“እንደ ሀገር ፈተናዎች እያለፉ፣ ቋጠሮዎችም እየተፈቱ በመሄድ ላይ ናቸው” – ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት

አዲስ አበባ፡- እንደ ሀገር በተወሰዱ ርምጃዎችና ማሻሻያዎች ፈተናዎች እያለፉ፣ ቋጠሮዎች እየተፈቱ እና ችግሮች እየተቀረፉ በመሄድ ላይ መሆናቸውን ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ገለጸ። ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን

የባሕር በር የማግኘት መብት ለማስከበር የተጀመረው ሥራ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል።

ምክር ቤቱ ትናንት ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ባደረገው ስብሰባ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን መገምገሙን አስታውቋል። በመግለጫው እንደተመላከተው፤ ባለፉት ዓመታት የተወሰዱ ሀገራዊ ሪፎርሞችና የተተገበሩ ኢኒሼቲቮች ፍሬ እያፈሩ ናቸው። በዚህም ፈተናዎች እያለፉ፤ ቋጠሮዎች እየተፈቱ፤ ችግሮች እየተቀረፉ በመሄድ ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ ለዘመናት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ስብራቶች ገጥመዋት እንደነበር ያስታወሰው ምክር ቤቱ፤ እነዚህን ስብራቶች በመጠገን ወደ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ እያፋጠነች ትገኛለች ብሏል።

እስካሁን የጀመረቻቸው ሪፎርሞች እየተሳኩ፤ የወጠነቻቸው ኢኒሼቲቮች ፍሬ እያፈሩ፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስከበር የምታደርገው ጥረት ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ለዚህ ምስክር መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል።

ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና አጋሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች እየተገኙ ያሉ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ድጋፎች ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሪፎርሞች ስኬት ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን አመላክቷል።

ሀገራዊ የሰላም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ምክር ቤቱ መገምገሙን አመላክቶ፤ ሕዝቡ የግጭትንና የጦርነትን አስከፊ ገጽታ በመረዳት ከግጭት ጠማቂዎች ጋር ላለመተባበር ያሳየው ቆራጥነት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። መንግሥት ለሰላማዊ መፍትሔ ያለው የጸና አቋምና ያደረገው እንቅስቃሴም ለውጤቱ መገኘት ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁሟል።

በትግራይ የነበረው ጦርነት በሰላም እንዲፈታ መንግሥት ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ሕዝቡ እፎይታ እንዲያገኝ አስችሎታል ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ፤ የሰላም ስምምነቱ መንግሥታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች እንዲከናወኑ፣ መሠረተ ልማቶችም እንዲጠገኑ አድርጓል ሲል አመልክቷል።

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎችም መንግሥት ሕግ በማስከበርና የሰላም መንገዶችን በማበረታታት ባከናወነው ተግባር አያሌ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በሌሎችም የሀገራችን አካባቢዎች የሰላምና የጸጥታ ሁኔታው ይበልጥ እየጸና እንደሚገኝም የደኅነት ምክር ቤቱ በጥልቀት ገምግሟል ብሏል።

እንደ ምር ቤቱ መግለጫ፤ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ካለበት ነባራዊ ሁኔታ፣ ዓለም እየሄደች ከምትገኝበት የፖለቲካና የኢኮኖሚ መንገድና ከምናልመው የብልፅግና መዳረሻ አንጻር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች አሉ። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሊኖር የማይገባውን፣ ፍላጎትን በኃይል የማስፈጸም ኋላ ቀር አማራጭ የሚከተሉ አካላትን የተመለከተ ነው። እነዚህ አካላት መልካቸው ይለያይ እንጂ በተለያዩ አካባቢዎችና በውጭ ይገኛሉ።

ጥፋት የጋራ ዓላማቸው በመሆኑ ተቀናጅተው ለማጥፋት ይሞክራሉ። ሕጋዊ የፓርቲ ሽፋኖችን ለሕገ ወጥ ተግባራት ይጠቀማሉ፤ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለሁከት ተግባር ለመጠቀም ይሠራሉ ብሏል።

በተጨማሪም በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር የመንግሥትን ሥራዎች በማደናቀፍ የተጠመዱ መኖራቸውን የጠቀሰው መግለጫው፤ በማኅበራዊ ቦታዎች፣ በቤተ እምነቶች፣ በመሥሪያ ቤቶች እና በንግድ ቦታዎች ተሰግስገው እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም እንደሚሞክሩ ጠቁሟል።

እነዚህ ኃይሎች የሐሰት ፕሮፓጋንዳውን የሚመሩ ክንፎችም እንዳላቸው አመላክቶ፤ መደበኛውንና ማኅበራዊውን ሚዲያ በመጠቀም የሕዝቡን ሰላም ይረብሻሉ። የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና የጸጥታ ተቋማት ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅተው በሚሠሩት ሥራ የጥፋት ኃይሎች ዓላማ እንዳይሳካ፣ አቅማቸው፣ ምኞታቸውም ከንቱ ሆኖ እንዲቀር መደረጉን አስታውቋል።

ከሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታዎች በተጨማሪ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ሁኔታዎችም በደኅንነት ምክር ቤቱ በጥልቀት መታየታቸው የተመላከተ ሲሆን፤ በሀገራችን ላይ ሊያሳድሩት የሚችሉት ተጽዕኖ በዝርዝር ውይይት እንደተደረገበት በመግለጫው ተጠቁሟል።

ሰላም፣ ጸጥታና ደኅንነት ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር የተሳሰሩ ናቸው ያለው ምክር ቤቱ፤ ፖለቲካዊ ብስለት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ማኅበራዊ መረጋጋት፣ የአንድን ሀገር የሰላም፣ የጸጥታና የደኅንነት ሁኔታዎችን ያሻሽላሉ። ከዚህ አንጻር በቅንጅት በመሥራት የተጀመሩ ሪፎርሞችን ወደ ማጽናት ምእራፍ ማድረስ ይገባናል ብሏል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት የተጀመረው እንቅስቃሴ ፍሬ እያፈራ መሆኑን ጠቅሶ፣ ይሄን ሥራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ባህላዊ መንገዶችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰላማዊ መንገዶች መጠቀም ይገባል። የሰላም መንገድን መርጠው ለሚመጡ አካላት ተገቢውን ክብካቤ ማድረግ እና ሠልጥነው ወደ ሕዝቡ እንዲቀላቀሉ መሥራት ያስፈልጋል።

የሰላም አማራጮችን ዘግተው ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈጸም በሚንቀሳቀሱት ላይ የተጀመረውን ሕግ የማስከበር ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ በመግለጫው ተመላክቷል።

የተደራጁ የኢኮኖሚ ወንጀሎችንና አሻጥሮችን ማምከን፣ ብሎም ፈጻሚዎቻቸውን ለሕግ ማቅረብ ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው ያለው ምክር ቤቱ፤ የገንዘብ፣ የኢኮኖሚና የአስተዳደር ተቋማት ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊውን አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃዎች እንዲወስዱ አቅጣጫ ተቀምጧል ብሏል።

የኢትዮጵያን ዓለም አቀፋዊ ተሰሚነት የሚያሳድጉ የዲፕሎማሲ ውጤቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቁሞ፤ ይህን ይበልጥ በማስፋፋትና በማጠናከር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስከበር ተገቢ ነው። በተለይም የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት መብት ለማስከበር ዲፕሎማሲያዊ፣ ሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገዶችን መሠረት አድርጎ የተጀመረው ሥራ በተጀመረው ግለት እንዲቀጥል የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን የሰላምና የልማት ሥራዎች በመደገፍና እያስመዘገበች ላለችው ለውጥ ለሰጠው እውቅና አመስግኖ፤ በቀጣናው፣ በአህጉሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምንና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የነበራትንና ያላትን ከፍተኛ ሚና በመረዳት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You