
አዲስ አበባ፡- በዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች በኦንላይን የንግድ ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ። በዘጠኝ
ወራት ከወጪ ንግድ አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱም ተገልጿል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ግምገማ በትናንትናው እለት አካሄደ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የሚኒስቴር መሥሪያቤታቸው የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ግምገማ ትናንትና ሲካሄድ እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል።
በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዓመታዊ አፈጻጸም ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር እንደነበረ በማንሳት፤ አሁን የወጪ ንግዱ እያደገ በመምጣቱ በዘጠኝ ወራት አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ለማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ጥራጥሬ፣ ቅባት እህል፣ ጫት እና ቁም እንስሳት በዘጠኝ ወራት 595 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ በሀገር ውስጥ የንግድ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ በተደረጉ ሥራዎች በኦንላይ የንግድ ፈቃድ ከመስጠት አንጻር በዘጠኝ ወራት 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሰዎች ተስተናግደዋል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ722 ሺህ ሰዎች ብልጫ አሳይቷል።
ከንግድ ፈቃድ አገልግሎት የተገኘው ገቢ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ግማሽ ቢሊዮን ብር እንደነበር አውስተው፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት አንድ ነጥብ 45 ቢሊዮን ለመድረስ መቻሉን አስረድተዋል።
የእሁድ ገበያን በተመለከተ በዘጠኝ ወራት 374 ተጨማሪ እሁድ ገበያዎችን ለመጨመር መቻሉን በመግለጽ፤ አጠቃላይ እንደ ሀገር ያሉት የእሁድ ገበያዎች አንድ ሺህ 438 ለማድረስ እንደተቻለ አመልክተዋል።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያስሚኒ ወሃብረቢ፤ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ሕገ ወጥ የወርቅ ንግዱ በመቀነሱ ወደ ብሄራዊ ባንክ የሚመጣው ወርቅ እጅግ በጣም ከፍ ሊል ችሏል ብለዋል።
በወጪ ንግድ ታሪክ በበጀት ዓመቱ የወርቅ አፈጻጸም፤ ቡናን መብለጥ ችሏል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የስምንት ወራት የማእድን ወጪ ንግድ አፈጻጸም ከ317 በመቶ በላይ ነው። የወርቅ አፈጻጸም ትልቁን ድርሻ የሚወስድ ሲሆን፤ በማድን ዘርፍ ለተገኘው የላቀ ውጤት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የዓለም አቀፍ የዋጋ ሁኔታ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፤ የወጪ ንግድ አፈጻጸም በግብርና 112 በመቶ፣ በማኑፋክቸሪንግ 57 በመቶ በኤሌክትሪክ እና በሌሎች ዘርፎች 94 በመቶ ለማሳካት ተችሏል።
የዓለም የወጪ ንግዶች ክፍያ መቀዝቀዝ፤ ሕገ ወጥ ንግድ፤ በወጪ ንግድ ላይ የኬላዎች ክፍያ መስፋፋት፤ የኢንተርኔት አቅርቦት ችግር እና የወጪ ምርት ኮንትራት ግዴታን አለመወጣት በሥራ ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩ አንስተዋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም