋል። በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ጥሩ ውጤት በማምጣት ከአንድ እስከ 10 ያለውን ደረጃ በመያዝ እውቅና ያገኙ ተመራቂዎችን አዲስ ዘመን ጋዜጣ አነጋግሯል።

ከናጎድ ቢዝነስ ግሩፕ አቶ ናትናኤል ጥሌክስ እንደሚናገሩት፤ ሥልጠናው በሞጁል ተከፍሎ ለሶስት ወራት የወሰደ ሲሆን፤ በሥልጠናው ዝቅተኛ ከሚባሉት የታክስ ጉዳዮች አንስቶ ከፍተኛ እስከሚባሉት ደረጃ ሥልጠና መውሰዱን ተናግሯል።

ሥልጠናውን ከመውሰዱ በፊት ግብር ሊከፍል ሲሄድ ብዙ ጊዜ ጥፋት በመሥራት እንደሚቀጣ የሚናገረው ናትናኤል፤ “ብዙ ጊዜ ወደ ቢሮ ሲሄድ ይሄኮ አይቻልም፤ እንደዚህ ማድረግ ነበረብህ ይሉኛል። አብዛኞቹን ጉዳዮች በቅጣት እያወቅሁ የመጣሁ ቢሆንም፤ ሥልጠናው ደግሞ አዳዲስ እውቀቶችን በመጨመር ከተጨማሪ ቅጣት ታድጎናል “ ነው ያሉት።

“ሥልጠናው መብቴንም እንዳውቅ ስላደረገኝ፤ በቅርብ ጊዜ ሊቀጡኝ ሲሉ በተማርኩት መሠረት በማስረዳት ለመትረፍ ችያለው።” ከዚህ አኳያ ሥልጠና መውሰዱ በራስ መተማመንን ይጨምራል፤ መብትን አውቆ ለመከራከር እና በግንዛቤ እጥረት ከመቀጣትም ያድናል ይላሉ።

ሠልጣኙ እንደሚገልጹት፤ እንደ ሀገር አብዛኛው ሰው ስለ ግብር አይነቶች ስለማያውቅ ጥፋት አጥፍቶ ከተቀጣ በኋላ ነው የሚማረው። ከዚህ አንጻር ቅጣቱ ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ለሶስት ወር ባይሆንም፤ በተቻለ አቅም ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት ለድርጅት ኃላፊዎች ስለ ግብር ሥልጠና ቢሰጥ መልካም ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ አሁን በኦንላይ ሪፖርት ማድረግ ተጀምሯል፤ ነገር ግን ሌሎችም ሥራዎች በኦንላይ እንዲያልቁ ቢደረግ ግብር ከፋዩ ቢሮ ሄዶ ከመንገላታት እንዲተርፍ እና ጊዜውን እንዲቆጥብ ያስችላል ይላሉ።

ከፒቤላ ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አቶ ደረጀ አጥናፉ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ሥልጠናው ወቅታዊ የሆኑ የታክስ ሕጎችን አጠቃሎ በያዘ መልኩ በሶስት ክፍል ነው የተሰጠው። ማለትም በቀጥተኛ ታክስ፤ ቀጥተኛ ባልሆነ ታክስ እና በግብር አስተዳደር የሚያጠቃልል ነው።

ሥልጠና መሰጠቱ ግብር ከፋዩ ግዴታውን በማወቅ የሚጠበቅበትን ግብር እንዲከፍል እና መብቱን ተረድቶ መጠየቅ እንዲችል ይረዳል። ስለሆነም ሥልጠናው ለግብር ከፋዩ ብቻ ሳይሆን፤ በማስተማር ሥራ ላይ የተሰማሩ ሁሉ ሊያውቁት የሚገባ መሆኑንም ያስረዳሉ።

አሁን እየሰለጡኑ ያሉት የፌዴራል ግብር ከፋዮች ብቻ ናቸው የሚሉት አቶ ደረጀ፤ ነገር ግን በቀጣይ በከተማ አስተዳደር እና በክልል ደረጃ የሚገኙ ግብር ከፋዮች ተመሳሳይ ሥልጠና ሊወስዱ ይገባል። ይህም መንግሥት ለመሰብሰብ ያቀደውን የግብር መጠን እንዲሰበስብ እና የሀገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ ያስችላል ሲሉ ይጠቁማሉ።

ሥልጠናው መሠረታዊ የሆኑ የታክስ ሕጎችን የያዘ በመሆኑ ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ እንደረዳቸው የሚገልጹት፤ ከአህመት አይዴኒዝ ድርጅት አቶ መሳይ በለጠ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ከዚህ በፊት ታክስ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት አንድ ግብር ከፋይን በዚህ ጥፋት ምክንያት ተቀጥተሃል፤ በዚህ ሕግ መሠረት ቅጣቱ ተፈጻሚ ይሆናል፤ ብሎ ማስተላለፍ እንጂ፤ የታክስ ሕጎችን ለግብር ከፋዩ የሚያስተምርበት ባህል አልነበረም።

“አሁን የግብር ሕጎችን ወደ ድርጅቶች ወይም ወደ ደንበኛው ወርደው ሥልጠና እንድናገኝ ማድረጉ ብዙ ነገር እንድንረዳ አድርጎናል።” ግንዛቤ ማግኘቱ ደግሞ ግብር ከፋዩ መብቱን አውቆ እንዲጠይቅ እና ለሚቀርቡ ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ እንዲሰጥ ያስችላል ይላሉ።

አሁንም ቢሆን ሁሉንም ነገር አውቀናል ማለት አይቻልም የሚሉት ሠልጣኙ፤ ለወደፊት የግብር አሰባሰቡን የተሻለ ለማድረግ፤ ግብር የሚሰበስበው ተቋም ከደንበኞች ጋር ተቀራርቦ ሊሠራና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናውን ሊያጠናክር ይገባል በማለት ይጠቁማሉ።

አቶ መልካም ዓለም ከሀፍኮም ድርጅት ሌላኛው ተሸላሚ ሠልጣኝ ናቸው። እሳቸው እንደሚናገሩት፤ “ጡረታ ከመውጣቴ በፊት ለረጅም ዓመታት የሠራሁት ገቢዎች ቢሮ ነው። ከዛ ወጥቼ ከልጄ ጋር ወደ ግል ሥራ ስሠማራ በጥሩ ነገር ያየሁት ሥልጠና ነው።”

“የዚያን ጊዜ የምናሰለጥናቸው ግብር ከፋዮች ውስን ነበሩ።” አሁን ላይ በስፋት መሠራቱ ግብር ከፋዩ ከቅጣት እንዲድን፤ እውቀት ኖሮት በጊዜ ሪፖርት እንዲያቀርብ፤ የሚቀጥራቸውን ሠራተኞች እንዲቆጣጠር እና የድርጅቱን የሂሳብ ሥራ መሥራት እንዲችል ይረዳል ይላሉ።

በቀጣይም ሥልጠና የመስጠት ተግባሩ እንዲጠናከር፤ በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች አዳዲስ መመሪያዎች የመላክ ሥራው ደንበኛው አንብቦ ግንዛቤ እንዲኖረው ስለሚያስችል ቢበረታታ እና የተቋሙ ድረ ገጽ ፈጣን እንዲሆን ቢደረግ መልካም ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You