
አዲስ አበባ፦ የትምህርት ጥራት ችግርን ከመሠረቱ ለማስተካከል በመጪው ዓመት ሁለት ሺህ 147 ትምህርት ቤቶች የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት መስጠት እንደሚጀምሩ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ የቅድመ አንደኛ እና የልዩ ትምህርት አስተባባሪ አቶ አሰግድ አታሂል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ የሚከናወኑ ተግባራት በቀጣይ የትምህርት ደረጃዎች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መሠረት የሚጥሉ ናቸው።
ከዚህ አኳያ በትግራይ ክልል ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ሳቢና ማራኪ እንዲሆኑ ከማድረግ ጀምሮ መምህራንን የማሠልጠንና የማብቃት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረው፤ ይህም የትምህርት ጥራት ችግርን ከመሠረቱ ለማሻሻልና በሥነ ምግባር የታነጸ ብቁ ትውልድ ለማፍራት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
በ2015 ዓ.ም ትምህርት ሚኒስቴር ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሆን መጽሐፍ አዘጋጅቶ በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ እንዲደረግ ሲሠራ መቆየቱን አውስተው፤ ነገር ግን በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሳይገነቡ ቀርተዋል ነው ያሉት።
በትግራይ ክልል በ2016 ዓ.ም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከአጋር አካላት ጋር ምክክር መደረጉን ጠቁመው፤ በምክክሩ መሠረት በዘንድሮ ዓመት ኽልተ አውላዕሎ እና ገረዓልታ አካባቢዎች አምስት ትምህርት ቤቶች በሙከራ ትምህርት ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
በክልሉ በቀጣይ ዓመት ሁለት ሺህ 147 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ገልጸው፤ በክልሉ የመንግሥት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስኪገነቡ ድረስ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማር ማስተማር ሥራው እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በክልሉ 460 የግል የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል። አንደኛ ደረጃ ትምህርት ሶስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን በዚህም ስድስት ዓመት የሞላው ህፃን የደረጃ ሶስት ተማሪ ይሆናል። ደረጃ አንድ እና ሁለት ደግሞ አራትና አምስት ዓመት የሞላቸው ህፃናት ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም