ከጥሬ ዕቃ እስከ ምርት የተዘረጋ የጎጆ ኢንዱስትሪ

አቶ አብዱለጢፍ አህመድ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት ምስራቅ ሀረርጌ ዞን፣ ደደር ወረዳ ነው። እንደማንኛውም የአካባቢው ነዋሪዎች ኑሯቸውን በግብርና ከሚመሩ ቤተሰቦቻቸው በመወለዳቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲሠሩና ሲደክሙ ያሳለፉ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በኋላም እድሜያቸው ከፍ ሲል የዚያድባሬን ወረራ ለመቀልበስ በወቅቱ የነበረው መንግሥት ያደረገውን የሀገር ጥሪ ተቀብለው በ1970 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ይቀላቀላሉ። በመለካከያ ሠራዊት ውስጥ በነበራቸው ቆይታ በጉደር ጥይት ፋብሪካ ውስጥ የመሥራት እድል አጋጥሟቸዋል፤ ይህም ለዛሬው ሥራቸው አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው ይናገራሉ።

አቶ አብዱለጢፍ የ32 ልጆች አባት ስለመሆናቸው ገልጸውልናል። በአንጥረኝነት ሙያቸው ታግዘው ካሳደጓቸው ልጆቻቸው 22ቱን ልጆቻቸውን ኩለው፤ ድረው ለቁም ነገር ማብቃታቸውንም ተናግረዋል። አሁንም ይህንኑ ሥራ እየሠሩ ቀሪ ልጆቻቸውን በማሳደግ ላይ እንደሚገኙም ይገልጻሉ።

በዚህ ሥራ ከ20 ዓመት በላይ መቆየታቸውን እና ከዚህ ውስጥ ስምንቱን ዓመት በባቢሌ ከተማ ማሳለፋቸውን ያስረዳሉ።

አንጥረኛውን በአካባቢው ታዋቂ ያደረጋቸው ወድቅዳቂ አልሙኒየሞችን እያቀለጡ ወደ ቤት ዕቃነት የሚቀይሩ መሆናቸው ብቻ አይደለም። ግብዓት ሲያጥራቸው ወደ ማዕድኑ መገኛ ሥፍራዎች በመሄድ አፈር እያቃጠሉ ለሥራቸው ግብዓት የሚሆናቸውን አልሙኒየም የሚያመጡ መሆናቸውም ነው።

‹‹የአልሙኒየም እጥረት ሲያጋጥመኝ የተፈጥሮ ማዕድኑ ወዳለበት ወረዳ እና ሼዶን ወደሚባሉ ቦታዎች እየሄድኩ ጎርፍ ያመጣውን ደለል ሰብስቤ እሳት እለቅበታለሁ፤ በዚህን ጊዜ አልሙኒየሙ እየቀለጠ በሰነጠቅሁለት ቦይ ውስጥ ፈስሶ ወደ አንድ ቦታ ይጠራቀማል። ያንን አምጥቼ ጥቅም ላይ አውለዋለሁ። እዚህ አካባቢ ከለገ ደንቢና ከሻኪሶ ያልተናነሱ የተለያዩ ብረት ነክ ማዕድናት አሉ›› ሲሉ ያስረዳሉ።

አቶ አብዱለጢፍ አሁን ከተማ አስተዳደሩ ባደራጀው ጎጆ ኢንዱስትሪ ውስጥ ታቅፈው፤ በተሰጣቸው ሼድ ውስጥ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እያመረቱ በመሸጥ ይተዳደራሉ። በፋብሪካ የሚመረቱ ምርቶችን አስመስለው ሞልድ በማዘጋጀት ያቀለጡትን አልሙኒየም ሞልዱ ላይ በማፍሰስ የሚፈልጉትን ቁሳቁስ ይሠራሉ። ምርታቸው ጥራትና እድሜ ያለው በመሆኑም በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እጅግ ተፈላጊ እንደሆነ ይገልጻሉ።

የተለያዩ መጠን ያላቸው ድስቶች፣ ጭልፋዎች፣ ዋንጫዎች፣ የመኪና ስፔር ፓርትና መሰል ምርቶች ከሚሠሯቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚህን ምርቶች እየተረከቧቸው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመውሰድ የሚሸጡ 11 ቋሚ ደንበኞችን ማፍራታቸውንም ገልጸውልናል። የሚያመርቷቸውን ብረት ድስቶች እስከ 400 መቶ ብር በሚደርስ ዋጋ እንደሚያስረክቧቸውም ተናግረዋል። ትልልቆቹንም እስከ 2ሺህ 500 ብር ይሸጣሉ።

አንጥረኛው 91 ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶች ሥልጠና ስለመስጠታቸው እና የእውቀት ሽግግር ስለማድረጋቸውም ነግረውናል። በከተማው ከሚገኝ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በትብብር እንደሚደሠሩ፤ ኮሌጁ ወናፍን የሚተካና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ እሳት ማጋጋሚያ ማሽን እንደገጠመላቸው፤ እርሳቸውም ባህላዊና ተግባራዊ እውቀታቸውን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለተማሪዎችና ለመምህራን እያካፈሉ እንደሚገኙ አብራርተውልናል።

ለወደፊትም ትብብራቸውን አጠናክረው የመሥራት እቅድ እንዳላቸው ነግረውናል። ወጣቶች ከንድፈ ሃሳብ (ቴዎሪ) ትምህርት በዘለለ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴና ልምምድ ቢሸጋገሩ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ምክራቸውን ለግሰዋል ።

የባቢሌ ከተማ ከንቲባ አቶ አህመድ ነጃሽ እንደሚያስረዱት ፤ ‹‹በ2017 በጀት ዓመት በከተማዋ 22 የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን ለማደራጀት ታቅዶ እስከ አሁን በ17 የሥራ ዘርፎች የተዋቀሩ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። በዚህም ለ67 ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሯል። የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ሙያን የሚጠይቁ እንደመሆናቸው ከቴክኒክና ሙያ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዲያድጉ ብዙ ሥራ እየተሠራ ይገኛል›› ሲሉ አስረድተዋል።

‹‹ለምሳሌ አቶ አብዱለጢፍ የሚሠሩበት አልሙኒየም ማቅለጫና ቁሳቁስ ማምረቻ ብረትን ለማቅለጥ የሚጠቀመው በማኑዋል (በወናፍ) ነበር። ያንን የሚተካ ማሽን ከተማ አስተዳደሩ ገዝቶ ሲያቀርብ የቴክኒክና ሙያ ተቋሙ ደግሞ ማሽኑን በመገጣጠም ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጓል። የአንዱን ክፍተት አንዱ እየሞላ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከግብርና ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በሐረሪ ክልልና በሀረርጌ ዞን ባዘጋጀው የመስክ ምልከታ በተፋሰስ ልማት ፣ በጎጆ ኢንዱስትሪ፣ በሌማት ትሩፋት ፣ በመስኖ ልማት፣ በከተማ ግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በመሳሰሉት የተመለከትናቸው የልማት ሥራዎች ሁሉ የጋዜጠኞችን ቀልብ የሳቡና ተጠናክረው ቢቀጥሉ የታሰበው ሀገራዊ እድገት ሩቅ እንደማይሆን የሚያመላክቱ ስለመሆናቸው አስተውለናል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You