ቋሚ ኮሚቴው የወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል በጎ አድራጎት ኮሚቴ የገንዘብ እንቅስቃሴ ኦዲት እንዲደረግ አሳሰበ

አዲስ አበባ፡-የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የወሎ ተርሸሪ ኬር እና ማስተማሪያ ሆስፒታል በጎ አድራጎት ኮሚቴ እስካሁን ድረስ ያደረገውን የገንዘብ እንቅስቃሴን ኦዲት አድርጎ እንዲያቀርብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር)የወሎ ተርሸሪ ኬር እና የማስተማሪያ ሆስፒታል በጎ አድራጎት ኮሚቴ፤ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ የሥራና የንብረት ርክክብ በተመለከተ ቅድመ ውይይት ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ባለሥልጣኑ የበጎ አድራጎት ኮሚቴው ያደረገውን የገንዘብ ወጪ እና ገቢ በውጪ ኦዲተሮች ኦዲት አስደርጎ ለቋሚ ኮሚቴው እና ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ሊያቀርብ ይገባል።

የልማት ድርጅቶችን፤ ማህበራትን እና ባንኮችን ጨምሮ ኦዲት የሚያደርጉ በመንግሥት እውቅና የተሰጣቸው የግል ተቋማት መኖራቸውን በመጠቆም፤ ባለሥልጣኑ ለዩኒቨርሲቲው የሚያስረክበውን 94 ሚሊዮን ብር በተመለከተ አጠቃላይ የነበረውን የባንክ ሂሳብ እንቅስቃሴ ኦዲት አስደርጎ ርክክብ ከመደረጉ በፊት የኦዲት ግኝቱን እንዲያቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

ሰብሳቢዋ እንደተናገሩት፤ ኦዲት የሚደረገው የገንዘብ እንቅስቃሴ ኮሚቴው ወደ ሥራ ከገባበት አንስቶ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ያለው ነው። ነገር ግን ሌላ ተጨማሪ ኦዲት እንዳይደረግ ከመጋቢት 30 ጀምሮ የበጎ አድራጎት ኮሚቴው የሥራ እንቅስቃሴ መቆም አለበት ብለዋል።

የወሎ ተርሸሪ ኬር እና ማስተማሪያ ሆስፒታል በጎ አድራጎት ኮሚቴ የሕዝብ አደራን ተቀብሎ እስካሁን ድረስ ሲሠራ ለቆያቸው ሥራዎች ምስጋና አቅርበው፤ ነገር ግን ማስተባበሪያ ኮሚቴው ሥራውን ለዩኒቨርሲቲው አስረክቦ ቢዘጋም፤ በሥራ ሂደት ለተፈጠሩ ስህተቶች ተጠያቂነት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የሆስፒታሉ ግንባታ በመንግሥት በጀት እየተሠራ እንደመሆኑ የወሎ ዩኒቨርሲቲ፤ ከሕዝብ የተሰበሰበው 94 ሚሊዮን ብሩ የሆስፒታሉ ግንባታ ላይ መካተት እንዳለበት ወይም ለሕዝቡ አስፈላጊ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግ ተወያይቶ እንዲወስን አቅጣጫ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም ኦዲት ከተደረገ በኋላ ከባለሥልጣኑ ማረጋገጫ በመውሰድ፤ የወሎ ዩኒቨርሲቲና ባለሥልጣኑ ተወያይተው እስከ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም በደሴ ከተማ የርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ሕዝብ በተሰበሰበበት በይፋ መደረግ እንደሚኖርበት አመልክተዋል።

የወሎ ተርሸሪ ኬር እና ማስተማሪያ ሆስፒታል በጎ አድራጎት ኮሚቴ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ አየለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ 122 ሚሊዮን ብር ለሆስፒታሉ ግንባታ በተለያየ መንገድ ተሰብስቧል።

አጠቃላይ ከተሰበሰበው ብር ለሆስፒታሉ ዲዛይን ማሠሪያ፣ ለአፈር ምርምር፣ ለቤት ኪራይ፣ የሠራተኛ ደመወዝ እና ሌሎች ወጪዎች ወጥተው በአሁኑ ጊዜ በባንክ ያለው እና ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ርክክብ የሚደረገው ሂሳብ 94 ሚሊዮን ብር ነው ሲሉ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በወጭ ሀገራት ያሉት የኢትዮጵያ ተወላጆች ድጋፍ እንዲያደርጉ ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ኩፖን ቢላክም፤ የተሰበሰበው ገንዘብ 438 ሺህ 526 ብር ብቻ መሆኑን ገልጸው፤ ለሥራው አለመሳካት የኤምባሲዎች ክፍተት እንደነበር ጠቁመዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You